በእስር ላይ የሚገኙ የማረሚያ ቤት ሀላፊዎችና በስብዓዊ መብት ጥሰት የተከሰሱ ግለሰቦች የካቲት 27/2011 በዋለው ችሎት የቀረበብን ክስ አግባብነት ይጎድለዋል፣ ለመከላከል እንዳንችል ተደርጎ ቀርቦብናል ሲሉ ዘለግ ያለ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል። የዋዜማ ሪፖርተር ጉዳዩን ተከታትሎ ያዘጋጀውን ዘገባ አንብቡት
ዋዜማ ራዲዮ- በተለያየ ወንጀል ተጠርጥረውና እና ታስረው በነበሩ ግለሰቦች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት ፈፅመዋል የተባሉ 33 የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ባለሞያዎች፣ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መርማሪዎች እና የማረሚያ ቤቶች ሀላፊዎች ታስረው በህግ ጥላ ስር እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል መርማሪ የነበሩት 10 ምርማሪዎች በፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 12ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ተመስርቶባቸዋል ፡፡
ስምንት የማረሚያ ቤት አስተዳደር የቀድሞ ሀላፊዎች ደግሞ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት የካቲት 12 ቀን 2011 ዓም የክስ መዝገብ ተከፍቶባቸው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡
በዚህ መዝገብ የተጠቃለሉት ኦፊሰር ገብረማርያም ወልዳይ፣ሱፐር ኢንተንደንት አስገለ ወልደጊዮርጊስ፣ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አሰፋ ኪዳኔ፣ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት ገብረእግዚአብሔር ገብረሀዋርያት፣ዋና ሱፐር ኢንተንደንት ተክላይ ሀይሉ ፣ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አቡ ግርማ ፣ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አዳነ ሀጎስ እና ዋና ሱፐር ኢንተንደንት ገብራት መኮንን የተባሉት ተከሳሾች የቂሊንጦ ፣የዝዋይ እና ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤቶች የቀድሞ የስራ ሀላፊዎች የነበሩ ናቸው፡፡
ነሀሴ 28 ቀን 2008 ዓም ከጠዋቱ 1 ሰዓት ላይ በፌደራል ማረሚያ ቤት የቂሊንጦ ማረፊያ ቤት ላይ ተከስቶ የነበረውን እሳት አደጋ ተከትሎ ታዲያ እሳቱን አስነስተዋል ተብለው የተጠረጠሩት እስረኞችን ወደ ሸዋሮቢት ተሀድሶ ልማት ማረሚያ ቤት በመውሰድ ከፍተኛ የሆነ ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈፀሙ መሆኑን እና ሰኔ 11 2009 በቂሊንጦ ተፈጠሮ የነበረውን ግጭት ተከትሎ ደግሞ 20 የሚሆኑ እስረኞችን ወደ ዘዋይ በመወሰድ የተለያዩ ኢ ሰብዓዊ ድርጊቶችን እንደፈፀሙባቸው የአቃቤ ህግ ክስ ገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎም ለከባድ የአካል ጉዳት እና ለህልፈተ ህይወት መንስዔ ሆነዋል በማለት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የእያንዳንዱን ተከሳሽ ወንጀል በተናጠል ዘርዝሮ በክሱ አካቶ ነበር፡፡ ክሱ በችሎት የተነበበላቸው ተከሳሾች ጊዜ ወስደው የካቲት 27 ቀን 2011 ዓም የመጀመርያ ደረጃ መቃወሚያቸውን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
1ኛ ተከሳሽ የሆኑት ኦፊሰር ገ/ማርያም በበኩላቸው ሰዎች ሁሉ በህግ ፊት እኩል ናቸው በማለት የህገመንግስቱ አንቀፅ 25 ቢደነግግም በእኔ ላይ የቀረበው ክስ ግን ይህን የሚፃረር ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም መነሻ ያደረጉት የቀረበባቸው 4 ክስ ላይ አቃቤ ህግ ከአባሪዎቻቸው ጋር በማለት ቢያስቀምጥም አባሪዎቹ በቁጥጥር ስር አለመዋላቸውን በመጥቀስ ነው፡፡ አንዱን አስሮ ሌላውን ነፃ ማድረግ አግባብ ያልሆነ እና የህገመንግስቱን አንቀፅ 25 የሚፃረር ነው ብለዋል፡፡ የአባሪዎቹ ማንነት አለመገለፁም ራስን ለመከላከል የሚከብድ ነው በማለት አቃቤ ህግ ክሱን እንዲሻሽል ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡
በተከሳሾች መቃወሚያ ላይ ሌላው የተጠቀሰው ደግሞ በክስ ዝረዝር የተካተቱት የወንጀል ድርጊቶች በፍጹም አቃቤ ህግ ከጠቀሳቸው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9/3/ የተፈፃሚነት ወሰን ላይ የሚወድቁ አለመሆናቸውን ነው፡፡
ተከሳሾቹ ቀጥለውም የወንጀል ድርጊቱ ተፈፀመ ቢባል እንኳን እንደ መንግስት ሰራተኛ የወንጀል ድርጊቱ የሚያርፈው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 423 (በህገ ወጥ መንገድ ሰውን መያዝ ወይም ማሰር) እና አንቀፅ 424 (በማይባ የአሰራር ዘዴ መጠቀም) ነው ብለዋል፡፡
የወንጀል ተግባሩ እና ወንጀል የሚያደርገው ህግ በጣም ተቀራራቢ መሆን ያለባቸው በመሆኑም ክሱ እንዲሻሻል ይታዘዝልን በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ሌላኛው የተከሳሾች መቃወሚያ ደግሞ “ተደጋግመው ወይም ተከታትለው የተደረጉ የወንጀል ድርጊቶች በአንድ የወንጀል ማድረግ ሀሳብና በአንድ ድንጋጌ ስር የሚሸፈኑ ሲሆን እንደ አንደ ወንጀል ይቆጠራሉ” የሚለውን የመንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 61ን መሰረት ያደረገ ነው፡፡
ይኸውም አቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ ላይ ስድስት የሚሆኑት በተመሳሳይ ጊዜ የተፈፅሙ እና ተመሳሳይ ድንጋጌዎች የሰፈሩባቸው በመሆኑ የተገጂዎች ስም ስለተለያየ ብቻ የተለያየ ክስ ሆኖ መቅረቡ አግባብ ያልሆነ ክስ የማብዛት ስራ ነውና በአንድ ክስ ይጠቃለልልን በማለት ችሎቱን ጠይቃዋል፡፡
ችሎቱም በቀረቡት መቃወሚያዎች ላይ አቃቤ ህግ ምላሽ እንዲሰጥበት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከ33ቱ ውስጥ በ15 ላይ የሚያደርገውን ምርመራ ገና ያልጨረሰ ሲሆን የወንጀለኛ መቅጫ የስነስርዓት ህጉን አንቀፅ 83 መሰረት በማድረግ በፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮችን በማሰማት ላይ ነው፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]