- ከአለም ባንክ አሁን ላይ 84 ሚሊየን ዶላር ተገኝቷል። ከአይኤም ኤፍ ጋር ደግሞ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው።
- ባንኮች ለተበዳሪዎቻቸው የመክፈያ ጊዜን እንዲያራዝሙ የማግባባት ስራ እየተሰራ ነው ።ለደንበኞቻቸው ብድር መክፈያ ጊዜን ማራዘም የጀመሩ ባንኮችም አሉ።
- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ከሚገጥመው የከፋ ችግር ለመታደግ ከቀጣይ ቀናት የመንግስት ተጨማሪ ውሳኔዎች ይጠበቃሉ።
ዋዜማ ራዲዮ- በአለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን የፈጠረው የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰብአዊ ቀውስን ከማስከተሉ ቀድሞ ኢኮኖሚያዊ ጫናን ነው ማምጣት የጀመረው። ይህን ዘገባ እስካዘጋጀንበት ጊዜ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ሆነው የተገኙት ግለሰቦች 11 መሆናቸው ነው መረጃ ያለው። ምናልባትም ጥንቃቄዎች በተገቢው ካልተተገበሩ ቫይረሱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጥረው ሰብአዊ ቀውስ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል በመንግስት ደረጃ ግልጽ ስጋት አለ።
የኮሮና ወረርሽኝ በፈጠረው ዓለማቀፍ ቀውስ ሳቢያ ኢትዮጵያ ከወዲሁ ኢኮኖሚያዊ ጫና ውስጥ ገብታለች።ይህንንም የሚያጠና የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን ተዋቅሮ ከተለያዩ ዘርፍ ባለሀብቶች ጋር ውይይት ማድረግ ጀምሯል። ትላንት ሰኞም ከባንክ አመራሮች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል። ውይይቱም በቫይረሱ ምክንያት በፋይናንስ ዘርፉም ላይ ሆነ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊመጣ የሚችለው ተጽእኖም ምን ሊሆን እንደሚችልና እንዴትስ መወጣት ይቻላል? በሚለው ላይ ያተኮረ እንደሆነ ዋዜማ ራዲዮ ከንግድ ባንኮች አመራሮች መረዳት ችላለች።
ቫይረሱ በተለይ በኢትዮጵያ የንግድ አጋር በሆነችው ቻይናና በሌሎች ሀገራት መስፋፋቱ ከተሰማ በሁዋላ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ የንግድ ባንኮች ተበዳሪዎች ምርት መላክ ባለመቻላቸው ብድራቸውን መመለስ አልቻሉም። የባንኮች የገንዘብ እጥረት አንዱ ምንጭም ይኸው መሆኑ ይገለጻል።
የአበባ የወጪ ንግድ ኮሮና ቫይረስ ትልቅ ችግር ውስጥ ከጨመራቸው ውስጥ ቁጥር አንዱ ነው ።በመቶ ሚሊየን ዶላሮች ለኢትዮጵያ በአመት ሲያስገባም የነበረው አበባ አሁን በተግባርም ወደ ውጭ መላክ መቆሙም ተገልጿል። ውጭ ለመላክ ተዘጋጅቶ የተመረተ አበባም ተቀባይ ባለመኖሩ እስከ መቃጠል መድረሱንም ሰምተናል።
በዚህ የአበባ ዘርፍና በሌሎች የወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ የዘርፍ ተዋናዮችም ብድራቸውን መመለስ ባለመቻላቸው አበዳሪ ባንኮች ለባለሀብቶቹ የብድር መመለሻ ጊዜ እንዲያራዝሙላቸው እየጠየቁ ነው። ለደንበኞቻቸው ብድር ማራዘም የጀመሩ ባንኮች መኖራቸንም ዋዜማ ራዲዮ መረጃ ደርሷታል። ከብድርና ከውጭ ምንዛሬ ማግኘቱ በላይም ኮሮና ቫይረስ የፈጠረው ስጋት ለጥቅል ኢኮኖሚው የባሰ ውድቀትን ያመጣል የሚል ስጋትም አንዣቧል። የአበባ ዘርፍ እንኳ ቢወሰድ ኢንዱስትሪው በመቶ ሺህ ሰዎችን የቀጠረ እንደመሆኑ የዚህ ዘርፍ መቆም የዚያኑ ያክል ስራ አጥነትን የሚፈጥርና በዚሁ ገቢ የሚተዳደሩ ቤተሰቦችን ለችግር የሚዳርግ ነው።
መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ ቡድን አቋቁሞም እስከዚህ ሳምንት መጨረሻ ከተለያዩ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ጋር ከተወያየ በሁዋላ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለተጎዱ ሌሎች ዘርፎች መፍትሄ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዋዜማ ራዲዮ ከገንዘብ ሚኒስቴር ምንጮቿ መረዳት ችላለች። መፍትሄዎቹም የብድር የክፍያ ጊዜ ሽግሽግን ጨምሮ ተጨማሪ የገንዘብ ምንጮችን መፍጠርም ሊሆን ይችላል ተብሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለሚመጣው የኢኮኖሚ ችግር በቂ ገንዘብ ማቅረብ ስለማይችል ከአለማቀፍ የገንዘብ ምንጮች ማለትም ከአለም ባንክና ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ.ኤም.ኤፍ ጋር እየሰራ መሆኑም ታውቋል። እስካሁን ኢትዮጵያ የአለም ባንክ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ችግር ውስጥ ለገቡ ሀገራት ከመደበው ገንዘብ የሚደርሳት 84 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መሆኑን አውቃለች። ይህን ገንዘብም ተፈራርሞ መረከብ ብቻ እንደቀረም ነው ዋዜማ ራዲዮ የሰማችው።
ሆኖም ከአለም ባንክ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ጥረቶችም እንደሚቀጥሉም ተረድተናል።እስካሁን ያልታወቀውም ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ የሚገኘው የገንዘብ መጠን ነው።አይ ኤም ኤፍ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ችግር ውስጥ ለገቡ ሀገራት 50 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የመደበ ሲሆን ለእያንዳንዱ ሀገር ምን ያክል እንደሚደርስ ግን ገና አልታወቀም።ኢትዮጵያ አይ ኤም ኤፍ ከመደበው ገንዘብ ድርሻ ቢኖራትም መጠኑ ላይ ግን ፈጠን ያሉ ውይይቶች ተደርጎ ገንዘቡ ይለቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
መንግስት በቀጣይ ቀናት የተለያዩ ውይይቶችን ከተለያዩ ዘርፍ አንቀሳቃሾች ጋር ካደረገ በሁዋላ ከውጭ ከሚገኘው ገንዘብ ጋር የራሱንም የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም የዋጋ ግሽበትን አሁን ካለበት ደረጃ ይበልጥ እንዳይባባስ በሚያደርግ መልኩ ለመተግበር ማቀዱንም ሰምተናል።ሆኖም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፊቱ ከባድ ጫና ይጠብቀዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]