PM Abiy Ahmed-FILE

 ዋዜማ ራዲዮ- መንግስት ከሀገር ቤት ተዘርፎ በውጪ ሀገራት ባንኮች ተደብቋል ያለውን ገንዘብ ለማስመለስ ከየሀገራቱ ጋር ንግግር መጀመሩን ካስታወቀ አንድ አመት ሊሆነው ነው። ይሁንና እስካሁን የመንግስት ጥረት ተሳክቶ ገንዘቡን ማስመለስ አለመቻሉን ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ለመረዳት ችላለች። 

አብይ አህመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የመጡ ሰሞን በባለሀብቶች ከኢትዮጵያ ተዘርፎ በተለያዩ ሀገራት ባንኮች የተቀመጠ ገንዘብን እንደሚያስመልሱ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተሰምተው ነበር። የመጀመርያ ካቢኒያቸውን ካወቀሩ በሁዋላ ለካቢኔ አባሎቻቸው ስልጠና ሲሰጡ ከኢትዮጵያ የተዘረፈ ገንዘብን ለማስመለስ የየሀገራት መሪዎች ሳይቀር መተባበር መጀመራቸውን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል። ይሁንና እስካሁን የመንግስት ጥረት ተሳክቶ ገንዘቡን ማስመለስ አለመቻሉን ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ለመረዳት ችላለች። መንግስትም በዚህ ላይ የሰጠው መግለጫ የለም።

     ዋዜማ ራዲዮ ከታማኝ ምንጮች ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ከኢትዮጵያ በወንጀል ተገኝተው በሌሎች ሀገራት ባንኮች የተቀመጠ ገንዘብን አስመልሳለሁ በሚል የተከተለው ስልት ውጤቱን ስኬታማ እንዳይሆን አድርጎታል።

ምናልባትም መንግስት እንዲህ አይነት ስራዎች በሚስጥር መካሄድ ሲኖርባቸው በተደጋጋሚ በግልጽ መናገሩ የእርምጃው ሰለባ እንሆናለን ብለው የሚያስቡ ግለሰቦች ይበልጥ እንዲጠነቀቁ አድርጓቸዋል።

ከምንጮቻችን እንደተረዳነው በውጭ ሀገራት ባንኮች የተቀመጡ በኢትዮጵያ በወንጀል ውጤት ወጥቷል የተባለ ገንዘብን ለማስመለስ ሚኒስትሮች ሳይቀር ከሀገራት መሪዎች ጋር ለመወያየት ጉዞ አድርገው ነበር።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ወርቅነህ ገበየሁ እና ጠቅላይ አቃቤ ህግ ብርሀኑ ጸጋዬ ከወራት በፊት ወደተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሄዱት ላይ ላዩን ለሌላ ጉዳይ ይምሰል እንጂ የሄዱበት ዋና ምክንያት ይሄው ከሀብት ማስመለስ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ተረድተናል።

በቻይናም ተመሳሳይ ጥረቶች ተደርገዋል። ቻይና እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሀብትን በተለያየ ሁኔታ ለማሸሽ ምቹ ናቸው ተብሎ ስለታሰበ ነው የጥረቱ ኢላማ የሆኑት። 

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የቀድሞ ሀላፊዎች ከታሰሩበት የሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘም የሚነሳ አለ።ሜቴክ ፈጸመ የተባለው ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ ግዥ ለመንግስት አስደንጋጭ እንደነበር የሚታወስ ነው።በተለይ ኮርፖሬሽኑ ግዥ የፈጸመው ቻይና እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ካሉ ብዙ ተመሳሳይነት ካላቸው ኩባንያዎች በመሆኑ ; መኪናን ጨምሮ በርካታ የማሽነሪ ግዥ የተፈጸመባቸው ኩባንያና የሜቴክ ግንኙነት ምንድነው ?የሚል ጥያቄ አስነስቶ ነበር።

     ሜቴክ ግዥ ሲፈጽምባቸው የነበሩ የውጭ ኩባንያዎች ውስጥ ድርሻ ኖሮት የጥቅም ተጋሪም ነበር የሚል ጥርጣሬም አለ። ሆኖም ኩባንያዎቹ ጋር ሲኬድ ከፊት የሚመጡት የውጭ ዜጎች በመሆናቸው ; ማን ከጀርባቸው አለ የሚለው የሚለውን ለማወቅ አስቸግሯል። 

እንዲሁም ሜቴክ የመኪና ግዥ ከሚፈጽምባቸው ኩባንያዎች “ሽሪም” የተሰኘው አንዱ ኩባንያ ህጋዊ ሰውነት የሌለው ሆኖ ተገኝቷል።እኚህ ነገሮች ሜቴክ ግዥ የሚፈጽምባቸው ኩባንያዎች ላይ የባለቤትነት ሳይቀር ድርሻ ሊኖረው እንደሚችል ጥርጣሬን ያጫረ ነበር።ነገር ግን መንግስት ባላለቀ ምርመራ ላይ የቴሌቭዥን ዶክመንተሪ ሰርቶ እንዲተላፍ ማድረጉ ብዙ የጥቅም ተጋሪዎች እንዲሸሸጉ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለውናል ምንጮቻችን። የተኬደበት መንገድ ለመንግስት ፖሊቲካዊ ትርፍን ያስገኘለት ቢሆንም ሀብትን ሚስጥራዊ በሆነ ምርመራ እንዳያስመልስ አድርጎታል።

     በሌላ በኩል መንግስት የከፍተኛ ሙስና ምርመራዎችን ሲያደርግ የተለያዩ  ኢ-መደበኛ ስልቶችን ከመጠቀም ይልቅ መደበኛ አካሄዶችን ለመጠቀም መፈለጉም ውጤታማ አላደረገውም።በተለይ የሀብት ማሸሽ ወንጀሎች በረቀቀና ተጠርጣሪዎች እየተመረመሩ መሆኑን ሳያውቁ ቢሆን ቢደረግ ውጤታማ የመሆን ዕድሉን ያሰፋዋል። 

     ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን የውጭ ሀገራት የተለያዩ ተቋማት ባለሙያ በማሳተፍ  መንግስትን  እያገዙት መሆኑን ማወቅ ችለናል። [የዋዜማን ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]  

https://youtu.be/AYfRu0Erfsk