PM Abiy Ahmed- File

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት ለአንድ ዓመት ቸል ብሎት የቆየው የጸጥታ ችግር በቅርቡ በክልልና ፌደራል ደረጃ የ6 ሲቪልና ወታደራዊ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ እስካሁን ቁጥራቸው ያልታወቁ የአማራ ክልል ፖሊስና ልዩ ሃይል አባላትም ሞተዋል፡፡ ይህንኑ ክስተት ተከትሎም በአዲስ አበባና በክልሉ በርካቶች ለእስራት ተዳርገዋል፡፡ ከዚህ አስደንጋጭ ክስተት መንስዔው ደሞ በአማራ ክልል መፈንቅለ መንግሥት መሞከሩ እንደሆነ መንግሥት የገለጸ ሲሆን እስካሁንም በዚህ አቋሙ እንደጸና ነው፡፡
እንዲህ ያለ የከፍተኛ ባለስልጣናት ግድያ በሀገራችን ሲፈጸም በኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን የመጀመሪያ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ብዙ ጥያቄዎችን ያስነሳውና ለወደፊቱም ስጋቶችን የፈጠረው፡፡ የሀገሪቱ የፀጥታ መዋቅር የገባበትን ቅርቃር የሚመለከት ዘገባ ቻላቸው ታደሰ አዘጋጅቷል


በአማራ ክልል የተፈጸመው የባለሥልጣናት ግድያ ሦስት ነገሮችን ወደፊት አጉልቶ አውጥቷል ማለት ይቻላል፡፡ አንዱ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት ወስጀዋለሁ የሚለውን የጸጥታ ዘርፍ ተቋማዊ ማሻሻያ ወይም በእንግሊዝኛው security sector reform የሚመለከት ነው፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ በተለይ ከአማራ ክልል በጠቅላላው ከሁሉም ክልሎች ልዩ ሃይሎች ጋር የተያያዘ ሲሆን በሦስተኛ ደረጃ ደሞ ፌደራል መንግሥቱና ክልሎች በጸጥታና ፖለቲካ ረገድ ስላላቸው መስተጋብር ምን አሳየን? ከሚለው ጋር ይገናኛል፡፡


የባሕር ዳሩ ክስተት በዐለም ዐቀፉ ሜዲያ ጎልቶ እንዲወጣ ያደረገው አንዱ ነገር የብሄር ሚሊሽያ ለለውጡ እንቅፋት ሆኗል፤ ፖለቲከኞችና ብሄርተኞች የፖለቲካ ምህዳሩ መከፈቱን ተጠቅመው የብሄራቸውን ሥልጣን መሠረት በማጠናከር ለሀገረቱ ጸጥታ ስጋት ሆነዋል የሚለው ግንዛቤ ነው፡፡ እናም አጋጣሚው ቀደም ሲል በሱማሌ ክልል በተለይም በኦጋዴን ብቻ ተወስኖ የነበረው የልዩ ሃይል አደገኛነት ሀገር ዐቀፍ ችግር መሆኑ በውጭው ዐለም ግንዛቤ እንዲያዝበት አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡


መንግሥት እንዳለው የባሕር ዳሩን ቀውስ የፈጠሩት ከልዩ ሃይሉ የተወሰኑ ክፍሎች መሆናቸው ተነግሯል፡፡ ከጥቃቱ የተረፉ ሃላፊዎች እንደሰጡት ምስክርነት ከሆነ “አዲሶች” እያሉ የሚጠሯቸው የቅርብ ጊዜ ተመራቂዎች ከነባሮቹ ልዩ ሃይሎች ጋር በደንብ የተዋሃዱ አይመስልም፡፡ ዘግየት ብሎ ግን የልዩ ሃይሉ ተወካዮች በውስጣችን አዲስና ነባር የሚባል ክፍፍል የለም ብለው ሲያስተባብሉ ሰምተናል፡፡


ስለ ባላስልጣናት ጥበቃም ማንሳት ያስፈልጋል እዚህ ላይ፡፡ በደንቡ መሠረት ለክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚደረግላቸው ጥበቃ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ወጥ በሆነ ሥርዓት እና የአሰራር ደንብ ያለው ነው መሆን ያለበት፡፡ ላለፉት ጥቂት ዐመታት ደሞ ለክልል መስተዳድሮች ጥበቃ የሚሰጡት የክልል ልዩ ሃይሎች ናቸው፡፡

ክልሎች ደሞ ልዩ ሃይላቸውን ያዋቀሩት እንደየራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ በየራሳቸው መንገድ እንጅ በፌደራል ፖሊስ ወይም ደኅንነት መስፈርት መሠረት ስላልሆነ ለክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ጥበቃ ፌደራል መንግሥቱ ያወጣው ወጥ የሆነ የጥበቃ ሥርዓት የለም ማለት ነው፡፡ ከግድያ የተረፉት የክልሉ ሃላፊዎችም እንዲህ ያለ ችግር እንደሚደርስብን ጨርሶ ፍንጭ አልነበረንም ማለታቸው ይህንኑ ክፍተት የሚያረጋግጥ ነው፡፡


