President Isayas Afeworki May 22/2018
President Isayas Afeworki May 22/2018

ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ የአልጀርሱን የሰላም ስምምነት ያለቅድመ ሁኔታ እንደምትቀበል መግለጿን ተከትሎ የኤርትራ መንግስት በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ይፋዊ ምላሽ ለመስጠት አልሞከረም።
ኢትዮጵያ በተግባር ወታደሮቿን ከባድመ ካላስወጣች በቀር የሰላም ስምምነቱን ተቃብያለሁ ማለቱ ብቻ በቂ ባለመሆኑ የኤርትራ መንግስት ምላሽ መስጠት አስፈላጊ ነው ብሎ እንደማያምን ተሰምቷል።
ኢትዮጵያ ወታደሮቿን በተቆረጠ ቀን ከባድመ ለማስወጣት የኤርትራን ምላሽ ስትጠባበቅ እንደነበረ አሁን ግን ጉዳዩ አዲስ መልክ እየያዘ መምጣቱን የኢትዮጵያ መንግስት ምንጮች ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ የሰላም እርምጃ በበርካታ የምዕራብና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ተሰፋ የተጣለበትና ውዳሴ የተቸረው ሆኗል።
ቀደም ባሉ ወራት ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማቀራረብ ሲሞክሩ የነበሩት የሳዑዲ ዐረቢያ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሰልማን ነበሩ። አሁን ጥረቱን በማጠናከር የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የምትመራው አዲስ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ሰኔ 8 እና 9 ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። ቢን ዛይድ ወደ አዲስ አበባ የመጡት የሁለቱን ሀገሮች ወዳጅነት ለማጠናከር ነው ቢባልም ልዩ ተልዕኮ እንዳላቸው ተሰምቷል። የዋዜማ  ምንጮች እንደነገሩን ልዑሉ ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማሸማገል ጥረት እያደረጉ ነው።  ከሶስት ሳምንታት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ወደ በሀገራቱ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ጉዳዩ ውይይት እንደተደረገበት ተነግሯል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከሳዑዲ ዐረቢያ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሰልማን ጋር በመሆን የኤርትራን ፕሬዝዳንት በስልክ ለማናገር ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ መቅረቱን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ራሳቸው ተናግረው ነበር።

ኢትዮጵያ ወታደሮቿን በማስወጣት ዕቅዷ እንድትገፋና ተጨማሪ የሰላም እርምጃዎች እንድትወስድ ከዚያ በኋላ ኤርትራን በቀላሉ ወደ ውይይት ጠረጴዛ ማምጣት እንደሚቻል አደራዳሪዎቹ ሀሳብ አላቸው። በኢትዮጵያ በኩል ግን የሰላም ሀሳቡን ተግባራዊ ለማድረግ ራሱ ከኤርትራ ጋር መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን በአፅንኦት መነሳቱን ጉዳዩን እናውቃለን ያሉ የመረጃ ምንጮቻችን ነግረውናል።
የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ ኢትዮጵያ የገጠማትን የውጪ ምንዛሪ እጥረት ለማቃለል አንድ ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ያደረገች ሲሆን ተጨማሪ ሁለት ቢለየን ዶላር የኢቨስትመንት ድጋፍም ቃል ተገብቷል። ሶማሊያና የኢንቨስትመንት ጉዳይ በልዑል  አልጋ ወራሽ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ እና በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መካከል በስፋት ውይይት እንደተደረገበትም ስምተናል።

በየመን ቀውስ ሳቢያ ሳዑዲና ኤምሬትስ የአፍሪቃውያንን የጦር ሰራዊት ለመጠቀም ፍላጎት እንዳላቸው ሲነገር ስንብቷል። [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/l8abxrKQ2U8