ዋዜማ ራዲዮ- የሀገሪቱ የፀጥታና ደህንነት ምክር ቤት ትናንት ባደረገው ስብስባ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚስተካከል አዲስ ስልፍና ተቃውሞ የማድረግ መብትን የሚያግድ ክልከላ ጥሏል።
አዲሱ የሰልፍ ገደብን የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ቢያቀርብበትም ከብዙ ክርክር በኋላ ስምምነት ተደርሶበታል።
በተለይ የፀጥታ ሀይሎች “እርምጃ መውሰድ እንዲችሉ” መባሉ የኦሮሚያን ክልል እንደሚያሳስበው ገልጿል።
በአዲሱ የፀጥታ ዕቅድ መሰረት ሀገሪቱን በተለያዩ ዕዞች በሚመሩ የፌደራል መከላከያ ስራዊት አመራር ስር በማድረግ ለመቆጣጠር ታቅዷል።
አደረጃጀቱ ከዚህ ቀደም የኮማንድ ፖስት በመባል የሚጠራውን መዋቅር የሚከተል መሆኑን በስብሰባው የተካፈሉና ስለ እቅዱ በቅርበት የሚያውቁ የዋዜማ ምንጭ ነግረውናል።
በተለይ የክልልና የልዩ ሀይል እንዲሁም የፌደራል የፀጥታ ሀይሎች መካከል ያለውን አለመናበብ ለማስወገድ ማናቸውም መመሪያ በፌደራሉ ዕዝ ብቻ የሚወሰን እንደሚሆን ከስምምነት ተደርሷል ብለዋል።
“አስቸኳይ አዋጅ ተብሎ ያልወጣው አለማቀፉ ማህበረሰብ ሀገሪቱ አደጋ ላይ ናት ብሎ ያስባል፣ኢንቨስትመንትና ቱሪዝምንም ያዳክማል” በሚል መሆኑን ምንጫችን ተናግረዋል።
በፌደራል ፀጥታ አካላቱና በክልል ርዕሰ መስተዳድሮች መካከል ከፍተኛ አለመግባባትና አለመተማመን መከሰቱንም ከስብሰባው የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
“ሰው በመግደል ተቃውሞን ከማባባስ በቀር መፍትሄ አይመጣም፣ ፖለቲካዊ መፍትሄ ቢበጅለት የተሻለ ነው” በሚል የተከራከሩም ነበሩ።
በተለይ ብሄርን ማዕከል ባደረገ ጥቃት ከፍ ያለ አደጋ ተጋርጦብናል ያሉ ክልሎች መለዮ ለባሹ ጣልቃ ካልገባ ብዙ ጥፋት ይደርሳል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
ማህበራዊ ሚዲያን በሚመለከትም ስፊ ክርክር ተደርጓል። “እንደ አስፈላጊነቱ እርምጃ እንዲወሰድ” ከስምምነት ተደርሷል።
ከምክር ቤቱ አባላት የቀረቡትን ሀሳቦች በማካተት አዳዲስ የፀጥታ እርምጃዎች በተከታታይ የሚገለፁ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።