ለ2012 ዓ.ም ምርጫ ማፈጸሚያ 3.7 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙ ታውቋል፡፡ ይህ የበጀት መጠን ከዚህ ቀደም በተደረገው የምርጫ በጀት በስምንት ዕጥፍ ከፍ ያለ ነው። በውይይቱ የተሳተፈው የዋዜማ ሪፖርተር እንደዘገበው

Birtukan Midekssa-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ወቅት መገናኛ ብዙሃን ሊኖራቸው የሚገባውን ሚና በተመለከተ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ “ሚደያ እና ምርጫ፤ ከባለፈው ተሞክሮ እና ልምድ ሊወሰድ ስለሚገባው ትምህርት” እና “የዲጂታል ሚዲያ ዕድሎች እና ተግዳሮቶች” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጓል፡፡


የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ምርጫ ቦርዱ በአዲስ መልክ ከተዋቀረ ከታሕሳስ 2011 ጀምሮ እየሰራ ያለውን ስራዎች ባስረዱበት ጋዜያዊ መግለጫ “መገናኛ ብዙሃን የምርጫ ቦርድን ያክል ገለልተኝነት ይጠበቀባቸዋል” ብለዋል፡፡

“የ2012 ምርጫ በተያዘለት እቅድ መሰረት ይከናወናልወይ?” የሚል እና “የሲዳማ ዞንን የክልልነት ጥያቄዎችን ምርጫ ቦርዱ እንዴት እያተናገዳቸው ነው?” በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያዎች ላይ መልስ የሰጡት ወ/ሪት ብርቱካን በአሁን ወቅት የምርጫ ቦርድ አባላት ጥቆማ እየተከናወነ በመሆ ቦርዱ በሙሉ ሀይሉ ስራ ለመስራት አለመቻሉን ጠቅሰው የ2012 ምርጫን በተመለከተ “በህገ መንግስቱ መሰረት በተያዘለት እቅድ እንደሚከናወን አድርገን እየሰራን ነው፤ የቦርድ አባላት ሲሟሉ በአገሪቱ ያሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ምርጫ ለማሄድ የሚያሥችሉ ናቸው ወይ የሚለው የሚወሰን ይሆናል” ብለዋል፡፡

የሲዳማ ዞንን የክልልነት ጥያቄ በተመለከተ ጉዳዩ መነሳት ከጀመረ የቆየ መሆኑን ጠቅሰው በህገ መንግስቱ መሰረት ህዝበ ወሳኔ ለማደረግ ቦርዱ መሟላት እንዳለበት ገልጸዋል ፡፡


የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ኮምኒኬሽን አማካሪ ወ/ሪት ሶልያና ሽመልስ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ሊኖረው ስለሚገባ የአሰራር ማብራሪያ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፤ ቦርዱ የሚጠቀምባቸውን ትክክለኛ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በተመለከተ እንዲሁም ዜና፣ ቃለ መጠይቅ ፣ የምርጫ ሪፖርቶችን እና ጋዜጣዊ መግለጫዎችን በተመለከተ ምርጫ ቦርዱ ከመገናኛ ብዙሀን ጋ ሊኖረው ስለሚገባ ግንኙነት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡


ለ2012 ምርጫ ከዚህ በፊት ከተደረጉ ምርጫዎች በእጅጉ በላቀ ሁኔታ ከፍተኛ ገንዘብ የተበጀተ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በአጠቀላይ ለምርጫ ሂደቱ 3.7 ቢሊዮን ብር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ጥያቄ የቀረበ መሆኑን የገለጹት ወ/ሪት ሶልያና ከተያዘው በጀት ውስጥ 900,000,000 (ዘጠኝ መቶ ሚሊየን ብር) ግምት ያለው እገዛ ከአለም አቀፍ አጋር አገራት ለማሰባሰብ የታቀደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ መጠን ከዚህ ቀደም ከተከናወኑ ምርጫዎች በጀቱ ከፍተኛ ልዩነት ያሳየበት ምክንያት፤ በአንድ ምርጫ ጣቢያ ይደረግ የነበረውን አንድ ኮረጆ ወደ ሁለት ለማሳደግ፣ ቀድሞ የነበሩትን የሸራ ኮረጆዎች በግልጽ በሚያሳዩ ሳጥኖች ለመቀየር ፣ እያንዳንዱ የድምጽ መስጫ ወረቀት የደህንነት መለያ ቁጥር እና የተወዳዳሪ ምስልን የያዘ ሆኖ እንዲሰራ መታቀዱ ፣ የመራጮች ቁጥር 53.9 ሚሊዮን እንደሚደርስ ሲገመት ከዚህም መካከል 45.3 ሚሊየን መራጮች እንደሚሳተፉ ፣ በአጠቃላይ በአገሪቱ 41,600 ምርጫ ጣቢያዎችን ለድረግ መታሰቡ ተገልጽዋል፡፡ በእነዚህ በተጠቀሱት እና በሌሎችም በርካታ ምክንያቶች የ2012 ምርጫ የተያዘው በጀት ከመቼውም በላይ ከፍ ማለቱ ተገልጽዋል፡፡