[ሙሔ ሀዘን ጨርቆስ ለዋዜማ ራዲዮ]

BodaBoda in Kenya- FILE POTO
BodaBoda in Kenya- FILE POTO

ትሪቨር ኖህ ምናለ በጦቢያ ቢወለድ እላለሁ-አንዳንዴ፡፡ የፖለቲካ ኮሜዲ በሀበሻ ምድር በሽ ነዋ!
ይኸው የኛው ጉድ በአጋዚ ስለሚያልቁ ንጹሐን ይነግሩናል ስንል ፓርላማ ገብተው ዶቅዶቄ ስለደቀነው አገራዊ አደጋ ይንዶቆዶቃሉ? ሰውየው Extremely ብሽቅ ሆነው እንጂ ‹‹ይንዶቆዶቃሉ›› የሚለው ቃል ለአገር መሪ የሚሆን አልነበረም፡፡
ግን ስንናደድስ!
እንዲያውም በፕሬዝዳንቱ የመክፈቻ ንግግር ስለ ዶቅዶቄ ሞተር ሳይክል አስከፊነት እንዲካተት ጠይቀው ነበር ይባላል፡፡ ዶክተር ሙላቱ ናቸው ‹‹አንተ ሰውዬ! ምን ነክቶሀል? ለቶርኖ ቤት ባለንብረቶች አይደለም እኮ ንግግሬን የማቀርበው›› ብለው የገሰጿቸው፡፡
ዩጎዝላቪያን ልትሆን ዋዜማ ላይ ላለች አገር ዶቅዶቄ ተፈናጦ የሚሞት ዜጋ ቁጥር ምኗ ነው? ስንት ዓይነት ‹‹ሄልሜት-ራስ›› አለ ባካችሁ?
እንዴት ናችሁ ግን እናንተ? አቃጥለው ደፉን እኮ!
እርሳቸው እንዳጋነኑት ባይሆንም ቅሉ ዶቅዶቄ በርካታ ከተሞችን እያመሰ ይገኛል፡፡ ወላይታ፣ሐዋሳና አዲሳባ በዚህ ረገድ ይጠቀሳሉ፡፡
ወላይታ የአራስ ልጅ ሞተር ላይ ተፈናጦ የናት ጡት የሚጠባበት አገር ነው፡፡ አላጋነንኩም፡፡ በቁም ነገር ቤተክርስቲያን ተገብቶ ‹‹ፓምፓራራራም…መድኃኒዓለም! ምን ይሳንሀል ዘንድሮን በሚስትና በዶቅዶቄ ባርከኝ›› ተብሎ ይጸለያል፡፡ ወንድ ልጅ ዲግሪ ሲጭንና ሞተር ሲገዛ ዘመድ አዝማድ ደግሶ ያበላል፡፡ ለዚያውም ቁርጥ…
በነገራችሁ ላይ እኒህ ጠቅላይ ሚኒስተር ከመጡ ጀምሮ ከተናገሩት የገባኝ ለአዲስ ዓመት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ስለ ቁርጥ ያወሩት ነገር ብቻ ነው፡፡ ከርሳቸው ይልቅ ባለቤታቸው ይገቡኛል፡፡ አንዳንዴ ኃላፊነት ቢቀያየሩ እላለሁ፡፡ ወይዘሮ ሮማን ቢመሩን፣ አቶ ኃይሌ ደግሞ የጡት ካንሰር በጎ ፈቃደኛ ቢሆኑ…?

ውድ የዋዜማ ሰዎች!
የጠቅላዩና የሞተር ቁርኝት ገርሞኝ አብሮ አደጎቻቸውን ጠየቅኩ፡፡ ለካንስ ‘HMD’ ልጅ ሳሉ በትውልድ ቀያቸው ቦሎሶ ሶሬ ሞተር ሳይክል ገጭቷቸው ያውቃል፡፡ በወላይታ እውቅ ወጌሻና በአፖስቶሊክ ጸሎት ነው የዳኑት፡፡ የሞተር ፎቢያ የጀመራቸው ምናልባት ከያን ጊዜ ጀምሮ ይሆናል፡፡
የቄራ ልጆች በጣም የሚያስቸግራቸውን ሰው ‹‹ጩቤ እሰቀስቅለታለሁ›› የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ የቦሎሶ ጎረምሳ ሲዝት ደግሞ ‹‹ሳድግ በሞተር ነው የምገጭህ›› ይላል፡፡ ‘HMD” እንዲያ እያሉ ነው ያደጉት፡፡ የሳኒቴሽን እንጂነር ሲሆኑ ሁሉኑም ነገር ተውት፡፡ ፖለቲከኛ ሲሆኑ ግን በጥይት ከሚቆላ ዜጋ ይልቅ በሞተር ተፈናጦ የሚሞት ወገን ያሳስባቸው ጀመር፡፡
ኦባማኬር እንደምንለው ‘ኃይሌኬር’ ብለን ለሞተር ተጎጂዎች የኢንሹራንስ ፖሊሲ እናበጃጅላቸው ይሆን? እንደው ደስ እንዲላቸው ማለቴ ነው…፡፡
እንዴት ናችሁ ግን እናንተ?
