የአውሮፕላኑ አደጋ መንስዔ ምርመራ ሲጠናቀቅ የሚቀርቡ ተያያዥ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች እንደሚኖሩና በተጎጂ ቤተሰቦችም ሆነ በአየር መንገዱ በኩል በውጪ ሀገር ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው። ዓለማቀፍ ጠበቆች ጉዳዩን ይዘው እየተከታተሉት መሆኑ ይታወቃል።
ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦይንግ ማክስ 8 አውሮፕላን መከስከስ ሳብያ ለሚመጣበት የካሳ ተጠያቂነት የሚውል 30 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በኢትዮጵያ መድን ድርጅት በኩል ተዘጋጀለት።
ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦይንግ 737 max 8 አውሮፕላን መከስከስ ምክንያት ለሚመጡበት ተጠያቂነቶች ወይንም liablities ክፍያ የሚሆን የመድን ዋስትና በገባበት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በኩል 30 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተዘጋጅቶለታል።
ሌሎች ተያያዥ የኢንሹራንስ ክፍያ ጉዳዮች ገና እየተጠናቀሩ ሲሆን በውጪ ድርጅቶች በኩል የሚከናወን ነው።
የዋዜማ ምንጮች እንደነገሩን ከሆነ በኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለአየር መንገዱ የተዘጋጀው 30 ሚሊየን ዶላር አየር መንገዱ ማክስ 8 በመከስከሱና ህይወት በመጥፋቱ ለሟች ቤተሰቦች ለሚከፈል ካሳ እንዲሁም ለተጓዦች ንብረት የሚከፈል ካሳ እና ለተያያዥ ጥያቄዎች ክፍያ የሚውል ነው።
አየር መንገዱ ለእነዚህ ጥያቄዎች ተገቢነትን እያረጋገጠ የሚፈጽመውን የካሳ ክፍያም ዊሊፍ በተባለ የኢንሹራን አማካሪ በኩል የሚፈፀም ይሆናል።
ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ካሳውን የሚከፍለው ደንበኛው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ይሁን እንጂ በካሳ ክፍያ ውስጥ በርካታ የጠለፋ መድን ሰጭ ወይንም ሪ ኢንሹራንስ (Re-Insurance) ኩባንያዎች ተሳትፈዋል።ከተሳተፉት የጠለፋ መድን ሰጭ ኩባንያዎች መካከል ብቸኛው የኢትዮጵያ ኩባንያ ኢትዮ ሪ እንዲሁም የአውሮፓ ሪ ኢንሹራንስ (Re-Insurance) ኩባንያዎች ተሳትፈዋል። የጠለፋ ኢንሹራንሶች መደበኛ የመድን ኩባንያዎች ከፍተኛ የካሳ ጥያቄ ሲኖርባቸው በሚኖራቸው የስራ ትስስር ካሳ የሚጋሯቸው ናቸው።
አሁን ለአየር መንገዱ የተዘጋጀው የ30 ሚሊየን ዶላር ካሳ ከቦይንግ 737 max 8 መከስከስ ጋር ለሚመጣበት የካሳ ተጠያቂነት እንጂ ለራሱ ለአውሮፕላኑ የሚከፈል እንዳልሆነም ሰምተናል። ዋዜማ ከምንጮቿ እንደተረዳችው ከሆነ የራሱ የአውሮፕላኑ የመድን ሽፋን 54 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ነው። ሆኖም የአውሮፕላኑ የካሳ ጉዳይ በሂደት ላይ ያለ ሲሆን ፣ ይህም የአደጋው ቅድመ ምርመራ ውጤት በቅርቡ ይፋ የተደረገ በመሆኑና ቀጣይ ስራዎች ስላሉ ነው ተብሏል።
የአውሮፕላኑ አደጋ መንስዔ ምርመራ ሲጠናቀቅ የሚቀርቡ ተያያዥ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች እንደሚኖሩና በተጎጂ ቤተሰቦችም ሆነ በአየር መንገዱ በኩል በውጪ ሀገር ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው። ዓለማቀፍ ጠበቆች ጉዳዩን ይዘው በአሜሪካን ሀገር እየተከታተሉት መሆኑ ይታወቃል።
ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው የበረራ ቁጥር ET302 ፣ ቦይንግ 737 max 8 አውሮፕላን ፣ እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2011 አ.ም ከቦሌ አለማቀፍ አየር ማረፍያ ወደ ናይሮቢ ጆሞ ኬንያታ አየር ማረፍያ ማምራት ጀምሮ በስድስት ደቂቃ ውስጥ ከራዳር ጠፍቶ ፣ ደብረዘይት አቅራቢያ ነበር የተከሰከሰው። በአደጋውም 149 ተጓዦች 8 የበረራ ሰራተኞች በድምሩ 157 የተለያየ ሀገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወታቸው አልፏል።
የቦይንግ ምርት የሆነው max 8 አውሮፕላን ከኢትዮጵያው አየር መንገዱ አደጋ በፊት በኢዶኔዥያም ተመሳሳይ አደጋ ደርሶበት ስለነበር የአውሮፕላኑ ሶፍትዌር ጥያቄ አስነስቶም ቆይቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ አየር መንገዶች max 8ን ከበረራ ውጭ አድርገውታል።በቅርቡ በትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ይፋ የተደረገው የቅድመ ምርመራ ውጤትም የአደጋው መንስኤ ወደ አውሮፕላኑ ሶፍትዌር እንደሚያደላ ፍንጭ የሰጠ ነገር መኖሩን ገልጸዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]