ዋዜማ ራዲዮ- የ59 አመቱ ኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ የኦፕሬሽን ክፍል ዋና ሀላፊ እና የሜ/ጀ ክንፈ ዳኘው ወንድም የሆኑት ኢሳያስ ዳኘው ዛሬ መጋቢት 25 ቀን 2011 ዓም የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለፍርድ ቤት ሰጥተዋል፡፡
አቶ ኢሳያስ በኢትዮ ቴሌኮም የNGPO ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት የዩኒቨርሲቲ ኔትዎርክ ዝርጋታ ግንባታ ፕሮጀክትን የትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄ ባልቀረበበት ሁኔታ ዜድ.ቲ.ኢ ለተባለ የቻይና ኩባንያ ያለጨረታ ሰጥተዋል በማለት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የካቲት 12-2011 ዓም ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡
ከባድ የሙስና ወንጀል በሚል ሁለት ክሶችን በውስጡ የያዘ መዝገብ የከፈተው አቃቤ ህግ ተከሳሹ ከዜድ.ቲ.ኢ ስራ አስኪያጅ እና ባለቤት ጋር በጥቅም በመመሳጠር የቴሌኮሙ የግዢ መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ የ44‚ 510‚ 971.0044 ዶላር ወይንም 768,704,469 ብር ውል እንዲያዝ አድርገዋል ማለት በክሱ አብራርቷል፡፡
በዚህም ራሳቸውን እና የዜድ.ቲ.ኢ ስራ አስኪያጅ እና ባለቤትን ለመጥቀም ስልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም በቴሌኮሙ እና በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል በማለት አቃቤ ህግ ክሱን አቅርቦ ነበር፡፡
ተከሳሹ የቀረበባቸው ክስ ላይ ያላቸውን መቃወሚያ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነስርዓት አንቀፅ 130 በሚያዘው መሰረት ጉዳያቸውን እያየ ላለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት አቅርበው ነበር፡፡
በመቃወሚያቸው ላይም አቃቤ ህግ በማስረጃ ማሰማት ሂደት ላይ የሚነሳ ነጥብ እንጂ አሁን መቅረብ ያለበት ባለመሆኑ ውድቅ ይደረግልኝ ቢልም ችሎቱ የተከሳሹን መቃወሚያ በከፊል በመቀበል አቃቤ ህግ አሻሽሎ እንዲያመጣ ትዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በችሎት ትዕዛዝ መሰረት አቃቤ ህግ ክሱን ቢያሻሽልም ተከሳሹ በጠበቆቻቸው በኩል በርካታ የመቃወሚያ ነጥቦችን በተሸሻለው ክስ ላይም አንስተው ነበር፡፡
ከዚህም አነዱ የተጠቀሰባቸውን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር አንቀፅ 32 የሚመለከት ነው፡፡ በዋና ወንጀል አድራጊነት መሳተፍ የሚለው አንቀፁ ሌሎች ተባባሪዎች እንዳሉ የሚያሳይ ከመሆኑም ባለፈ በክሱ ዝረዝር ላይ በጥቅም በመመሳጠር እያለ አቃቤ ህግ መተንተኑ አሁንም ግብረ አበር እንዳለ ያሳያል ብለዋል፡፡
በቀዳሚው መቃወሚያቸው ላይ መሰረት ተደርጎ የግብር አበር ስም ይጠቀስ ካልሆነ በልዩ ወንጀል ተካፋይ መሆን የሚለው አንቀፅ 33 እና በዋና ወንጀል አድራጊነት መሳተፍ ተብሎ የተጠቀሱባቸው አንቀፅ 32 ይቀየር ተብሎ በችሎት ትዕዛዝ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
በተሻሻለው ክስ ላይ አንቀፅ 33ን አቃቤ ህግ ቢያስወጣም በዋና ወንጀል አድራጊነት የሚለው አንቀፅ 32 ግን አልተቀየረም፡፡
እናም ቢዚህ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ተከሳሽ እና ጠበቆች በድጋሜ ቢያሰሙም ችሎቱ ዛሬ ለብይን ሲሰየም ውድቅ አድርጎታል፡፡
የክሱን ዝርዝር በሚገባ ተመልክተነዋል ያለው ችሎቱ አቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ ላይ ወንጀሉን ለማብራራት በሚገባ ጥረት ያደረገ መሆኑን ተገንዝበናል ብሏል፡፡ አክሎም አሁን ላይ የቀረቡትን መቃወሚያዎች አቋም ተይዞ ውሳኔ የሚሰጥባቸው አይደሉም ያለ ሲሆን በቀጣይ በምስክር ማሰማት እና ማስረጃ ማሳየት ሂደት ላይ የሚለይ ጉዳይ ስለመሆኑ ለተከሳሹ በመግለፅ ለሁለተኛ ጊዜ የቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ አድርጎታል፡፡
በሰነ ስርዓት ህጉ አንቀፅ 132 መሰረት መቃወሚያው ውድቅ ከተደረገ በኋላ ቀታዩ የፍርድ ቤት ሂደት የተከሰሹን የእምነት ክህደት ቃል መቀበል ነው፡፡
እናም በችሎቱ የመሀል ዳኛ በክሱ የቀረበውን ወንጀል ስለመፈፀማቸው ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ኢሳያስ የተመሰረተብኝ ክስ ምንም መሰረት የሌለው ውሸት መሆኑን ፍርድ ቤቱ በቀጣይ በሂደት እንደሚረዳልኝ አምናለው ብለዋል፡፡ የተጠቀሰውን ሁሉንም አላደረኩም ወንጀለኛም አይደለሁም በማት የእምነት ክህደት ቃላቸውን በችሎት አስመዝግበዋል፡፡
በዚህ መሰረትም አቃቤ ህግ ማስረጃውን እንዲያቀርብ እና ምስክሮቹን እንዲያሰማ የችሎቱን ፍቃድ ጠይቋል፡፡ ችሎቱም የአቃ ህግን ምስክሮች ለመስማት ለሚያዚያ 17 ቀን 2011 ዓም ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ኢሳያስ ከላይ ክስ የተመሰረተባቸውን የዩኒቨርሲቲ ኔትዎርክ ዝርጋታ ፕሮጀክት ጨምሮ ፣ ኢትዮ ቴሌኮም በሶማሌ ክልል ባደረገው የፓወር ፕላንት ፕሮጀክት እና ያለ ጨረታ የተቀጠረ የውጪ አማካሪ ድርጅትን በሚመለከት በሙስና ተጠርጥረው ከ3 ወራት በላይ ምርመራ ሲደረግባቸው እንደቆየ ይታወሳል፡፡
ክስ እስኪመሰረት ባለው ጊዜም በከፍተኛው ፍርድ ቤት እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኛ ሰሚ ችሎት በተደጋጋሚ ዋስትና ሲፈቀድላቸው እና በፖሊስ ይግባኝ ሲጠየቅባቸው ቆይቶ ነበር፡፡