በዛሬው ጦማሬ (እድሜ ለአቶ ኃይሌ) ስለ ሞተር ሳይክልና ሸገር ጥቂት የምለው ይኖረኛል፡፡
###

ግመል የአረቡ ዓለም የበረሀ መርከብ ናት ካልን፣ “ቦዳቦዳ”ን የምሥራቅ አፍሪካ መንኮራኮር ልንለው ይገባል፡፡ ‘ቦዶቦዳ’ ዶቅዶቄ ማለት ነው፡፡ ሕንድ ተጸንሶ፣ ናይሮቢ ተፈልፍሎ፣ ሞቃዲሾ አድጎ፣ ካምፓላ እንደአሸን የፈላ ባለ ሁለት እግር ተሸከርካሪ ነው፡፡
ደልሂ ዜጎች በነፍስ ወከፍ ሦስት አላቸው፡፡ እዚያ ለልጅ ልደት ቶርታ ይዞ መሔድ ነውር ነው፡፡ ስኩተር ዶቅዶቄ ነው ደንቡ፡፡ አገራቸው ቶርኖ ቤት የመሰለው ያለምክንያት አይደለም፡፡
የኛዋ አዱ ገነት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ጥላቢሱ ባለሐዲዱ ባቡር እንጂ ቀልበ ቢስ ዶቅዶቄ አልደፈራትም ነበር፡፡ ዶቅዶቄ ወይ ለፖስተኛ ወይ ለትራፊክ ነው፡፡ የጨዋ ልጅ የሚጋልበው ነገር አልነበረም፡፡ በዚህ ሁኔታ ለዘመናት ታፍራና ተከብራ የኖረች ከተማ…እነሆ በመጨረሻ በዘመነ ኃይሌ ተሸነፈች፡፡ ለቦዳቦዳ እጅ ሰጠች፡፡ እውነት ለመናገር ይህ ለምንወዳት አዲስ አበባ በፍጹም መልካም ዜና አይደለም፡፡
ዶቅዶቄ ‹‹ሞተር የተገጠመለት የከተማ ዝንብ›› ማለት ነው፡፡ ጢዝዝዝዝ…..ከተማ ያቆሽሻል…እንዲሁም ያረክሳል፡፡
ዶቅዶቄዎች ቀትረ ቀላል ናቸው፤ ቀትረ ቀላል ብቻም ሳይሆን ቀልበ ቢስ ናቸው፣ ቀልበ ቢስ ብቻም ሳይሆን ክብረ ቢስም ናቸው፡፡ ለመግጨትም ለመገጨትም፣ ለመሞትም ለመግደልም ቅርብ…፡፡
ሾፌሮቻቸው በመንጃ ፍቃድ አይደለም የሚነገዱት፡፡ የ‹‹አደገኛ ቦዘኔነት›› የብቃት ማረጋገጫ አላቸው፡፡ ስለዚህ የትራፊክ ሕግን ማክበር በነሱ ቤት አለመሰልጠን ነው፡፡ ዶቅዶቄዎች ብዙዉን ጊዜ የሚጋለቡት እንደራሳቸው ምራቅ ባልዋጡና ባልተገሩ ጎረምሶች ነው፡፡ በዚህ አዲሱ ሩብ ዓመት ብቻ በ10ሩ ክፍለ ከተሞች 87 ሰው ይቺን ምድር ተሰናብቷል- በሞተር ተገጭቶ፡፡ አቶ ኃይሌ ወደው አልተጨነቁም…
እስከዛሬም ዶቅዶቄ ከትምህርት ቤት የተለቀቁ ፈልፈላ ሕጻነትን፣ ታዳጊዎችን፣ ተመራቂዎችን አሮጊቶችን፣ ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ ነጋዴዎችን፣ እንዲሁም ደግሞ በሕዝብ ዘንድ በከፍተኛ ፍቅር የሚወደዱ፣ በኦሮሚያ በመትረየስ ሰው የሚገድሉ የመከላከያ አባላትን ጭምር ገድሏል፡፡ (ይህ ነገር የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር መሰለብኝ…)
እንዴት ናችሁ ግን እናንተ?
