markel HMD

ዋዜማ ራዲዮ-የጀርመኗ መሪ አንጀላ ማርከል በኢትዮጵያ የሚካሄደው የፖለቲካ ማሻሻያ እንዲፋጠን ጠየቁ። የእስረኞች መፈታትን አወድሰዋል።

የጀርመን የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ምንጮች እንደነገሩን አንጀላ ማርኬል ከጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የፖለቲካ ቀውስ ጀርመንን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራትን እንደሚያሳሳብ ገልፀው ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ማሻሻዎችን እንዲተገብር መክረዋል።
የጀርመን ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በቅርቡ በአዲስ አበባ ጉብኝት አድርጎ ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፏል።
ማርኬል መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት የወሰደውን እርምጃ አድንቀው ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት እንዲደረግ፣ የፀጥታ ሀይሎችም የሀይል እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠቡ የመንግስታቸው ፍላጎት መሆኑን አብራርተዋል።
ሁለቱ መሪዎች በቀጣይ በሚወሰዱ የፖለቲካ እርምጃዎች ላይ የተነጋገሩ ሲሆን የጀርመን የውጪ ጉዳይ ምንጫችን ዝርዝሩን ከመናገር ተቆጥበዋል።  በአዲስ አበባ የጀርመን ኤምባሲም በሁለቱ መሪዎች መካከል ውይይት መደረጉን ገልጿል።

በተያያዘ ዜና የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር የልማት አማካሪ ድርጅታቸውን ወክለው አዲስ አበባን ጎብኝተዋል። ከጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ጋርም ተነጋግረዋል።

ብሌር ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚ መስክ ያደረገችው ጥረት በፖለቲካዊ ቀውሱ አደጋ ላይ መውደቁን በማመልከት መንግስት እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል።
በተለይም ባለሀብቶችና አበዳሪዎች ባልተረጋጋ ሀገር ላይ ማሳተፍ ስለሚያዳግታቸው የፖለቲካ መፍትሄ በቶሎ እንዲፈለግ መክረዋል። ብሌር አዲስ አበባ በነበሩበት ወቅት በኦሮምያ የስራ ማቆም አድማ እየተደረገ ነበር።

[በዝግ ዲፕሎማሲ ዙሪያ ያሉ መረጃዎችን ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ያገኛሉ]  

https://youtu.be/ULnKIRpzpBc