የአማራ ክልል ልዩ ሃይል አባላት ከሰሞኑ ንግግራቸው “ለውጡን ለማስቀጠል ቁርጠኛ ነን” የሚል አረፍተ ነገር ደጋመው መጠቀማቸው ከጸጥታ ጉዳዮች አልፈው ምን ያህል ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንደተጋቡባቸው የሚጠቁም ይመስለናል፡፡ ይሄ ደሞ ላንድ ጸጥታ ዘርፍ አደገኛ ምልክት ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ችግር ምንጭ በብሄርተኝነቶችና ድርጅታዊ ቅራኔዎች መጦዝ ሳቢያ አንድም ፖለቲከኞች የብሄር ፖለቲካን ወደ ጸጥታው ዘርፍ እንዲያጋቡ፣ አሊያም የጸጥታው ዘርፍ ሃላፊዎች በሲቪሉ ፖለቲከኞች ላይ ያልተገባ የፖለቲካ ተጽዕኖ እንዲፈጥሩ የሚያስችል ሁኔታ ማገንገኑ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ፌደራል መንግሥቱ በመከላከያ ሠራዊቱ፣ ክልሎችም በልዩ ሃይላቸው ብቻ የሚተማመኑበት ሁኔታም ይታያል፡፡ ይሄ ደሞ ነገ ተነገ ወዲያ ከዚህም የከፋ ውጤት እንደሚያስከትል ለመናገር ነብይ መሆን አይጠይቅም፡፡


መቸም የክልል ልዩ ሃይል ለፌደራል መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን ያንዱ ልዩ ሃይል ለሌላው ክልለ ስጋት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩም አዲስ አበባ ላይ ያልተናገሩትን በቅርቡ ደሴ ሂደው ክልሎች ለሚሊሽያና ልዩ ሃይል የሚወጡትን ወጭ ጠቅሰው ማማረራቸው ልዩ ሃይሉን መንግሥታቸው እንደ ስጋት እንዳየው ግልጽ ፍንጭ የሰጠ ነበር፡፡

ከአራቱ ትላልቅ ክልሎች ኦሮሚያ ብቻ ልዩ ፖሊስ የለኝም ስለሚል በሌሎች ክልሎች ላይ ከተነጣጠረው የብሄር ሚሊሽያ ምልመላ ትችት በተወሰነ ደረጃ ተርፏል ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም የኦነግ የቀድሞ ታጣቂዎችን ጭምር እያሰለጠነ መደበኛ ፖሊሱን ማጠናከሩ ግን ለአጎራባች ክልሎች ስጋት መፍጠሩ አልቀረም፡፡


ገና ከጅምሩ ለኦሮሚያና አማራ ክልል ጸጥታ ተቋማትና ልዩ ሃይሎች የቀድሞ ወታደራዊ መኮንኖች መሾማቸው፣ “ጸጥታ ሃይሎች ወታደራዊ ባሕሪና ቅርጽ እንዲይዙ ያደርጋል” በማለት ዋዜማ ራዲዮ ስጋቷን ገልጻለች፡፡ ልዩ ሃይሎችም በጊዜ እንዲፈርሱም ላለፉት 3 ዐመታት አሳስባለች፡፡ ልዩ ሃይሎች ከሚገቡባቸው የግጭት መስኮች መካከልም ከክልል ፖሊስ ጋር ወይም ርስበርሳቸው እንደሚሆን ጭምር ስትጠቁም የቆየች ሲሆን እስካሁን ባለው መረጃ ከሰሞኑ የታየውም ይኼው ነው፡፡


የባሕር ዳሩ ክስተትና ባጠቃላይ የክልል ልዩ ሃይሎች ነገር የሚያስነሳው አንዱ መሠረታዊ ጉዳይ የጸጥታ መዋቅር ማሻሻያ አስፈላጊነት ነው፡፡ ችግሩ እስካሁን የዐቢይ መንግሥት ላይ ላዩን እንጅ ወደ ክልል ደረጃ የሚዘልቅ ተቋማዊ የጸጥታ ማሻሻያ ሥራ አልሞከረም፡፡

በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ ተደርጓል ከሚባለው ሰፊ ተቋማዊ ማሻሻያ በስተቀር እንደ ደኅንነትና ፖሊስ ባሉት ጸጥታ ተቋማት ረገድ ሃላፊዎችን ከመቀየር ያለፈ፣ የረባ ተቋማዊ ማሻሻያ ተደርጓል ማለት አይቻልም፡፡