እውነት ለመናገር ‘HMD’ እንዳጋገኑት ባይሆንም በከተማችን በሞተር በርከት ያለ ሰው እየሞተ ነው፡፡
‹‹ጉንጉን››ን የጻፉት ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል የአልጋ ቁራኛ ከሆኑ 6 ወር አለፋቸው፡፡ ሞተር ነው የገጫቸው፡፡ አዲሳባ ገዳይ አይጠፋም መቼም፡፡ ወይ ፌዴራል፣ ወይ ለግንባታ የተቆፈረ ጉድጓድ ወይ ታክሲ ወይ ሞተር ይገድላል፡፡ በሸገር ለመኖር ነው እንጂ ከባድ ለመሞት ብዙ አማራጭ አለ፡፡
በወዲያኛው ሳምንት የሆነ አገር ደርሼ ስመለስ ዶቅዶቄዎች ከተማዬን እንደጢንዚዛ ሲያውኳት ተመለከትኩ፡፡ ሞተርሳይክሎች በዝንብ ሕገ ደንብ ነው የሚራቡት ደግሞ፡፡ ቆሻሻ ካገኙ እልፍ ይሆናሉ፡፡
ሃያ ሁለት ከጌታሁን በሻህ ወደ ቦሌ በሚወስደው አቋራጭ አስፋልት፣ አዲሱ ቺቺንያ ጎዳና (የትግርኛ ተናጋሪዎች ከመብዛታቸው ጋር ተያይዞ ሰፈሩን ‹‹ፂፂኒያ›› የሚሉት አሉ) እልፍ አእላፍ ዶቅዶቄዎች ተሰግስገው ተመለከትኩ፡፡ ጋላቢዎቻቸው በቄንጥ እላያቸው ላይ ተፈናጠዋል፡፡ አንዳንዶቹ ጋላቢዎች ጫት ጎርሰው ጉንጫቸው የባጃጅ ጎማ አክሏል፡፡ ምን ይሆን ሥራቸው ብዬ መመራመር ያዝኩ፡፡ በዚህ ሐሳብ ዉስጥ ሳለሁ ታዲያ አንድ ሞተረኛ ሜቴክ የሰራው ከሚመስል  ሄሊኮፕተር ድምጽ በበለጠ እያጎራ በከፍተኛ ፍጥነት ከጎናችን አለፈ፡፡ ሴቶቻችን ቀሚስ መልበስ ትተዋል እንጂ ባስነሳው አቧራ መለመላቸውን ባስቀራቸው፡፡
“ግን ምን ሆኖ ነው እንዲህ የሚከንፈው?” ስል ጠየቅኩ፡፡
“በረራ ላይ ይሆናል” አሉኝ የሱ ጓደኞች የሚመስሉ ዱርዬ ልጆች፡፡ ለካንስ ዱርዬ አይደሉም፡፡ ሁሉም ከአዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች ዲግሪ አላቸው፡፡ ሁሉም ተክዚና ወጥረዋል፡፡ ተክዚናው በሪቮልቪንግ ፈንድ የተገዛ እንሆነ ተነገረኝ፡፡

አንባቢ ሆይ!
