ዋዜማ ራዲዮ- በቅርቡ መንግስት የሚንስትር መስሪያ ቤቶችን ቁጥር ከ28 ወደ 20 መቀነሱን ተከትሎ የሚታጠፉና የሚዋሀዱ መስሪያ ቤት ሰራተኞች ዕጣ ፈንታችን አሳስቦናል ብለዋል።
በከፍተኛ ሀላፊነት ሲሰሩ የነበሩ አሁን በስራ ልምድ በትምህርት ዝግጅትና በደሞዝ ጭምር በሚያንሷቸው የሌላ መስሪያቤት ሰራተኞች ስር መመደባቸው ተገቢ አይደለም ብለው ያምናሉ። ቀደም ሲል በያዙት ሀላፊነትና የሙያ መስክ ስለመቀጠላቸው እንደሚጠራጠሩና በሂደት በሰው ሀይል መደራረብ ስራ እናጣለን የሚል ስጋትም አላቸው።
በሀገሪቱ የሚደረገውን ለውጥ ለመደገፍ አስፈላጊውን ዋጋ እንከፍላለን ያሉት ሰራተኞቹ ሽግሽጉን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመው በቡድን የሚሰባሰቡ አካላት እንዳይኖሩ ተገቢው ትኩረት ሊደረግ ይገባል።
በውህደት ወደ አንድ በተቀላቀለ የሚንስትር መስሪያ ቤት በመካከለኛ ሃላፊነት እያገለገሉ ያሉ ግለስብ እንደነገሩን ተመሳሳይ ስራና ሀላፊነት ከኣአንድ በላይ ለሆኑ ሰዎች በመሰጠቱ ግርታና አለመግባባት መከሰቱን ታዝቤያለሁ ብለዋል። እያንዳንዱ መስሪያቤት ፈጠን ብሎ የሰው ሀይል አደረጃጀቱን ለውጡን ታሳቢ ባደረገ መልክ ቢከልስ ተጨማሪ የሰው ሀይል ብርታት እንጂ ችግር ሊሆን አይችልም፣ እንዳውም አንዳንድ ተቋማት የበረታ የሰው ሀይል ችግር ያለባቸው ናቸው ሲሉ ያስረዳሉ።
ከታጠፉ መስሪያ ቤቶች አንዱ የሆነው የመንግስት ኮምኔኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ሰራተኞች የተወሰኑት ወደ ዜና አገልግሎት ድርጅት እንደሚቀላቀሉ የተነገራቸው ሲሆን የቀሩት ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮና ብሮድካስት ባለስልጣን እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል።
በቅርቡ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ጋር ሊቀላቀል እንቅስቃሴው ከተጀመረ በኋላ ባለበት እንዲቀጥል ወደ ተደረገው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ( ኢ ዜ አ) 22 ሰራኞች እንዲመደቡ የተደረገ ሲሆን ቀሪዎቹ ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት እና ብሮድካስት ባለስልጣን እንደሚመደቡም ታውቋል፡፡
በተለይ ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት እንደሚዛወሩ የሚጠበቁት ሰራተኞች በጠቅላይ ሚንስትሩ ልዩ ጽህፈት ቤት ስር በተጠናከረ መልኩ ሊቋቋም ለሚታሰበው የሚዲያና የኮሚዩኒኬሽን ክፍል አጋዥ ይሆናሉም ተብሎ ታስቧል፡፡
የመንግስት የኮምኒኬሽን ስራዎችን በተመለከተ በመንግስት በኩል የተዘበራረቀ አስተያየት መኖሩም ተሰምቷል። የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እስከ ወረዳ የዘለቀና የገዥው ፓርቲን ዓላማዎች እንዲያስፈፅም የተደራጀ በአመዛኙ የካድሬ ስራዎችን ሲያከናውን የቆየ ተቋም ነው። በአቶ በረከት ስምዖን ጠንሳሽነት የተቋቋመው ይህ መስሪያ ቤት ከክልል መንግስታት ጋር ግጭት ውስጥ የሚያስገባ የስራ ሀላፊነትም ነበረው። አሁን መንግስት ስራውን የሚናገርለት ማዕከላዊ ቃል አቀባይ ያስፈልገዋል ወይስ ሁሉም ተቋም የራሱ የዘርፍ ቃል አቀባይ ይኖረዋል በሚለው ጉዳይ ላይ ግልፅነት አለመኖሩን የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ሳይቀር እያስረዱ ነው።
የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ጠንካራ የህዝብ ግንኙነት ተቋም እንዲዋቀር ፍላጎት እንዳለውና ለዚህም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ስምተናል።