ዋዜማ ራዲዮ- የአሜሪካ መንግስት እጅግ ዘመናዊና በዓለም ላይ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በመስጠትም ሆነ በተሰማራባቸው የጦር ግንባሮች ተልእኮዎችን በስኬት በመፈጸም አስተማማኝነቱ የሚነገረለትን C-130 የተባለውን የጦር መጓጓዣ አውሮፕላን ለኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በስጦታ አበረከተ፡፡
በአሜሪካው መከላከያ መስሪያ ቤት ፔንታጎን ከ60 ዓመታት በላይ ተመራጭ እንደሆነ የሚነገርለት C-130 Hercules ተብሎ የሚጠራውና ሎክሂድ (Lockheed Martin) ግዙፍ ኩባንያ የሚመረተው ይኸው የጦር አውሮፕላን በዋነኝነት በጦር ግንባሮች የጦር መሳሪያ፣ ስንቅና መድሐኒት ለማቀበል፣ የቆስሉ ወይም ጉዳት የደረሳቸውን ወታደሮች ለማንሳትና ለማንኛውም አስቸኳይ አደጋዎች በማንኛውም የጦርነትና የአደጋ ቀጠናዎች ልዩ እገዛ በመስጠት ይታወቃል፡፡
አስፈላጊ ሲሆንም በተፈለገባቸው የጦር ቀጠናዎችም ከሰማይ ቦምብ በማዝነብ ድብደባም መፈጸም እንደሚችልና በአሜሪካም ሆነ በሌሎች አገሮች ከተመረቱ የጦር አውሮፕላኖች በግምባር ቀደም ተመራጭና የተዋጊ ወታደሮች አለኝታ ተብሎም ሲጠራ ይሰማል፡፡
የሰላም ማስከበር ሚና ለማገዝና በሁለቱ አገራት የለውን ወታደራዊ ትብበርና ግንኙነት ለማጠናከር በሚል እሳቤ የአሜሪካው መከላከያ መስሪያ ቤቱ ይህንኑ የጦር አውሮፕን ረቡዕ ግንቦት 29፣ 2010 ዓ.ም ለኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አስረክቧል፡፡
ርክክቡም በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጊቢ ውስጥ የተከናወነ ሲሆን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምበሳደር የሆኑት ሚካኤል ሬይነር እና በአውሮፓና አፍሪካ የአሜሪካ አየር ኃይል ተወካይ የሆኑት ብርጋዴር ጀነራል ዴይተር ባሬይሽ እንዲሁም በኢትዮጵያ በኩል የአየር ኃይል ኃለፊው ሌተ. ጀነራል አደም መሃመድ ርክክቡን ፈጽመዋል፡፡
ስጦታው በሁለቱ አገሮች መካክለ ያለውን ወዳጀነትና ትብበር በጥልቀት የሚያስተሳሳርና አገራቱ በቀጠናው ሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ያለቸውን የጋራ የመሪነት ሚና የሚያጠናክር መሆኑን አመባደር ሬይነር ገልጸዋል ፡፡
ብርጋዴር ጀነራሉ ባሬይሽ በበኩላቸው ስጦታው “በአገሮቻችን መካካል የቆየውን ጥብቅ ወዳጅነት ወደ ላቀና አዲስ የትብብር መስክ የሚያሸጋግርና ለጋራ አላማ አንድ ሆነን ዘመቻ ለማካሄድ የሚያስችለንን መሰረት መጣላችንን የሚያመለክት ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በቴክሳስ በሚገኘውና በዓለም ግዙፉ የጦር አውሮፕላን አምራች ሎክሂድ (Lockheed Martin) ከ2,700 በላይ አውሮፕላኖች ተመርተዋል፡፡ የአንዱ አውሮፕላን የሽያጭ አማካይ ዋጋው 35 ሚሊየን ዶላር ያህል ነው።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በደርግ ዘመነ መንግስት የ C-130 ዝርያ የሆነ ሁለት L100 ሄርኩልስ አውሮፕላን የነበራት ሲሆን ለረጅም አመታት የአሜሪካ ምርቶችን መጠቀም አቁማ ነበር። ከአራት አመት በፊት ያገለገለ C-130 አውሮፕላን ከአሜሪካ መንግስት በዕርዳታ አግኝታለች። የመለዋወጫ፣ የአውሮፕላኑ ዋጋ ውድነትና የአብራሪዎች ስልጠና ሩሲያ ሰራሽ አውሮፕላኖች ላይ ጥገኛ እንድትሆን አድርጓታል።