ዋዜማ ራዲዮ- ከአራት አመት በፊት መንግስት ሸቀጥ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ያቋቋመው “አለ በጅምላ” የተባለ የንግድ ተቋም ራሱ በዕዳ ተዘፍቆ በቀውስ ላይ ይገኛል። 36 መደብሮችን ለመክፈት አቅዶ እስካሁን መክፈት የቻለው 7 ብቻ ነው። ከባንክ በብድር ከወሰደው ገንዘብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ለአማካሪ ድርጅት ተከፍሏል። የዋዜማ ሪፖርተር ድርጅቱ እንደምን ወደ ውድቀት ሊያመራ ቻለ? የሚለውን አብይ ሀሳብ ተመልክቶታል
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ግንቦት 18 ቀን 2006 የኢትዮጵያ ንግድ ድርጅት በሚል ተቋም ስር “አለ በጅምላ” የሚል ስያሜን የያዘ የሸቀጥ ምርቶችን በጅምላ የሚያከፋፍል መንግስታዊ የጅምላ ንግድ ሱቅን መገናኛ በተሰራው የመጀመርያ መደብር ውስጥ በዝናብ ተገኝተው ሲያስመርቁ ” ይህ አለ በጅምላ የተባለ ስሙም ደስ የሚል በግንቦት 20 ዋዜማ የተሰጠን ስጦታ” የሚል ንግግር አድርገው ነበር። ባለፈው አመት ደግሞ የሸቀጦች የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከፓርላማ አባላት ጥያቄ ቀርቦላቸው “የሸቀጦችን ዋጋ ለመቆጣጠር እንደ አለ በጅምላ አይነት ተቋምን እንጠቀማለን” ሲሉ የፓርላማው አባላት ገሚሶቹ ሲስቁ ቀሪዎቹ ደግሞ ሲያጉረመርሙ በቴሌቪዥን በቀጥታ ስርጭት መርሀ ግብር ታዝበናል።
“አለ በጅምላ” ን መንግስት ያቋቋመው በሀገሪቱ የጅምላ ንግድ ገበያ ውስጥ እስከ 30 በመቶ ድርሻ በመያዝ የሸቀጦች የዋጋ ትመና በግለሰብ ነጋዴዎች እጅ ላይ ወድቆ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በሚል ነው። ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚያገዛቸውን ምርቶች ለቸርቻሪዎች እየሸጠ ቸርቻሪዎች ደግሞ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሸጡ ማድረግም አላማ ነበረው። በወቅቱ የነጻ ገበያ መርህ አለኝ ብሎ አመታት የመራ መንግስት እንዴት እንደ አዲስ የጅምላ ንግድ ውስጥ ይገባል ተብሎ ብዙ ቢተችም ስለ “አለ በጅምላ” አስፈላጊነት በተደጋጋሚ እንዲሰበክ ተደረገ።
ኢቲ ካርኒ የተባለ የውጪ አማካሪ ኩባንያም “አለ በጅምላ” ን ለማቋቋም የማማከሩ ስራ ብዙም ግልጽ ባልሆነ መንገድ ተሰጠው። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ የኢኮኖሚ አማካሪ የነበሩት አቶ ንዋይ ገብረአብ የአለ በጅምላ የቦርድ ሊቀ መንበር ነበሩ ። ኢቲ ካርኒ የተሰኘውን አማካሪ ድርጅት ወደ አለ በጅምላን ማቋቋሙ ላይ እንዲያማክር በማድረግ ውስጥም እሳቸው ሚና ነበራቸው።
አለ በጅምላም በአንድ ቢሊየን ብር ካፒታል እንደተቋቋመ ተነገረ። ኢቲ ካርኒ አማካሪ ድርጅትም በሶስት አመት ውስጥ አለ በጅምላ በ27 የኢትዮጵያ ከተሞች 36 እንደ ስኳር ዘይት የተለያዩ ለስላሳ መጠጦችን ዱቄትና መሰል የፍጆታ ምርቶችን በጅምላ የሚሸጥበት መደብሮችን እንዲያቋቁም “ያማክራል ውጤታማ መሆኑንም ያረጋግጣል” የሚል ውል ተፈርሟል። ለዚህ ስራውም ከ250 ሚሊየን ብር በላይ እንዲከፈለው ስምምነት ተደረገ።
ዛሬ አለ በጅምላ የተባለው 36 ሱቆች በ27 ከተሞች የሉትም ። ሰባት ሱቆች ብቻ ነው ያሉት። ከዚህ ውስጥ ሶስቱ አዲስ አበባ ብቻ ያሉ ናቸው።በሀገሪቱ በጅምላ ንግድ ይይዛል የተባለውን ድርሻም አልያዘም የሸቀጦች የዋጋ ንረት እንዳይጨምር ይከላከላል የተባለውም ከወሬ ያለፈ አልሆነም።
የመንግስት ሰዎች አለ በጅምላ የተባለውን ተቋም ለመመስረት ያሰቡት ዎልማርት የተባለው የአሜሪካን የሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ልስራ የሚል ጥያቄ ሲያነሳ ነው እንጂ የሀይለማርያም ደሳለኝ መንግስት ሀሳቡም አልነበረውም።
