ዋዜማ ራዲዮ-የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በመጪዎቹ ቀናት “ወሳኝ” የተባለለትን ውሳኔ ያሳልፋል።
ስራ አስፈፃሚው ያለፉትን ቀናት በስብሰባ ያሳለፈ ሲሆን በመጪዎቹ ቀናት አዳዲስ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ ስብሰባ የሀገሪቱን የወደፊት አቅጣጫ የሚቀይር የውሳኔ ሀሳቦች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል።
የድርጅቱን የስብሰባ ዕቅድ የነገሩን ምንጮች ግን ስለ ስብሰባው አጀንዳ ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
“ድርጅቱ በእስከዛሬ ታሪኩ ወሳኝ የሚባል መሰረታዊ ጉዳይ አንስቶ ይነጋገራል” ይላሉ የወሬው ምንጫችን።
ለውይይት የተመረጡት ጉዳዮች በምስጢር ተይዘዋል። ሀሳቦቹ በቅርቡ ከአንድ ወር በላይ በተደረገው የየህወሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የተነሱና ለህዝብ ይፋ ያልተደረጉ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ በፓርቲው ፅህፈት ቤት ስራተኛ የሆኑ አንድ ግለሰብ ነግረውናል።
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት፣ አባልና አጋር ድርጅቶች ቀጣይ ሚና በፌደራል መንግስቱ ውስጥና ሌሎችም ጉዳዮች ተነስተው ነበር።
ድርጅቱ ከመጪው የኢህአዴግ አጠቃላይ ጉባዔ በፊት አቋም ሊወስድበት የ[ፈለገው ጉዳይ የሀገሪቱን የአስተዳደር ሁኔታ ከዚህ በፊት ከነበረው የልማታዊ መንግስት ፍልስፍና ወደ አዲስ መንገድ ለመውሰድ ያለመና የብሄር ፌደራዚሙ ሳይፈርስ በማዕከላዊነት እንዲመራ የሚያስችል ሊሆን ይችላል ሲሉ ግምታቸውን የነገሩን አሉ።
የኢህአዴግ በቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የተነደፈው የልማታዊ መንግስት አስተሳሰብና አሁን በሀገሪቱ የተከሰተው የብሄር ፌደራሊዝም ያስከተለው ቀውስን በተመለከት በርካታ አወዛጋቢ ክርክሮች ሲያደርግ ቢቆይም አማራጭና አሸናፊ ሀሳብ ሆኖ ለመውጣት የቻለ ሀሳብ አልተገኘም። ይሁንና ሀገሪቱ አዲስ የርዕዮት አለም መንገድ መከተል አለባት ብለው የሚያምኑ የድርጅቱ አባላት በጉዳዩ ላይ የበሰለ አማራጭ ሀሳብ የሚቀርብበት መድረክ እንዲፈጠር ሲጠይቁ ቆይተዋል።
[ይህ ዘገባ መጀመሪያ ይፋ ከተደረገ በኋላ አርታኦትና ማስተካከያ ተደርጎበታል]