ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት ሰባት ዓመታት በመንግስታቱ ድርጅት ተጠሪ የነበሩትን ዶ/ር ተቀዳ አለሙን በማንሳት አምባሳደር ታዬ ዐፅቀስላሴን መመደቡን አስታወቀ።
የውጪጉዳይ ሚኒስቴር እንዳረጋገጠልን የረጅም ዘመን የዲፕሎማሲ አገልግሎት ያላቸው ዶ/ር ተቀዳ አለሙ ወደ ዋናው መስሪያ ቤት ተጠርተዋል። አምባሳደር ተቀዳ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ የረጅም ዘመን አገልግሎት የሰጡ አንጋፋ ባለሙያ ሲሆኑ የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባልም አይደሉም።
ዶ/ር ተቀዳ በአዲስ ሀላፊነት ይሾማሉ በሚል ላነሳነው ጥያቄ ማረጋገጫ አላገኘንም። ይሁንና ቀደም ሲል በነበሩበት የሚኒስትር ማዕረግ አልያም በውጪ ጉዳዮች ላይ ለጠቅላይ ሚንስትሩ በአማካሪነት ሊመደቡ ይችላሉ የሚል ግምት እንዳላቸው የሰራ ባልደረቦቻቸው ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ በኤርትራ አዲስ አምባሳደር ለመሾም እየተዘጋጀች መሆኗም ለሽግሽጉ አንድ ምክንያት ተደርጎ ተወስዷል።
ሌላው አዲስ ተሿሚ አምባሳደር ታዬ ዐፅቀስላሴ አሁን በግብፅ ካይሮ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ ሲሆን ቀደም ሲል በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቆንስላ ሆነው ሰርተዋል። አምባሳደር ታዬ በዳይሬክቶሬት ሀላፊነትና በሚኒስትር ዴኤታ ደረጃም በመስሪያ ቤቱ አገልግለዋል።
በተለይም በዓባይ ውሀ ጉዳይ ከግብፅ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ዉጥረት በነበረበት ወቅት ገንቢ ሚና በመጫወት አምባሳደር ታዬ ተጠቃሽ ናቸው።
በምስራቅ አፍሪቃ ከተፈጠረው አዲስ የጂኦፖለቲካ ክስተት አንፃር ኢትዮጵያ አጠቃላይ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዋን ለመፈተሽና ለማሻሻል የምትገደድበት ደረጃ ላይ መድረሷን የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ባልደረቦች ያሰምሩበታል።
የሀገሪቱን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ የመከለስ ጉዳይም አንዱ የለውጡ አካል መሆኑን ለዋዜማ የደረሰ መረጃ ያመለክታል።