ዋዜማ ራዲዮ – ስኔ 15/2011 ዓ.ም መንግስት “መፈንቅለ መንግስት” ሲል የጠራው የአማራ ክልል ባለስልጣናት ግድያ በሰፊ መዋቅር የተደራጀ እንደነበርና በአዲስ አበባም ወታደራዊ ተቋማትና ባለስጣናት ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ዋዜማ ሬዲዮ ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አምባቸው መኮንንን (ዶ/ር) ጨምሮ ሁለት የክልሉ ባለስልጣናት በባህርዳር በቢሯቸው እንዳሉ በታጣቂዎች ከተገደሉ ከሶስት ስዓት በኋላ በአዲስ አበባ በመኖሪያ ቤታቸው ከጡረተኛ ወታደራዊ ጓዳቸው ጋር የነበሩት የመከላከያ ሰራዊቱ አዛዥ ሰዓረ መኮንን በጠባቂያቸው መገደላቸውን መንግስት አስታውቋል።
ከተለያዩ ምንጮች ያሰባሰብነው መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ ጥቃቱ በሌሎች የሁለት ክልል መሪዎች ላይ ጭምር ያነጣጠረ ውጥን ነበረው። ዒላማ ከተደረጉት የክልል መሪዎች አንዱ አዲስ አበባ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አልነበሩም።
በተጨማሪ ጦር ሀይሎች አካባቢ በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የሬድዮ ግንኙነት ዋና ማዕከል ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ለመፈፀም የተንቀሳቀሰው ሀይል በመንግስት ሀይሎች በቁጥጥር ስር ውሏል።
ምርመራው ያልተጠናቀቀ በመሆኑና ከጉዳዩ ስሱነት አንፃር መንግስት ለህዝቡ የተሟላ መረጃ ለመስጠት ጊዜ ያስፈልገዋል ያሉት የመረጃ ምንጫችን፣ የጥቃቱ ዓላማ የጠቅላይ ሚንስትር ዓቢይ አህመድን መንግስት ለመገልበጥ ያነጣጠረ ስለመሆኑ በድፍረት ይናገራሉ።
መንግስት ግን ጥቃቱ በክልል ደረጃ የክልል መንግስትን ለመጣል ያለመ እንደነበር ከጥቃቱ ዕለት ጀምሮ ሲያስረዳ ቆይቷል።
በባህርዳር የተካሄደው ግድያ በሀገሪቱ ከታቀዱ በርካታ ጥቃቶች አንዱ እንደነበርና ሌሎቹ ጥቃቶች በውል ባልታወቀ ምክንያት መክሸፋቸውን የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች መኖራቸውንም ምንጫችን ይናገራሉ።
በእስካሁኑ ሂደት በህቡዕ ተደራጅተዋል የተባሉ ወታደራዊና ሲቪል ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል። በመካከለኛ ማዕረግ የሚገኙ የሰራዊቱ አባላትና የተለያዩ የክልል የፀጥታ ሀላፊዎችም ከታሰሩት መካከል ናቸው።
ብሄራዊ ደህንነትና መረጃ አገልግሎት በተለይ በአማራ ክልል ስለነበረው ፀረ-መንግስት እንቅስቃሴ ያሰባሰበው ሰፊ መረጃ እንደነበርና የተወሰነውንም ለጠቅላይ ሚንስትሩ ማቅረቡንም ሰምተናል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ችግሩን በፖለቲካዊ መንገድ መፍታት ስለሚሻል በሚል ነገሩን ብዙም ሳይገፉበት እንደቀሩም እየተነገረ ነው።
ሰኔ 15 በተፈጠረው ግድያና ቀውስ ዙሪያ ንክኪ ሳይኖራቸው አይቀርም ተብለው
መንግስት ከጥቃቶቹ ጀርባ በአደራጅነት እጃቸው አለበት ሲል የሚከሳቸው ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ የአማራ ክልልን የፀጥታ መዋቅርና ቀድሞ በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ የነበራቸውን ትስስር ተጠቅመው ህቡዕ መዋቅር ዘርግተው ነበር ብለው የሚያምኑት መርማሪዎች ትኩረታቸውን በአማራ ክልል የፀጥታ ዘርፍ ሀላፊዎች ላይ አድርገዋል።
ሀገራዊ ህልውናን የሚፈታተነውን ይህን ክስተት በተመለከተ መንግስት የጠራና ከአንድ ማዕከል የተጠናቀረ፣ ወጥነት ያለው መረጃ ማቅረብ ተስኖት የታየ ሲሆን በድርጊቱ ዙሪያ እማኞችና የተለያዩ ተቋማት የሚያቀርቧቸው አስተያየቶች ሀገራዊ መደናገርን አስከትለዋል።
የአዘጋጁ ማስታወሻ– ስለጉዳዩ መረጃ በምናሰባስብበት ወቅት በርካታ ግርድፍ መረጃዎችን አግኝተናል። አንዳንዶቹን ወቅቱ ስለማይፈቅድ፣ የተወሰኑትን መረጃዎች በህይወት የሌሉና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ተጠቃሾች በመኖራቸው በዝርዝር አላቀረብናቸውም። በሌላ ዘገባ የምንመለስባቸው ይኖራሉ።