ዋዜማ ራዲዮ-የበረታውን የፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ ገዥው ግንባር በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተውተረተረ ይገኛል። መሰረታዊ የፖለቲካ ማሻሻያ መደረግ አለበት የሚሉ ድምጾች በበረቱበት በአሁኑ ሰዓት ስባት ሚሊየን አባላት ያሉት ኢህአዴግ ራሱን አንድ አድርጎ መራመድ ተስኖታል። የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ለአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቷል። የመከላከያ ኤታማዦር ሹሙ ሳሞራ የኑስ መልቀቂያ ያስገባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዲነሱ የቀረበው ሀሳብ ከምንግዜውም በላይ አጀንዳ ሆኖ እየተናፈሰ ነው። ከዋዜማ ራዲዮ አቅም በፈቀደ በገዥው ግንባር ሰፈር ያለውን መረጃ በግርድፉ ከተለያዩ ምንጮች አሰባስበን አቅርበናል አንብቡት።
በተቃውሞ እየተናጠ መረጋጋት የራቀው ኢህአዴግ ሰፊ የአመራር ሽግሽግ እንደሚያደርግ ለፓርቲው ቅርብ የሆኑ ሰዎች ግምታቸውን እየሰጡ ነው፡፡ ለዋዜማ የግል አስተያየታቸውን በስልክ ያካፈሉ አንድ የቀድሞ የፓርቲው ከፍተኛ ባለሥልጣንና አምባሳደር እንደሚሉት ብአዴንና ህወሓት በጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትላቸው ደካማ አመራር ‹‹ፍጹም ደስተኞች እንዳልሆኑ›› በይፋ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ ‹‹ቀደም ባለው ስብሰባ ስብሀት ነጋ ኃይለማርያም ላይ የሰላ ሂስ መስጠቱን አውቃለሁ፡፡ አልቻልክበትም ብሎታል፡፡…አሁን የቸገራቸው እሱን አንስተው ማንን እንደሚያመጡ ነው፡፡›› ይላሉ እኚሁ የቀድሞ ባለሥልጣን፡፡
በመሪዎች ደረጃ ለውጥ ይጠበቅ የነበረው ከወራት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው በ11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ቢኾንም የሐዋሳው ጉባኤ የተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ላልተወሰነ ጊዜ በመገፋቱ የሥልጣን ሽግሽጉ ከተጠበቀው ጊዜ ቀደም ብሎ እንዲካሄድ በአራቱም የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ ፍላጎት ታይቷል፡፡ ይህም በመሆኑ ከትናንት በስቲያ ማምሻውን አራቱ የፓርቲ አመራሮች ስብሰባ አቋርጠው የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የተላለፈው መልዕክት ተሰርዞ በምትኩ ደኢህዴንና ብአዴን ስብሰባቸውን እንደጨረሱ አስቸኳይ የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ እንዲካሄድ ተወስኖ ነበር፡፡
ትናንት ምሽቱን ደግሞ ዳግም ስብሰባው ዛሬ ሐሞስ እንደሚካሄድ እየተነገረ ነው። የስብሰባው የጊዜ ሰሌዳ መዘበራረቅ ፓርቲው በሀገሪቱ እየበረታ የመጣው ቀውስ ያስከተለው ስጋት መሆኑን ግምታቸውን የነገሩን አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ግማሽ ካቢኔያቸውን ለመፐወዝና አዳዲስ አደረጃጀቶችንና መዋቅሮችን ለማስተዋወቅ በአዲስ መንፈስ ኮሚቴ አቋቁመው እየሰሩ እንደነበር እንደሚውቁ የጠቀሱት እኚህ የቀድሞ ሹምና አምባሳደር፣ ባለፉት ሳምንታት ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር (ሞንጀሪኖ) የሚመሩት አንድ ቡድን አዳዲስ ተሽዋሚዎችን በመመልመል ተጠምዶ እንደነበር እንደሚውቁም ተናግረዋል፡፡