ዶቅዶቄዎች እንዲህ የሚሮጡት ደም የፈሰሳትን ወላድ ነፍስ ለማዳን ነው እንዴ? አይደለም፡፡ ለተክዚና ነው፡፡ ኋላ እንደተረዳሁት ‹‹በረራ›› ማለት ራሱ አራራን ለማከም የሚደረግ የሞተር ግልቢያ ነው፡፡ ቦዳቦዳዎች እንዲያ የሚበሩት ‹‹አቦ ሚስማር›› መቃም ጀምሮ ከምርቃና በፊት ጫት ያለቀበትን ዜጋን ለመታደግ ነው፡፡ ከቦዳቦዳዎች መቀመጫ ላይ ምንጊዜም የኮባ ቅጠል የማይጠፋውም ለዚሁ ነው፡፡ የኮባ ቅጠል ማለት የሞተር “ሴፍቲ-ቤልት” ነው፡፡
ሸገርን የሞሏት ዶቅዶቄዎች 60 በመቶ የሚሆኑት ጫት አመላላሾች ናቸው፡፡ መስቀል ፍላወርና 22 አካባቢ ዋና ጣቢያቸው ነው፡፡ ብዙዎቹ ከዩኒቨርስቲ የተመረቁና ሥራ ያጡ የክፍለሀገር ልጆች ሀብት ናቸው፡፡ በመስቀል ፍላወር የሚገኙት በተለይ ኑሯቸው ከጫት ገቢ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እድሜ ለዚህ ተስፋ አስቆራጭ መንግሥት! ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት የቃሚ ቁጥር ጨምሮ እንጂ ቀንሶ አያውቅም፡፡ ስለዚህም የሞተረኞች ገቢ ይጨምራል እንጂ አይቀንስም፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ዝቅተኛ ገቢ ያስመዘገቡትም ሰሞኑ በምሥራቁ ኢትዮጵያ በነበረው የድንበር ግጭት ምክንያት ነው፡፡

ዉድ የጦማሬ አንባቢዎች!
በአዲሱ ቺቺንያ (ጺጺኒያ) የሚገኙ ዝነኛ ጫት አከፋፋዮች የሱቅ አናት ላይ ደማቅ የማስታወቂያ ሰሌዳ ይታያል፡፡ ሁሉም ሰሌዳዎች ላይ ታዲያ የጫት ቤቱ ስምና የሞተረኛ ስልክ ቁጥር አይጠፋም፡፡ ተራ ጫት ቤትንና ባለኮከብ ጫት ቤትን የሚለየውም ይኸው ነው፡፡ ባለኮከቦቹ የትራንሰፖርት አገልግሎት በራሳቸው ወጪ ይሰጣሉ፡፡ ቢዝነስ ካርዳቸው “ነጻ የሞተር ሳይክል ሰርቪስ እንሰጣለን-ምርቃናዎ ሳይበርድ እንደርስሎታለን፤ ካሉበት ይዘዙን” ይላል፡፡
አንዳንድ ጫት ቤት ደግሞ የግል ቦዳቦዳ ባይኖረውም በሥሩ የሚንቀሳቀሱ ጥገኛ ሞተረኞች አሉት፡፡ በመካኒካል ኢንጂነሪንግ ተመርቀው ሥራ ያላገኙ ወጣቶች አሁን አሁን እንደምንም ተጋግዘው ዶቅዶቄ ገዝተው ጫት አመላላሽ ሆነው ኑሯቸውን እየለወጡ እንደሆነ ኢቢሲ በወጣቶች ፕሮግራም ላይ ገልጿል፡፡ የተሳካለት የጫት ኤክስፖርተር መሆን ቢያቅታቸው፣ የተሳካላቸው ጫት ትራንስፖርተር መሆን አላቃታቸውም፡፡

ዉድ የጦማሬ ወዳጆች!
እርግጥ ነው በቦዳቦዳ ብዙ ወንጀል ተፈጽሟ ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው በቦዳቦዳ አያሌ ዜጎች ጫት ልከዋል፣ አስልከዋል፣ቅመዋል፣ አስቅመዋል፡፡ ግን ቦዳቦዳ ሙሉ በሙሉ በእኩይ ተግባር የተሠማራ፣ ዉግዝ ማሽን ነው እንዴ? አይደለም !! ለዚህ ሁነኛ አብነቶችን መስጠት እችላለሁ፡፡
