PM Abiy Ahmed and General Abdel Fattah Al-Burhan- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር ላይ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የኢትዮጵያና ወታደራዊና ሲቪል ልዑካን ቡድን በድንበር አካባቢ ተገኝቶ የሀገሪቱን ራስን የመከላከል ዝግጁነት የገመገመ ቅኝት ማድረጉን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

መንግስት የድንበር አካባቢ የፀጥታ ችግሩ የጋራ ወታደራዊ አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ አንዲጣራና በዲፕሎማሲ እንዲፈታ በይፋ የሱዳን መንግስትን ጠይቋል።

ከአምስት ቀናት በፊት ሱዳን በኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች የተደገፉ ታጣቂዎች ድንበሬን ጥሰው በመግባት ጥቃት አድርሰውብኛል ስትል ከሳለች። በጥቃቱ የሞትና የመቁሰል ጉዳት መድረሱንም ሱዳን ትናገራለች።ይህንንም ተከትሎ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በተፈጠረው ግጭት በኢትዮጵያም ሆነ በሱዳን በኩል ጉዳት ለደረሰባቸው ሀዘኑን የገለጸ ሲሆን እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች በሁለቱ አገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን ጥብቅ ወዳጅነት እንደማይወክል ገልጿል።


ይሁንና ከሱዳን በኩል የብቀላ ጥቃት ሊኖር ይችላል በሚል ስጋት መንግስት ወታደራዊ ዕዞቹን በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ ማዘዙን ሰምተናል። በዛሬው ዕለትም (ሰኞ) የአማራ ክልል የፀጥታ ሀላፊዎች እና በሰሜን እዝ አዛዥ ጀኔራል ድሪባ መኮነን የተመራ የልኡካን ቡድን ቅኝቶችን አድርጓል፡፡

ወታደራዊ አዛዦች የተካተቱበት የልዑካን ቡድን ጉብኝት በምእራብ ጎንደር የሚገኙ ባለኃብቶች በተረጋጋ መልኩ ስራቸውን ማከናወን እንዲችሉ አለኝታ መስጠትና የፀጥታ ዘርፉን ማዘመን እና በበቂ ሁኔታ በማሰማራት ከተለያዩ ትንኮሳዎች የመጠበቅ ዓላማ እንዳለውም ተረድተናል፡፡

ምእራብ ጎንደር ከሱዳን ጋር የ400 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው ድንበር የሚጋራ ሲሆን በድንበሩ አካባቢ ካለፉት አስራ አምስት አመታት ወዲህ ተደጋጋሚ ግጭት እየተፈጠረ መቆየቱን ነዋሪዎች ይናገራሉ። አካባቢው ሰፊ የጥጥ፣ ሰሊጥ፣ እጣን፣ እና ሌሎች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚደረግበት ነው።

በአካባቢው ባለኃብቶች ብቻ ሳይሆን ገበሬዎችም ጭምር መሬታቸው በሱዳን ወታደሮች እንደተወሰደባቸው እና የሱዳን የጦር ሰራዊት በቋራ እና ታች አርማጭሆ ባሉ አካባቢዎች የኢትዮጵያ ድንበር ጥሶ እንደገባ አቤቱታ ሲቀርብ መቆየቱ ይታወሳል። ዋዜማ የኢትዮጵያ ድንበር ስለመጣሱ በራሷ አላረጋገጠችም።

ከምንጮቻችን ባገኘነው መረጃ መሰረት የዛሬው የልዑካን ቡድኑ ቅኝት ሱዳን ሰሞኑን ወታደሮቼ ተገደሉብኝ በማለቷ የአጸፋ እርምጃ እንዳትወስድ የድንበሩን አካባቢ ለማጥበቅ እና አካባቢውን ለማልማት በሚደረገው ጥረት እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት ዘላቂ መፍተሄ ለማምጣት ነው ተብሏል፡፡

በሱዳን በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትርና በወታደራዊ ምክር ቤቱ መካከል ባለው ሽኩቻ ማዕከላዊነት ያለው የፀጥታ አመራር የለም። [ዋዜማ ራዲዮ]