ዋዜማ ራዲዮ- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ባለፈው አመት የካቲት ወር ማገባደጃ ላይ ለባለ እድለኞች እጣ ከወጣባቸው 32 ሺህ 653 13ኛው ዙር የ20/80 የጋራ መኖርያ ቤት ኮንደሚኒየሞች ለባለእድለኞች ምንም የማስተላለፍ ሳይሰራ አብዛኞቹን የማስተላለፍ ስራ ተጀምሯል : ርክክብም እየተፈጸመባቸው ነው ብለው መናገራቸው ከፍተኛ መደናገርና ቅሬታ አስነስቷል።
እነዚህ የጋራ መኖርያ ቤቶች እጣ ከወጣባቸው በኋላ የኦሮሞ መብት ተሟጋች ነን በሚሉ ግለሰቦች ፣ ቤቶቹ የተሰሩት የኦሮምያን ወሰን አልፈው ነው ፣ ቤቶቹ ሲሰሩ ለተነሱ አርሶ አደሮች የተከፈለው ካሳም በቂ አልነበረም በሚል ባስነሱት ተቃውሞ ቤቶቹ ለባለ እድለኞች እንዳይተላለፉ መደረጉ ይታወሳል።
የኦሮምያና አዲስ አበባን የወሰን ጉዳይ እንዲፈታ የመፍትሄ ሀሳብ የሚያቀርብ ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቢቋቋምም እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አላመጣም። እነዚህ አዝጋሚ ሁኔታዎች ባሉበት ምክትል ከንቲባ ታከለ የ20/80 ቤቶቹ እየተላለፉ ነው ማለታቸውም ባለ እድለኞቹን የመንግስት ቢሮዎችን ማንኳኳት እንዲጀምሩ አድርጓቸዋል።
ምክትል ከንቲባው ተመሳሳይ ይዘት ያለው መግለጫ ሁለት ጊዜ ያህል በኣአደባባይ ስጥተዋል። መጀመርያ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ፊት ቀርበው የአስተዳደሩን የስራ አፈጻጸም ሲያቀርቡ በአዲስ አበባና በኦሮምያ ክልል የአስተዳደር ወሰን ችግር ምክንያት ያልላለፉት የ20 /80 የጋራ መኖርያ ቤቶች ዘጠኝ ሺህ ብቻ እንደሆኑ ገልጸዋል። ከሳምንት በፊት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ላይ ቀርበው በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ በ13ኛው ዙር እጣ ከወጣባቸው የ20/80 የጋራ መኖርያ ቤቶች ውስጥ ከዘጠኝ ሺህ ቤቶች ውጭ ሌሎቹ ቤቶች ላይ መንግስት የማስተላለፍ ስራን እየሰራ እንደሆነ የሚያሳይ መልእክት ያለው ነገር ተናግረዋል።
ይሄን ተከትሎም ባለፈው አመት እጣ የወጣባቸው የቤቶች20/80 የጋራ መኖርያ ቤት እድለኞች ተደራጅተው ለመንግስት ጥያቄን ማቅረብ ጀምረዋል። ከቤት እድለኞቹ መካከል ከሶስት መቶ በላይ የሆኑት ተደራጅተው እሮብ እለት በአዲስ አበባ የቤቶች አስተዳደርና ልማት ቢሮ ተገኝተው ቅሬታቸውንና ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን ለዋዜማ ራዲዮ ገልጸዋል።
የቤቱ ባለ እድለኞች ለቤቶች አስተዳደር ቢሮው ያቀረቡት ጥያቄ ፣ የ20/80 ቤቶቹ ለኛ ለባለእድለኞቹ ሳይተላለፉ በምክትል ከንቲባው እየተላለፉ እንደሆነ የተናገሩበት መነሻው ምንድነው? የከተማ አስተዳደሩ የበላይ ባለስልጣን እንዲህ አይነት መረጃ ከሰጡስ እንዴት ለኛ እስካሁን እንዴት ጥሪ አልተደረገም ? ችግር አለባቸው የተባሉት ዘጠኝ ሺህ ቤቶችስ ተለይተው ታውቀዋል ወይ ? በትክክልስ መች ነው ቤቶቹን የከተማ አስተዳደሩ የሚያስረክበን ? የሚሉት ናቸው።
እሮብ እለት በአዲስ አበባ የቤቶች አስተዳደርና ልማት ቢሮ ሀላፊን አግኝተው ማነጋገር እንዳልቻሉ የገለጹልን ቅሬታ አቅራቢዎች በቀጣይ ሳምንት አርብ የካቲት 6 ቀን 2012 አ.ም የከተማው ከፍተኛ ባለስልጣናትና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ቅሬታ አቅራቢዎቹም ጥያቄያቸውን አቅርበው ውይይት እንደሚያደርጉ እንደተነገራቸውም ነው የሰማነው።
ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ከጋራ መኖርያ ቤቶቹ ጋር በተያያዘ የተዛነፈ መረጃ መስጠት ለምን እንደፈለጉ ግልጽ አይደለም።ስለ 20/80 ቤቶቹ መተላለፍ ብቻም ሳይሆን የልማት ተነሽ ለተባሉ አርሶ አደር ቤተሰቦች ለካሳነት የተሰጡት ቤቶች መጠንንም ከእጥፍ በላይ ቀንሰው ነው ሲገልጹ የተሰሙት። ተጠሪነቱ ለእርሳቸው የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ግብር እና የአርሶ አደር ልማት ኮሚሽን የዚህ አመት እቅዱ 23 ሺህ የጋራ መኖርያ ቤቶችን ለልማት ተነሽ ለተባሉ አባወራዎች እስከ ቤተሰቦቻቸው መስጠት መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ በጽሁፍ የተደረገፈ መረጃ አላት። 23 ሺህ ቤቶቹ መተላለፋቸውንም አረጋግጠን መዘገባችን ይታወሳል። እርሳቸው ግን በካሳነት የተሰጡ ቤቶችን ከእጥፍ በላይ አሳንሰው ሲገልጹ ነበር። የማይገባቸው በርካታ ግለሰቦች ቤቶቹን ማግኘታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው። ካሳ የተሰጣቸው አርሶ አደሮች ለቤቱ ክፍያ እንደሚፈመሙ ምክትል ከንቲባው የተናገሩት ቤቱን የተረከቡት ግለሰቦች ከሚሉት ጋር የተቃረነ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]
To contact Wazema Editors wazemaradio@gmail.com