ዋዜማ ራዲዮ- ኢኤን ኤን(ENN) ቴሌቭዥን ጣቢያ ከሀምሌ አንድ ጀምሮ ስርጭቱን አቋርጦ በይፋ ሊዘጋ መሆኑ ተሰማ።
በመጪው አርብ 110 የሚሆኑ ቋሚ ሰራተኞቹን በይፋ ሊያሰናብት መዘጋጀቱንም የቅርብ ምንጮች ነግረውናል።
የኢኤን ኤን ከስርጭት መውጣት ምክንያት የመንግስት መስሪያቤቶች መረጃ ለጣቢያው መስጠት ማቆማቸው አንዱ ሲሆን የአመት ስፖንሰር የሆኑት ኢትዮ ቴሌኮም እና ንግድ ባንድ በድንገት ውላቸውን ማቋረጣቸው የጣቢያውን ገቢ ማሳጣቱን የኢኤን ኤን ምንጮቻችን ለዋዜማ ጠቁመዋል።
እንደ ምንጫችን ጣቢያው ከዳሽን ባንክ በብድር ሊያገኝ የነበረው 500 ሚሊዮን ብር ብድር በብሄራዊ ባንክ ትዕዛዝ እንዲሰረዝ መደረጉን ነግረውናል።
ኢኤንኤን በሀገሪቱ ህዝባዊ ተቃውሞ በተፋፋመበት ወቅት ሁከት አባባሽና “ብሄር ከብሄር ለማጋጨት የሚቀሰቅስ” ዘገባ በማቅረብ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበት ነበር።
ለዘገባው ሀሰተኛ ምስል መጠቀሙና ዘገባው የተላለፈበት ሰዓት ተዳምረው ጣብያው “ስውር ተልዕኮ አለው” የሚል ውንጀላ እንዲቀርብበት ምክንያት ሆኗል።
ከሕወሐት አመራሮች ጋር የቀረብ ግንኙነት ያለው ኢኤንኤን መቀመጫውን አዲስ አበባ አድርጎ ወቅታዊ ጉዳዮችንና የመዝናኛ ይዘት ያላቸውን ፕሮግራሞች ያቀርብ ነበር።