በአገሪቱ የመጀመርያው የግል ድንገተኛ የአምቡላንስ ሕክምና አገልግሎት ሰጪ “ጠብታ አምቡላንስ” ይባላል፡፡ ባለቤቱ አቶ ክብረት አበበ ናቸው፡፡ ለቀልጣፋ ማኅበረሰባዊ አገልግሎታቸው አገሪቱ ባትሸልማቸውም አውሮፓ ሸልማቸዋለች፡፡ አቶ ክብረት ታዲያ ከቅርቡ ጊዜ ወዲህ አምቡላንሶቻቸው በየመንገዱ እየዘገዩ ሕይወት የማዳን ተግባራቸው ተደናቀፈ፡፡ ምን ያርጉ…በየት ይሹለኩ? ሸገር እንደሁ በትራፊክ መጨናነቅ ምጥ ይዟታል፡፡
አቶ ክብረት አሰቡና መላ መቱ፡፡ ጥቂት የዶቅዶቄ አምቡላንሶችን አሰማሩ፡፡አሁን በጣም የተሳካ ሥራ እየሰሩ ነው፡፡ “ትራዉማ ባግ” የያዙ፣የቆመ ልብ የሚያስነሱ፣ ደም የሚያስቆሙ መሳሪያዎች የተገጠመላቸው ቦዳ-ቦዳዎች ክንፍ አውጥተው እየበረሩ አደጋ ቦታ ይደርሳሉ፤ ነፍስ ያድናሉ፡፡ እርግጥ ነው የአደጋው ስፍራ እስኪደርሱ ነፍስ አጥፍተው ሊሆን ይችላል፡፡
ቦዳቦዳዎች ለእቁብ አገልግሎትም ተመራጭ ሆነዋል፡፡ የካይዘን ፍልስፍናን የሚከተሉ እቁብ ቤቶች አንድ የእቁብ ሞተር ይገዛሉ፡፡ አንድ ጎረምሳ ይቀጠራል፡፡ ቻይና ሰራሽ ዶቅዶቄውን እያከነፈ፣ እቁብተኛን እያነፈነፈ ገንዘብ ይለቅማል፤ ግራና ቀኝ ኪሱን በብር አሳብጦ ወደዕቁብ ሰብሳቢው ከች…፡፡
ጋራዥና ስፔርፓርት እንደዘንድሮ ተፋቅረው ያውቃሉ እንዴ? ተክለኃይማኖት የነበሩ መኪና መለዋወጫ ሱቆች ብዙዎቹ በልማት ወደ ልደታ ተንሸራተዋል፡፡ አሁን ልደታ የመኪና መለዋወጫ ዕቃ ማዕከል ሆናለች፡፡ አዲሱ ሱማሌ ተራም ከልደታ በዳርማር ሞላ ማሩ የሚወስደው መንገድ ይዟል፡፡ ይህ ማለት የተሰረቀም ያልተሰረቀም የመኪና ዕቃ የሚሸጡት በቅርብ ርቀት ነው ማለት ነው፡፡
ጋራዦች በአንጻሩ ርቀዋል፡፡ ቄራ፣ ቡልጋሪያ፣ መብራት ኃይል፣ ጎፋ ወርደዋል፡፡ እንዲህ የተራራቁትን ያስተሳሰረ ማንም ሳይሆን ዶቅዶቄ ነው፡፡ ፊልትሮ፣ ፍሬንሸራ፣ የሞተር ዘይት፣ ፍሬን ዘይት፣ በአንድ ስልክ ጥሪ ብቻ በደቂቃ ጋራዥ መድረስ ችለዋል፡፡ እድሜ ለቦዳቦዳ!! ለአገልግሎታቸው ታዲያ ቢበዛ 50 ብር እንደው ቢበዛ 100 ብር ቢጠይቁ ነው፡፡
ዉድ የዋዜማ ሰዎች!
በመንገድ መቆላለፍ ስንት ትዳር ፈረሰ? በታክሲ እጦት ስንት አፍላ ፍቅር ደፈረሰ፣ በአንጀት የታክሲ ሰልፍ ስንት ሀሞት ፈሰሰ!!
መላ ተገኝቷል፡፡ በንፋስ ፍጥነት ፍቅረኛ ዘንድ የምታደርስ ቦዳቦዳ አገር ዉስጥ ገብታለች፡፡ ከተደወለላት የዘገየን ፍቅረኛ እንደፓስታ ከተዝለገለገ የታክሲ ሰልፍ ፈልፍላ አውጥታ በፍጥነት የቀጠሮ ቦታ ታደርሳለች፡፡
ለአምቡላንሱም፣ ለጋራዡም፣ ለፍቅር ቀጠሮም የዶቅዶቄ ሚና ከፍ እንዲል ያደረገው ደግሞ የሸገር ቁልፍልፍ መንገድ ነው፡፡ ኢምፔሪያል፣ ጀርመን አደባባይ፣ ሚካኤል አደባባይ፣ ጀሞ አደባባይ፣ ጃክሮስ አደባባይ እንደ ፖለቲካችን ተቆላልፈዋል፡፡ ቦዳቦዳዎች ብቻ ነው ቁልፍልፉን የሚፈቱት፡፡ የትራፊክ መብራት አይበግራቸውም፡፡ ቀይ ሲበራ ከተፈናጠጡበት ወርደው ዶቅዶቀያቸውን እየገፉ ይሻገራሉ፡፡ ያውም ትራፊክ ካለ ነው ይህን የሚያደርጉት፡፡ ከሌለ መብራት ይጥሳሉ፡፡ ደግሞ መንግሥት በሌለበት አገር! እንኳን መብራት ሕገ መንግሥትስ ይጣስ የለ?