የክልል ልዩ ሃይሎች ከሌሎች ጸጥታ ተቋማት ጋር ያላቸው መስተጋብር እንደ ድሮው በተደበላለቀ ሁኔታ መቀጠሉ የሚያሳየንም ይህንኑ ነው፡፡ ላይ ላዩን የተደረገው የጸጥታ አመራር ሽግሽግም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ሙሉ ስምምነት ስለሌለው ይመስላል ፖለቲካዊ ጦስ ሲያመጣ እያየን ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በደኅንቱ የተደረጉ ቅነሳዎችንና ሽግሽጎችን ሕወሃት እነደ ብሄር መድልዖ ወስዷቸዋል፡፡ የፌደራልና አዲስ አበባ ጸጥታ ተቋማትን ሃላፊዎች ባጭር ጊዜ መቀያየራቸውም ተቋሞቹን አዳክሟቸዋል የሚል እምነት ያላቸው ወገኖች አሉ፡፡


ለክልሎች ሕገ መንግሥቱ የፈቀደላቸው ፖሊስና ሚሊሽያ ብቻ ቢሆንም መንግሥት ግን ልዩ ሃይሎችን የሚመለከት አንዳችም ተቋማዊና ሕጋዊ መፍትሄ ማስተዋወቅ አልቻለም፡፡ በተቋማዊ የጸጥታ ማሻሻያ ሰበብ ልዩ ሃይሎችን ለማፍረስ ቢፈለግስ ብሄርተኝነትም እየጎለበተና በገዥው ግንባር አባል ድርጅቶች መተማመናቸው በተሸረሸረበት ሁኔታ ከእንግዲህ ክልሎች ፍቃደኛ ይሆናሉ ወይ? የሚለውም አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ቢያንስ ሕወሃት የመገንጠል ትርክትን ወደፊት ከማምጣቱ አንጻር ሲታይ ልዩ ሃይሉን በትኖ በፖሊስ ብቻ ጸጥታውን የማስጠበቁ ነገር የሚታሰብ አይመስልም፡፡


እዚህ ላይ ሌላው ማንሳት ያለብን ተዛማጅ ነጥብ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በቀውሱ ላይ ብሄራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱን አለመሰብሰባቸው ነው፡፡ ምልባት በይፋ ሳይናገር ምክር ቤቱ ተሰብስቦ ከሆነም ያወጣው መግለጫ የለም፡፡ ይህም ጠቅላይ ሚንስትሩ የጸጥታ ተቋማዊ ሥራዎችን ወደ ጎን እየገፉ እንደሆነ ሊጠቁም ይችላል፡፡ ችግሩን ወደፊት ገለልተኛ ወይም ከፌደራልና ከክልሉ የተውጣጣ አጣሪ ቡድን ያጣራው እንደሆነም ጠቅላይ ሚንስትሩ እስካሁን የገቡት ቃል የለም፡፡


ክስተቱ ስለ ፌደራልና ክልል መስተጋብር ምን ይነግረናል? 

ፌደራል መንግሥቱ የክልሉን ልዩ ሃይል ባያፈርሰው እንኳ አወቃቀሩን እንደገና በመፈተሸና የሃይል ብዛቱን በመቀነስ ያዳክመው ይሆን? የሚሉ ስጋት ይነሳሉ፡፡ ስጋቱ የሚነሳው አጎራባች ክልሎች ልዩ ሃይላቸውን፣ ሚሊሻቸውንና ፖሊሳቸውን እያጠናከሩ ባሉበት ሁኔታ ልዩ ሃይሉን ማፍረስ ይቅርና እንደ ሱማሌ ክልል ልዩ ሃይል ማዳከም ሞራላዊ፣ ፖለቲካዊና ሕጋዊ አመክንዮ ሊኖረው ስለማይችል ነው፡፡ በርግጥም የልዩ ሃይል መዳከም ክልሉን ለሌላ ጸጥታ ችግር ሊያጋልጠው ይችላል፡፡ 

በቅርቡ በከሚሴና ሰሜን ሸዋ በተፈጸሙ ጥቃቶች የኦነግ እጅ እንዳለበት አንዳንድ የክልሉ ሃላፊዎች መናገራቸው እና ኦነግ ወሎ የኦሮሞ ግዛት ግዛቴ ነው ዐይነት ትርክት በሚያሰማበት ሁኔታ የፖለቲካ መፍትሄ እስኪገኝ ድረስ ክልሉ ለውጫዊ ጸጥታ ችግር ተጋላጭ እንደሚያደርገው ግልጽ ነው፡፡ አክራሪ ብሄርተኞች እንደሆኑ የብሄር ቅራኔንና ግጭትን ተቋማዊ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ክልሉ ግዙፍ እንደመሆኑ የጸጥታ ችግሮቹ ሀገር ዐቀፍ ትርምስ እንዳያስከትል መጠንቀቅ ተገቢ ነው ፡፡
የክልሉን ጸጥታ ሃይል ላይ ጅምላ ተቋማዊ ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ማን ምን ሚና ነበረው? የሚለውን በገለልተኛ ምርመራ ማስመርመር ሌላኛው ትክክለኛ ርምጃ ይሆናል፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ በክልሉ የሚቆይበትን ጊዜ የክልሉ መንግሥት ከሚፈቅደው ውጭ እንዳይሆን ማረጋገጥና ከክልሉ ዕውቅናና ይሁንታ ውጭ የትኛውንም ጸጥታ ርምጃ አለመውሰድም ሌላ አወንታዊ ርምጃ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡


