ዋዜማ ራዲዮ- በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ሚና ያለውና ያለፉትን ዓመታት በዘርፈ ብዙ ችግሮች ፈተና ላይ የወደቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ላጋጠመው ችግር መነሻ ናቸው ያላቸው በብድር ዘርፍ ላይ የነበሩ ከፍተኛ ሀላፊዎችን ከስልጣን ማንሳቱን ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ሰምታለች።
ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉት በጥቅሉ ስድስት ከፍተኛ ሀላፊዎች ሲሆኑ፣ ከዚህ ውስጥ ሁለቱ የብድር ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንቶች ፣ ማለትም የብድር አጸዳደቅ እና የብድር ግምገማ ምክትል ፕሬዝዳንቶች ናቸው። አራቱ ደግሞ በሁለቱ ምክትል ፕሬዝዳንቶች ስር ያሉ አራት በብድር ላይ የሚሰሩ ዳይሬክተሮች መሆናቸውን ተረድተናል።
በብድር ዘርፍ ላይ እየሰሩ ያሉ የባንኩን ሰራተኞች የመተካቱ ስራ እንደሚቀጥልም ተነግሯል።
ዋዜማ ራድዮ እንደሰማችው ከሆነ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር ዘርፍ ላይ ከሀላፊነት እንዲነሱ የተደረጉት ብዙዎቹ አቶ ባጫ ጊና የባንኩ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ጊዜ ከአዋሽ ባንክና ከኦሮምያ ህብረት ስራ ባንክ ያስመጧቸው ናቸው።አቶ ባጫ ለባንኩ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባት ተጠያቂ ሆነው ከሀላፊነታቸው ሲነሱ በሳቸው ምትክ ወደ ሀላፊነት የመጡት አቶ አቤ ሳኖ የአመራር ሽግሽግ በማድረግ ላይ ናቸው።ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገው የአመራር ምደባ በብድር ዘርፍ ላይ ሲሰሩ የነበሩ አመራሮችን በማንሳት በምትካቸው ሌሎች ተሹመዋል።ከአዋሽ ባንክ የመጡት አቶ ሙሉነህ አቦዬ በንግድ ባንክ የፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት በነበሩት ዳዊት ቀኖ ተተክተዋል።ሌላኛዋ በአቶ ባጫ ተሹመው የብድር ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ትእግስት አባተ በአቶ ሙሉነህ ለማ ተተክተዋል። በሁለቱ ምክትል ፕሬዝዳንቶች ስር የነበሩ አራት የብድር ዘርፍ ዳይሬክተሮችም ከሀላፊነታቸው ተነስተው በሌላ ተተክተዋል።ከሀላፊነታቸው ከተነሱት ዳይሬክተሮች መካከል ተካልኝ ቆርቻ እና ቴዎድሮስ ይቤ ይገኙበታል።
የመንግስት የፖሊሲ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለይ ከብድር አሰጣጥ ጋር የነበረው አፈጻጸም ለችግር ዳርጎታል። የሚሰጠው ብድር ከሰበሰበው ቁጠባ ጋር ካለመመጣጠኑም ባለፈ ከፍተኛ መድሎ የታየበትም ነበር።
የቀድሞው የባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ባጫ ጊና ከሀላፊነት ከመነሳታቸው በፊት በነበረው ያለፈው አመት የባንኩ የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ባንኩ የሰጠው ብድር ከሰበሰው ቁጠባ በእጥፍ በልጦ ነበር። nይህ ብዙም ያልተለመደና ባንኩን ለችግር ያጋለጠ ሆኗል።
የንግድ ባንኩ የ2012 በጀት አመት አፈጻጸምም ከእቅድ አንጻር ብዙ ጉድለት የታየበት ሆኖ አልፏል። በ2012 አ.ም የታቀደው ተቀማጭ ብር 100 ቢሊየን ብር ሲሆን የተሳካው 54 ቢሊየን ብር ነው። ይህ ከቀደሙት ሁለት አመታት አንጻር ዝቅተኛ ነው።የ2011 አ.ም ተቀማጭ ገንዘብ 89 ቢሊየን ብር ነበር። የ2010 አ.ም ደግሞ 87 ቢሊየን ብር ነበር።
የ2012 አ.ም ትርፍ 14 ቢሊየን ብር ነው።ይህ ከእቅዱ አንጻር 36 በመቶ የቀነሰ ነው። ከ2011 አ.ም አንጻር ደግሞ 10.3 በመቶ ቀንሷል።በ2012 አ.ም 42.5 ቢሊየን ብር ወጭ አደርጋለሁ ቢልም ወጪው ግን 55 ቢሊየን ብር ሆኗል።ይህም 64.3 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት አስቦ 69 ቢሊየን ገቢ ቢያገኝም ወጪው ስለናረ ብዙም ውጤታማ አላደረገውም ነበር።
ባንኩ በገባበት ችግር ምክንያት ለሰራተኞቹ ይሰጥ የነበረውን የቤትና የመኪና ብድር ለማቆምም ተገዷል። የአሁኑ የንግድ ባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ የተቋሙን ችግር ለመፍታት እየሰሩ እንደሆነ እየተነገረላቸው ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]