- ጠቅላይ ሚንስትሩ ሀሞስ ፓርላማ ቀርበው በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሪፖርት ያቀርባሉ
- አቶ ተስፋዬ ዳባ ለአፈጉባኤነት የተሻለ ግምት ተሰጥቷቸዋል
ዋዜማ ራዲዮ- በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አካባቢ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኢህአዴግ አራቱ የፓርቲ አመራሮችም ሆነ ከመከላከያው አካባቢ ተሰሚነታቸው እየቀነሰ እየመጣ ነው፡፡
በተለይም ከህወሓት መንደር የሆኑ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እንዲሁም የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችና የደኅንነት ቁልፍ ሰዎች ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሮችን የማንበብና ፈጣን ዉሳኔን የመስጠት፣ እንዲሁም አዲስ ሐሳብ የማፍለቅ የአመራር ሰጪነት አቅማቸው በእጅጉ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የሚወጡ ደብዳቤዎች ከሠራዊቱ አመራሮች በአስፈላጊው ፍጥነት ምላሽ አያገኙም፤ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በቤተመንግሥት እንዲገኙ ጥሪ ተደርጎላቸው በቀጠሯቸው ሰዓት ወደ ቤተመንግሥት የማይመጡበት አጋጣሚ ተከስቶ ያውቃል፡፡ አንዳንድ ከፍተኛ መኮንኖችም ለፀጥታ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ለሁነኛ ስብሰባ ሲጠሩ ዝቅ ያሉ መኮንኖችን በተወካይነት ይልካሉ፡፡ ይህም የሚያሳየው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተሰሚነታቸው እየተሸረሸረ መሆኑን ነው ይላሉ ምንጮች፡፡
አዲስ አፈ ጉባዔ
አገሪቱ ፖለቲካዊ ፈተና ላይ በወደቀችበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እንኳ ወደ ሚዲያ ለመምጣት ያልደፈሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከነገ በስቲያ ሐሙስ በሚቀመጠው ሸንጎ ይታደማሉ፣ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ይሰጣሉ፣ የመንግሥታቸውን አቋምም ያስረዳሉ ፡፡
በሳምንት ሁለት ጊዜ ማክሰኞ እና ሐሙስ በመደበኛነት የሚታደመው የተወካዮች ምክር ቤት ሸንጎ መስከረም 29 ሲከፈት በዋዜማው የሥራ መልቀቂያ ያስገቡት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ መርተውት ነበር፡፡
በሐሙሱ የምክር ቤቱ ሸንጎ የተያዙ አጀንዳዎች ዘርዝር ምን እንደሆኑ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ባይሳካም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፕሬዝዳንቱ የተደመጠውን ንግግር የድጋፍ ሞሽን ያደምጣሉ፣ የምክር ቤቱ አባላቱ በሞሽኑ ላይ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ካሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ይሰጣሉ ተብሏል፡፡ ይህም ሞሽን ውይይት ከተደረገበት በኋላ በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀጽ 12 ንኡስ 12 መሠረት ይጸድቃል ተብሏል፡፡
የአዲስ አፈ ጉባኤ ምርጫ በዕለቱ ይካሄድ አይካሄድ የታወቀ ነገር ባይኖርም ለምክር ቤቱ ቅርብ ነን የሚሉ ምንጮች ግን በቀጣይ ቀናት የምክር ቤቱ ስብሰባ የሚቀጥል ከሆነና የአቶ አባዱላ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ በምክር ቤቱ ተቀባይነት ካገኘ እርሳቸውን የሚተኳቸው ሰው የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ዳባ እንደሚሆኑ ይገምታሉ፡፡ አቶ ተስፋዬ በምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው፡፡