ዋዜማ ራዲዮ- ከአንድ ወር በኋላ በዳላስ በሚደረገው የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌደሬሽን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በበዓሉ ላይ ለመገኘት ያቀረቡት ጥያቄ ከረፈደ የመጣ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለማስተናገድ እንደሚቸገር በመግለፅ ጥያቄውን ሳይቀበለው ቀርቷል።
የፌደሬሽኑ የቦርድ አመራሮች በጉዳዩ ላይ በዝርዝር ከመከሩ በኋላ የዝግጅቱ ቦታ (ስታዲየም) ሰው የመያዝ አቅም ፣ የፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች እንዲሁም የኢንሹራንሰ ሽፋንን በቀረው አጭር ጊዜ ማስተካከል ስለማይቻል ጠቅላይ ሚንስትሩ ባይገኙ እንደሚሻል ውሳኔ አሳልፏል።
ውሳኔው የፖለቲካ ማንነትን መሰረት ያደረገ አለመሆኑንና ፌደሬሽኑ ለፖለቲከኞች ግብዣ የመላክም ፣ ለተሳትፎ ሲጠየቅ የመቀበል ሙሉ መብት እንዳለው ያስረዳል።
“ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ይህን በዓል ለመታደም መጠየቃቸው ለፌደሬሽናችን ክብር ነው” ያለው የቦርዱ መግለጫ በቀጣይ ጠቅላይ ሚንስትሩን ማስተናገድ የሚቻልበት ዕድል የሚኖር ከሆነ ቀድሞ እንደሚዘጋጅበት ተናግሯል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የዕርቅና መግባባት አጀንዳቸውን ወደ ባህር ማዶ ለማስፋት በማለም በበዓሉ ላይ ተገኝተው አጭር ንግግር የማድረግ እቅድ ነበራቸው። እግረ መንገዳቸውንም ከታዋቂ ኢትዮጵያውያን ጋር ለመነጋገር ዝግጅት እያደረጉ እንደነበር ተሰምቷል።
አንድ የኢትዮጵያ የሀገር መሪ በዚህ በዓል ላይ ለመገኘት ሲጠይቅ ዐቢይ አህመድ የመጀመሪያው ናቸው።