ዉድ የጦማሬ እድምተኞች!
ባጃጅ የገጠር ታክሲን ከሥራ ዉጭ እንዳደረገው፣ ቦዳቦዳ ላዳን ያሽቀነጥረዋል ባይ ነኝ፡፡ ጀሞ አካባቢ ብዙ ቤተሰብ ልጆቹን ኬጂ የሚያመላልሰው በቦዳቦዳ ነው ሲሉኘ አላመንኩም ነበር፡፡ ለካንስ በየሰፈሩ ቦዳቦዳ ስኩል ባስን ተክቷል፡፡
የዶቅዶቄ ባለቤቶች ብዙዎቹ አንድ ጊዜ አገልግሎት ለሰጡት ሰው ከመልስ ጋር ደማቅ ቢዝነስ ካርድ ይሰጡታል፡፡ ቢዝነስ ካርዱ ላይ የሞተር ሳይክል ፎቶ አይጠፋም፡፡ አንድ አረፍተ ነገርም አትጠፋም፤ “ለማንኛውም አይነት የትራንስፖርት አገልግሎት ይደውሉ” የምትል፡፡ “ለማንኛውም” ተሰምሮበታል፡፡
የተሰመረበት ቃል ምን ማለት መሰላችሁ? ቁምሳጥንም ቢሆን በሞተር እንጭናለን ማለታቸው ነው፡፡ ልጃገረድ ከመጥለፍ ጀምሮ ሕጋዊ ሰርግ እስከማጀብ አገልግሎት እንሰጣለን ማለታቸው ነው፡፡ የሽቦ አልጋ ከነፍራሹ እንሸከማለን እያሉ ነው፡፡ አሁን አሁን ሞተር ሳይክል ያላጀበው ሰርግ ጠጅ ያልተጣለበት ሰርግ እንደማለት ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ የሚሰማሩ ሞተረኞች ግን ምሩቃን ሳይሆኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ብቻ ናቸው፡፡
አንድ እግርን ሞተር ላይ አድርጎ፣ የተቀረነው አየር ላይ አንሳፎ መሪ ሳይዙ ለመንዳት በሚደረግ የሰርግ ትርኢት ስንቱ ሞተረኛ የፊት ጥርሱን አጣ፡፡ ይህ ሁሉ ቅብጠት ታዲያ ሙሽራና ሙሽሪት ቪዲዮ ላይ ታሪክ ጥሎ ለማለፍ ነው፡፡ ለዚህ አይነቱ አገልግሎት እስከ 3ሺ ብር ይጠየቃል አሉ፡፡
ማንኛውንም የትራንስፖርት አገልግሎት እንሰጣለን ማለት ምን ማለት ነው?
ከዕለታት አንድ ቀን በጎተራ ሳልፍ ለዚህ ጥያቄ መልስ አገኘሁ፡፡ ጎተራ ኮንዶሚንየም አንድ ሞተረኛ በዳንቴል የተሸፈነች አንድ 14 ኢንች ቴሌቪዥን በሆዱ ይዞ ወንደላጤዉን ተሳፋሪ ከነመሶቡና ቡታጋዙ አፈናጦ በሞተር ወደ ዉስጥ ይዞት ሲገባ ባይኔ በብረቱ አየሁ፡፡ ለማጠቃለል ያህል ቦዳቦዳዎች ማንኛውንም የደረቅ ጭነት አገልግሎትም ይሰጣሉ፡፡
የፈሳሽስ ቢሆን!!! ዉሀ በማይዳረስባቸው የገላን ኮንዶሚንየሞች ቢጫውን ጄሪካን እንደኩላሊት ግራና ቀኝ ሽንጣቸው ላይ አዝለው ዉሀ የሚያመላልሱት ሞተሮች አይደሉምን?

ዉድ የዋዜማ ሰዎች!