ሲጀመር አለ በጅምላ ሲቋቋም አንድ ቢሊየን ብር የመቋቋሚያ ካፒታል በጥሬ ገንዘብና በአይነት ተሰጥቶታል ተብሎ ሲወራ የነበረው ውሸት ሆኖ ተገኘ። አለ በጅምላ ሲመሰረት ከመንግስት በጥሬ ገንዘብ ያገኘው ሀምሳ ሚሊየን ብር ብቻ ነበር። ጅንአድ ይጠቀምባቸው የነበሩ መደብሮች በአይነት ተሰጥተውታል። ከዚያ ውጭ ግን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 596 ሚሊየን ብር እንዲበደር ነው የተደረገው።
መንግስት ራሱ የሚያቋቁመውን ተቋም ይህን ያክል ገንዘብ እንዲበደር ማድረጉ ብዙ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ። በመመስረቻ ካፒታል ታሪክም የመጀመርያው ይመስላል። የተበደረውንም ገንዘብ እንዳለ ቢጠቀምበትም ምንም አልነበር። ከተበደረው 596 ሚሊየን ብር ውስጥ ከ250 ሚሊየን ብር በላዩን ለአማካሪው ኢቲ ካርኒ እንዲከፍል ነው የተደረገው። እዚህ ጋር ትልቅ የህግ ጥሰት ይነሳል። ኢቲ ካርኒ ያማከረበትን ገንዘብ ከአለ በጅምላ ሊቀበል አይገባም ነበር።ምክንያቱም ኢቲ ካርኒ የማማከር ውሉን ሲፈርም አለ በጅምላ አልተቋቋመም። ስለዚህ ውል ሲፈረም የሌለ ተቋም የውል ማስፈጸሚያ ሊከፍል አይገባም። ሆኖም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የጅምላ ሱቅ ለመክፈት ማማከሪያነት ተከፈለ።
ከተከፈለም በሁዋላ ግን ኢቲ ካርኒ የተሰኘው አማካሪ ኩባንያ አለ በጅምላ በውል የተገቡትን ግቦች ሳያሳካ ከ2006 እስከ 2009 አ.ም ያለውን የሶስት አመት ውል ጨርሷል። ምክንያቱም የአማካሪ ኩባንያው የሶስት አመት ስራ በ27 የሀገሪቱ ከተሞች 36 የአለ በጅምላ ሱቆችን ማስከፈት ነበር።አለ በጅምላ ግን ሰባት ሱቅ ብቻ ነው ያለው። የተባለውን ያክል ቁጥር ያላቸው ጅምላ ማከፋፈያዎችን እንዲከፍትም ገንዘብ የለውም ። ጭራሽ አሁን የ596 ሚሊየን ብር እዳውን መክፈል ጀምሮ የሚሸጣቸውንም እቃዎች ማምጣት አቅቶታል። የድሬዳዋ የመቀሌና የጅማ ከተማ አስተዳደሮች አለ በጅምላ ማከፋፈያ እንዲከፍት የተለያየ መጠን ያለውን ቦታ ሰጥተውት ነበር።ማከፋፈያ ሱቆችን መክፈት ስላቃተውም የከተማ አስተዳደሮቹ ቦታ የመስጠት ሀሳባቸውን ሰርዘውታል።
አለ በጅምላ በከፍተኛ ብድር ስራ ውስጥ ገብቶ እንደነበር እየታወቀ ያልተገቡ አሰራሮች ይፈጸምበት ነበር። ከውጭ የሚገዛቸው እቃዎች አግባብነት ባለው የግዥ ሀላፊዎች ተሳታፊነትና በጨረታ መገዛት ሲገባው አንድ የተቋሙ ሀላፊ ከሚያውቀው የውጭ ኩባንያ ጋር ተደዋውሎ ግዥ ሲፈጽም ቆይቷል። ይህ የወንጀል ውጤትን አምጥቷል በሚል ምርመራ በጠቅላይ አቃቤ ህግ የተጀመረ ቢሆንም የተወሰደ እርምጃ ግን እንደሌለ አረጋግጠናል።ቤቱ በኪሳራ እና እዳ መመራቱ አለመረጋጋት ስለፈጠረበትም ሁለት አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሶስት አመራሮች ተፈራርቀውበታል።
አሁን አለ በጅምላ የፍጆታ እቃዎች ንግድ ስራ በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ስር ነው ያለው።ከ2008 አም ጀምሮ በኮርፖሬሽኑ ስር የሆነው ተመሳሳይ ስራን የሚሰሩ ተቋማት አንድ ላይ ቢሆኑ ውጤታማ ይሆናሉ በሚል ከፊት የተቀመጠ ምክንያት ቢሆንም ፣ ዋናው አላማ ግን አለ በጅምላ ብቻውን ቢቆም የተሰሩበት ያልተገቡ ተግባራት ፍጥጥ ብለው ስለሚወጡና ተጠያቂነትን አለማምጣት ከባድ ስለሚሆን ነው። በዚያውም የገንዘብ እጥረት ውስጥ ስለገባ በኮርፖሬሽኑ ውስጥ አብረውት ከታቀፉት እነ የእህል ንግድ ላይ ገንዘብ እየተበደረ በመስራት ገበናዎቹ እንዲሸፋፈኑለት ነው። በቅርቡም ሸቀጦችን የሚገዛበት ገንዘብ አጥቶ ከሌሎች ርጅቶች 400 ሚሊየን ብር ተበድሮ ነው መንቀሳቀስ የቻለው። [ተጨማሪ የድምፅ ዝርዝር ዘገባ ከታች ይመልከቱ]
https://youtu.be/nYeVyMDNN14