ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብፅ በሕዳሴው ግድብ ውሀ አሞላል ላይ ሲያደርጉ የነበረውን ውይይት አጠናቀቁ፣ ግብፅ ስነዱን አልፈረመችም።
ማክስኞ በአዲስ አበባ ሲደረግ የነበረው በሕዳሴው ግንብ ውሀ አሞላል ላይ ባለሙያዎች ያቀረቡት የቴክኒክ ጥናት ላይ ሲደረግ የነበረው ድርድር በመስማማት ምሽቱን ተጠናቋል። ሱዳንና ኢትዮጵያ ስነዱን ወዲያውኑ ሲፈርሙ የግብፅ ልዑካን ቡድን ግን በጉዳዩ ላይ ከሀገሪቱ መንግስት ከፍተኛ ባላስልጣናት ጋር ተነጋግሮ እንደሚመለስ አስታውቋል።
ድርድሩ በመግባባት የተደረገ እንደነበርና የግብፅ ልዑካንም በቃል ስምምነቱን መግለፁን ስምተናል።
የግድቡ የውሀ አሞላል እንደ ዝናቡ መጠን ታይቶ ከአራት እስከ ሰባት ዓመት ሊወስድ እንደሚችል በባለሙያዎች የቀረበውን ጥናት መነሻ በማድረግ ሀገሮቹ ከስምምነት ደርሰዋል።
ቀደም ሲል ተቋርጦ የነበረው ውይይት የኢትዮጵያና የግብፅ መሪዎች በቻይና የአፍሪካ-ቻይና ጉባዔ ወቅት ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት ድርድሩን ለመቀጠል በደረሱት ስምምነት መሰረት ነው።የሶስቱ ሀገራት የውሀ ሚኒስትሮች ስብሰባ ከመክፈቻው በስተቀር በዝግ ሲካሄድ የዋለ ነው።
ዋዜማ ራዲዮ ከዚህ ቀደም እንደዘገበችው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሞላል ላይ የሶስቱ ሀገራት የባለሙያዎች ቡድን በበርካታ ነጥቦች ላይ እየተስማሙ ከመጡ በሁዋላ ግብፅ የወከሏት ባለሙያዎች ውይይቱን አቋርጠው ወጥተዋል። ግብፅ በወቅቱ የህዳሴው ግድብ የገባበት ምስቅልቅልን ተከትሎ አማራጮችን ለማየት መውጣቷ ተነግሯል።
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቤይጂንግ በተካሄደው የቻይና አፍሪካ ጉባኤ ላይ ከግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ጋር ውይይት ካደረጉ በሁዋላ ግብጽ በውሀ አሞላሉ ላይ ለመነጋገር ወደ ጠረጴዛ ተመልሳለች።በሁለቱ ውይይት ወቅት ግብጽን ወደ ጠረጴዛ እንድትመለስ ያደረጋት ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ ግልጽ ባይሆንም ሁለቱ ሀገራት በግድቡ ላይ የሚደረጉ ሁለት ጥናችን የሚያደርጉ ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች አሰራር ጋር በተያያዘ የነበሩ ልዩነቶች ከመሪዎቹ ውይይት በሁዋላ መፈታታቸው ተነግሯል። ሆኖም ድርድሩ ከመጣበት ሂደት አንጻር አሁንም የግብፅን አቋም መተንበይ እንደማይቻል ጉዳዩን በቅርበትየሚያውቁ ባለሙያ ነግረውናል።
ስለድርድሩ መቋረጥ ቀደም ሲል አቅርበነው የነበረውን ዘገባ እዚህ ይመልከቱ።– https://goo.gl/y3FsVx