አይሱዙዎች አልቃኢዳ፣ ሲኖትራኮች ቀይሽብር እንደሚባሉቱ ቦዳቦዳዎች “የእጅ ቦንብ” የሚል ቅጽል እንደወጣላቸው ነግሬያችሁ ይሆን? ለምን ነው እንዲያ መባላቸው ብል ነዳጅ መስጫው በእጃቸው ስለሚገኝ ነው አሉኝ፡፡ አንዳንድ ሰፈር ደግሞ “አጥፍቶ ጠፊዎች” ይሏቸዋል፡፡ ለምን ነው እንዲህ መባላቸው ብል የገጩት ከመሞቱ በፊት ጋላቢዎቹ ራሳቸው ቀድመው ስለሚሞቱ ነው ተባልኩ፡፡ እውነት ነው፡፡ የሞተረኛ አሟሟት ምኑም አያምርም፡፡
መልካሙ ዜና ብዙዎቹ ሔልሜት ሳያጠልቁ አይነዱም፡፡ ምሩቃን ስለሆኑ ይሆናል፡፡ የሕንድ ሙዚቃ ነፍሳቸው ነው ታዲያ፡፡ እንደ ሕንድ የተማረ ዜጋ ግሽበት በመፈጠሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁሉም ፍላሽ የሚቀበሉ ቴፖች አሏቸው፡፡ ሁሉም ፓርላማ ድረስ የሚያሰማ ስፒከር ያስገጥማሉ፡፡ ሙዚቃ ዝቅ አድርገው መክፈት አይወዱም፡፡ ሲጋልቡም ሲያዘፍኑም ጮክ አድርገው ነው፡፡ ኤፍ ኤም ከከፈቱ ስፖርት ዞን፣ ሸገር ስፖርት፣ አበበ ግደይ…ኦያያያ…ን ብቻ ነው፡፡ ቁም ነገር አይወዱም፡፡ ቁም ነገር ቁጭ ያደርጋል ይላሉ፡፡ ኮሌጅ በመበጠሳቸው ይበሳጫሉ፡፡ መማር ቁምነገር መስሎን…. ተሳሳትን ሲሉ ይብሰለሰላሉ፡፡
የሕንዱ ባላጂ ማኑፋክቸሪንግ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከመንገድ መዘጋጋት ጋር ተያይዞ የዶቅዶቄ ፍላጎት በየዓመቱ በ30 በመቶ እየጨመረ ስለሆነ ምርቴን አስፋፋለሁ ሲል ዝቶ ነበር፡፡ ከሆነ ዓመታት በፊት ለገጣፎ ለዶቅዶቄ ፋብሪካ 3ሺ ካሬ ቦታ ወስዷም ነበር፡፡ አሁን ፋብሪካው በሕይወት ይኑር አይኑር እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ኾኖም በርከት ያሉ የንግድ ድርጅቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዶቅዶቄ አስመጪ ሆነዋል፡፡ በዚህ ረገድ ጌቱ ተፈራ አስመጪን የሚያህለው የለም፡፡ በዓመት ብዙ ሺህ ዶቅዶቄ ኢትዮጵያ አስገብቶ ይቸረችራል፡፡ ምሩቃን ሥራ ሲያጡ አንድ ላምስት ኾነው ይገዙታል፡፡ እድሜ ለሪቮልቪንግ ፈንድ!
አሁን የባጃጅ ፍላጎት ተቀዛቅዞ ትኩሳቱ ወደ ቦዳቦዳ ተሸጋግሯል፡፡ ከዓመታት በፊት 45ሺ ብር ይሸጡ የነበሩ TVS Apache RTR ሕንድ ስሪት ቦዳቦዳዎች አሁን 73ሺ ብር ደርሰዋል፡፡ የጫት ቦዳቦዳዎች ወጪያቸውን በ12ወር ይመልሳሉ ተብያለሁ፡፡ መርቅነው አስልተውት ካልሆነ ይህ ትልቅ ገቢ ነው፡፡
መንገድ ትራንስፖርት አገሪቱ ዉስጥ ከ7መቶ ሺህ የሚልቁ ተሸከርካሪዎች ይገኛሉ ይላል፡፡ ቦዳቦዳዎችን ግን የቆጠራቸው አይመስልም፡፡ እነሱም ይታያሉ እንጂ አይዳሰሱ፡፡ ሞተር የተገጠመላቸው ዝንቦች! ሰላቢዎች!!!

[ሙሔ ሀዘን ጨርቆስ ለዋዜማ ራዲዮ]