አዳዲስ ተሸዋሚዎችን ያስተናግዳሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተቋማት መሐል በዶክተር ደብረጺዮን ይመራ የነበረው የመገናኛ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ቦታ ሲሆን የብየነ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳን) ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲመሩ የቆዩት ጄኔራል ተክለብርሃን ወልደዓረጋይ ከቦታቸው ተነስተው የዶክተር ደብረጽዮንን የቀድሞ መሥሪያ ቤት እንዲመሩ መታጨታቸው ተስምቷል።፡፡ ኮሚቴው ከዚህም ባሻገር ሦስት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችንና ሁለት ኤጀንሲዎችን በአዲስ ለማዋቀር እየሰራ ሲሆን ዶክተር ነገሪ ሌንጮን የሚተካ እጩ አመራር በማፈላለግ ላይ እንደነበረም ተሰምቷል፡፡ ይህ የምልመላና የአዲስ መዋቅር እንቅስቃሴ የሀገሪቱ ቀውስ በመበርታቱ ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓል፡፡
በኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ መሰረት የመከላከያና ደህንነት ተቋማትን የመከለስና ሹም ሽር የማድረግ ስምምነት ቢደረግም የደህንነት ተቋሙ ጉዳይ ገና አልተጀመረም። የመከላከያ ኢታማዦር ሹም ሳሞራ የኑስን ለመተካት ሲደረግ የቆየው ምክክርም መቋጫ አላገኘም።
ከመከላከያ አካባቢ የወጡ ያልተረጋገጡ መረጃዎች በቀጣዮቹ ሳምንታት ዉስጥ ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ መልቀቂያቸውን እንደሚያስገቡ የሚጠበቅ ሲሆን ሲሆን ጄኔራል ሳዕረ መኮንን ይመር ቀጣዩ ጠቅላይ ኢታማዡር ሹም እንደሚሆኑና በሥራቸው የብሔር ውክልና ያላቸው ሦስት ጄኔራሎች እንዲኖሯቸው እንደሚደረግ ምክረ ሀሳብ መቅረቡን ጉዳዩን እናውቃለን ያሉ ምንጮች ነግረውናል። ፖለቲካዊ መረጋጋትን ለመፍጠር ሲባል እንዲሁም ወቅታዊ የፖለቲካ ሚዛኑን ከግምት በማስገባት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስን ሊተኩ ይችላል የሚል ግምት ከመነሻው ጀምሮ ሲናፈስ ቆይቶ የነበረ ቢኾንም ጉዳዩን የያዘው ኮሚቴ መካከል ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉም እየተነገረ ነው።
ይህ ጉዳይ በምደባ ኮሚቴው በኩል አወዛጋቢ ሆኗል። ለወቅታዊ ፖለቲካው ምላሽ ብርሀኑ ጁላ ተመራጭ ዕጩ ቢሆንም በልምድና በግዳጅ አፈፃፀም ሳዕረ ቢሆን ይሻላል ወደሚለው መደምደሚያ ተደርሷል። የዚህ ሳምንቱ የፖለቲካ ዝንባሌ ይህን ውሳኔ ሊያስቀይረው ይችላል የሚለው ግምትም እንዳለ ነው።
የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከጥር 23 ቀን ጀምሮ ስብሰባ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከደኢህዴን ቀደም ብሎ ለስብሰባ የተቀመጠው ብአዴን በሰሜን ወሎ በተፈጠሩ ግጭቶች አቋርጦት የነበረውን ስብሰባ ከጥር 27 ወዲህ እያካሄደው ይገኛል፡፡ ብአዴን ከፍተኛ አመራሮቹን ጭምር ሊቀይር ይችላል የሚሉ ግምቶች መሰማት የጀመሩት በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ ሲሆን በተለይም በፓርቲው ዘንድ ፍዝ ሚና ያላቸውን ሊቀመንበሩን አቶ ደመቀ መኮንንን ሊያሰናብት እንደሚችል ሰፊ ግምት ተሰጥቷል፡፡ ከስልጣን እንዲለቁ የበረታ ግፊት አለ። በአባላት መካከል በተደረገ ግለ-ግምገማ አቶ ደመቀ መኮንን በስልጣን እንዳይቆዩ የሚያደርግ ብርቱ ትችት እንደቀረበባቸው ተሰምቷል። በተለይ የክልሉ ህዝብ ወኪል ሆነው በማዕከላዊ መንግስት ውስጥ አንዳችም ተፅዕኖ መፍጠር ያለመቻላቸው በእናት ድርጅታቸው በኩል ከፍ ያለ ቅሬታ ፈጥሯል።
በሕወሓቶች ዘንድ የክልሉ ፕሬዚደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለል እንዲሉ ከፍ ያለ ፍላጎት መኖሩም ይነገራል፡፡ ብአዴንና ደኢህዴን እንደተገመተው አመራሮቻቸውን ገምግመው የሚያሰናብቱ ከሆነ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትርና ምክትላቸው ስለመነሳታቸው ተጨማሪ ማረጋገጫ እንደሚሆንም ይገመታል፡፡
ፕሬዚዳንቱን በሕዝበኝነት፣ ዋና ጸሐፊዉን በሥልጣን ጥመኝነት በቅርቡ የገመገመው ኦህዴድ ያልተጠበቀ የለውጥ ኃይል ኾኖ በወጣበት በዚህ ወቅት በኢህአዴግ ደረጃ በከፍተኛ አመራሩ ዘንድ የአመራር ሽግሽግ መደረጉ የሚያጠራጥር እንዳልሆነ የሚናገሩት እኚህ ባለሥልጣን ‹‹መጪዎቹ ወራት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ጊዜያት እንደሚሆኑ እምናለሁ›› ይላሉ፡፡