የክልሉ ክስተት ባንድ በኩል በፌደራሉና የአማራ ክልል መንግሥት መካከል ያልተስተካከለ የጸጥታ መስተጋብር ብሎም የጸጥታ መረጃ ፍሰት መፋለስ መኖሩን አሳይቶ አልፏል፡፡ በሌላ በኩል የፌደራሉ ጸጥታ ሃይል ወደ ክልሉ የገባበት መንገድ ጥያቄ የሚያስነሳ ይመስለናል፡፡ ምናልባት የፌደራሉ ጸጥታ ሃይል በክልሉ ለተራዘመ ጊዜ ከቆየ ወይም ከክልሉ መንግሥት ፍላጎት ውጭ ሌሎች ትርፍ ርምጃዎችን ከወሰደ ግን ይሄ ጉዳይ እንደገና መነጋገሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ከሰሞኑ ቀውስ ጋር በተያያዘ ዐለም ዐቀፉ የግጭት አጥኝ ድርጅት ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጦር ሠራዊቱን ለፖለቲካ ማስፈጸሚያ ከማድረግ እንዲቆጠቡ የመከረው አዝማሚያዎች ስላልጣሙት እንደሆነ ይታወቃል፡፡


ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፌደራል ጸጥታ ሃይሎች ምላሽ ምን ያህል የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ያከበረና ተመጣጣኝ ነበር? ከክልሉ ጸጥታ ሃይል ጋር ያላቸው መስተጋራቸውስ ሕጉን የተከተለ ነው ወይ? በትክክልስ የፌደረራሉ ጸጥታ ሃይል ምን ሚና ተጫወተ? የሚሉትን ጥያቄዎች መነሳት ያለባቸው ናቸው፡፡ ችግሩ ግን መንግሥት በዚህ ላይ ግልጽ መረጃ አልሰጠም፡፡ ቀሪው ልዩ ሃይል ከክልሉ ፖሊስና ከፌደራሉ ጸጥታ ሃይል ጋር ምን ያህል ተባብሮ እየሰራ እንደሆነም የጠራ መረጃ የለም፡፡

በርካታ የክልሉ ጸጥታ አባላት የሞቱት ከየትኞች ጸጥታ ሃይሎች ጋር በተደረገ ተኩስ ልውውጥ እንደሆነም ገና አልታወቀም ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ደሞ በልዩ ሃይሉ ዕጣ ፋንታ ላይ የራሳቸው አንድምታ ይኖራቸዋል፡፡የክልሉ ሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኮሎኔል አለበል አማረ እና የልዩ ሃይሉ ዋና አዛዥ ጀኔራል ተፈራ ማሞም አንድ ጊዜ ብቻ አጫጭር ቃለ ምልልሶችን ካደረጉ በኋላ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ለእስር ስለተዳረጉ ስለ ክስተቱ የተሟላ መረጃ መስጠት ሳይችሉ ነው የቀሩት፡፡


ባጠቃላይ ክስተቱም ሆነ ከዚያ ቀጥሎ የመጣው የፌደራሉ ጸጥታ ሃይል ጣልቃ ገብነት ለክልሉ አንድምታቸው ዘርፈ ብዙ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በጸጥታ፣ መንግሥታዊና ድርጅታዊ ፖለቲካ እንዲሁም አስተዳደራዊ መዋቅርም ላይ አሉታዊ አሻራ ጥለው ማለፍ የሚችሉ ናቸው፡፡ በጸጥታ ሃይሉ ስነ ልቦና ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳር ይችላሉ፡፡ በክልሉ ውስጣዊ ጸጥታ ላይ ብቻ ሳይሆን ክልሉ ወደፊት ከፌደራል መንግስቱ ወይም ከአጎራባቾቹ ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች ጋር በሚኖረው የጸጥታ መስተጋብር ላይ አሉታዊ አሻራው መፍጠሩም የሚቀር አይመስልም፡፡ በሀገሪቱ ቁልፍ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ያሰናዳነውን የድምፅ ዘገባ ከታች ያድምጡ

https://youtu.be/2V47mYkt-o4