ዋዜማ ራዲዮ- የኮሮና ቫይረስን ስርጭትና ጉዳት ለመገመት በመንግስት በተሰራ የአደጋ ዝግጁነት ቀመር በኢትዮጵያ 28 ሚሊየን ያህል ሰዎች በቫይረሱ ሊያዙ እንደሚችሉ ዋዜማ ያገኘችው ሰነድ ያመለክታል።


የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በጋራ ባዘጋጁት በዚህ 22 ገፅ ሰነድ በከተሞች አካባቢ ያለው ማህበረሰብ ሙሉ በሙሉ ማለትም 23 ሚሊየን ያህሉ ለወረርሽኙ ተጋላጭ ነው።


50 በመቶ የገጠር ነዋሪ ማለትም 43 ሚሊየን ያህል ህዝብ ለወረርሽኙ የመጋለጥ አደጋ ያንዣበበበት ነው።


ይህ ጥናት የከፋ ሁኔታ ቢከሰት የሚለውን ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ ሲሆን የተለያይዩ የመከላከያ መንገዶች ተግባራዊ ተደርገውና መንግስት ባለው አቅም ተረባርቦም ቢሆን 28 ሚሊየን የሚጠጋ ሰው በቫይረሱ ሊጠቃ ይችላል። ይህ ጥናት ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የተጠናቀረ ሲሆን የቀጣዮቹ ሶስት ወራትን የታማሚዎች ቁጥር በየወሩ ከፋፍሎ አስቀምጧል።


የመጀመሪያው ወር

194,104 ስዎች ሊታመሙ ይችላሉ ከነዚህ ውስጥ 9,700 ያህሉ ፅኑ (ICU) ታማሚዎች እንደሚሆኑ መረጃው ያሳያል። 6, 600 የሞት አደጋም ሊያጋጥም ይችላል። ሀገሪቱ ባላት ውሱን የላብራቶር ምርመራ አቅም 1, 242 የሞት አደጋዎችን ብቻ በምርመራ መለየት ሲቻል የቀሩት የሞት አደጋዎች ወደ ምርመራ ሳይደርሱ ምክንያታቸው ኮኖና መሆኑ ሳይረጋገጥ የሚከሰቱ ሊሆኑ ይችላሉ።


በሁለተኛው ወር

211,750 የቫይረሱ ተጠቂዎች እንደሚኖሩ ሲገመት 10,588 ያህሉ በፅኑ (ICU) ታማሚዎች ናቸው። 7,200 የሞት አደጋ ሊያጋጥም ይችላል። 1,355 የሞት አደጋዎች በላብራቶር በተደረገ ምርመራ የተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዘ ሆኖ ይመዘገባል።

በሶስተኛው ወር

232,925 ህሙማን የሚኖሩ ሲሆን 11,646 ያህል ፅኑ (ICU) ታማሚዎች ይኖራሉ። 7, 900 ያህል የሞት አደጋ የሚኖር ሲሆን 1,491 በምርመራ የተረጋገጠ የሞት አደጋ እንደሚያጋጥም የጤና ሚኒስቴርና የኣኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ትንበያ ይናገራል።

ችግሩን ለመጋፈጥ ዘርፈ ብዙ እርምጃዎች እንደሚይስፈልጉ የተነተነው ሰነዱ ከፖለቲካ አመራር ጀምሮ በክልሎችና በፌደራል መንግስቱ እንዲሁም በተቋማት መካከል ከፍተኛ መናበብ እንደሚያስፈልግ አብራርቷል።


ቀዳሚው እርምጃ በሽታውን መከላከል ላይ ያተኮረ መሆን እንዳለበትና ይህን ተግባራዊ ለማድረግም ሳይንሳዊና ፈጣን እርምጃ የዜጎችን ህይወት እንደሚታደግ ይመክራል።


ከ14 ቢሊየን ብር በላይ የገንዘብ ወጪ ለዚህ የመከላከል ዘመቻ እንደሚያስፈልግም በሰነዱ ተብራርቷል። ትንበያው ይሆናልን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በመመልከት ሊከለስ እንደሚችል ሰነዱ ያሳስባል።አንዳንድ ሙያዊ መስፈርቶችንም እንዳልተገበረ ጥናቱ አምኗል። የሰነዱን ጨመቅ ከታች ይመልከቱ [ዋዜማ ራዲዮ]