ዋዜማ ራዲዮ- ሰኔ 16 ቀን 2010 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ለመደገፍ በተደረገው ሰልፍ ላይ የደረሰውን የቦምብ ፍንዳታ ተከትሎ በድርጊቱ ላይ እጃችው አለበት ያልቻው 5 ግለሰቦች ላይ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከስ መመስርቱ ይታወሳል።
በሽብር ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ጌቱ ግርማ፣ ብርሀኑ ጁፋር ፣ ጥላሁን ጌታቸው ፣ ባህሩ ቶላ እና ደሳለኝ ተስፋዬ ጉዳያቸውን ለመከታተል ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብር ወንጀል ችሎት ቀርበው ነበር።
የመከላከያ ምስክሮቻቸውን እና ማስረጃዎቻቸውን አቅርበው ሲከላከሉ የሰነበቱት ተከሳሾቹ ከዚህ ቀደም በሰጡት መግለጫ ላይ ማረጋገጫ እንዲሰጡ የኢፌደሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ እና ዋና ጠቅላይ አቃቤ ህግ ብርሀኑ ጽጋዬን በምስክር ዝርዝር አካተው ነበር።
የተከሳሾች ጠበቆች በዛሬው ችሎት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ቀርበው እንዲመሰክሩ ብንጠይቅም ምላሽ አላገኘንም፣ ከለውጡ በፊት ባለሰልጣናት በጽሁፍ እንኳን ምላሸ ይሰጡ ነበር አሁን ግን ይሄ እንኳን እየሆነ አይደለም ብለዋል።
አክለውም የትላልቀ ሀገራት መሪዎች እንኳን የፍርድ ቤት ጥሪ አክብረው በሚቀርቡበት ጊዜ የፖለቲካ ተሿሚዎች የፍርድ ቤት ትእዛዝ የማያከብሩ ከሆነ ፍርድ ቤቱ ራሱን ማስክበር አለበት በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
በተጨማሪም 1 አመት ክ8 ወራት ያህል በእስር መቆየታቸውን በማስታወስ ያልተፋጠነ ፍትህ እንደተነፈገ የቆጠራል ብለዋል።
ምስክሮቹ እንዲያረጋግጡ የተፈለገው የቪድዮ ማስረጃ መጀመርያ መቅርብ አለበት ያለው ችሎቱ ማስረጃውን ተመልክተን ያ በቂ ከሆነ ምስክሮቹን መጥራት ላያስፈልግ ይችላል መጠራት ካለባቸው ግን ይጠራሉ ችሎቱ ከማዘዝ የሚያስፈራው ነገር የለም ሲሉ ዳኞች ለተከሳሾች አስረድተዋል።
ማስረጃው ከኦሮሚያ ብሮድካስት እና ከብሄራዊ መረጃ ሲቅርብ ለመመርመርም ለጥር 29 ቀጠሮ ተስጥቷል።
በዚህ የሽብር ወንጀል ክስ የ2 ሰዎች ህይውት ማለፉን እና ክ163 በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አቃቤ ህግ መጥቀሱ ይታወሳል። [ዋዜማ ራዲዮ]