Teddy Afroዋዜማ ራዲዮ- ለኢትዮዽያ ቴሌቭዥን ያልተጠበቀ መዘዝ ይዞ የመጣው የቴዲ አፍሮ ጉዳይ የኢቢሲ የማኔጅመንት አካል ራስ ምታት ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ዋዜማ ከድርጅቱ ነባር ጋዜጠኞች ባገኘቸው መረጃ የቴዲ አፍሮ ቃለመጠይቅን በተመለከተ ሐሙስ ዕለት ሦስት ሰዓታትን የፈጀ ዘለግ ያለ ዝግ ስብሰባ መካሄዱንና ስብሰባው በጣቢያው ምክትል ሥራ አስፈጻሚው መመራቱን፣ በስብሰባውም ሂስና ግለ ሂስ መካሄዱን ምንጮች አመልክተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ዉሳኔ ለመስጠት ማኔጅመንቱ ከጣቢያው ሥራ አስፈጻሚ ከአቶ ስዩም መኮንን ዘንድ ሌላ ቀጠሮ ይዟል፡፡ ይህን ዘገባ እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ ድርጅቱ ከአንዳች ውሳኔ ለመድረስ ሳይችል ቆይቷል።
በስብሰባው ላይ ወደዚህ ዉዝግብ ጣቢያው እንዴት ራሱን ሊከት ቻለ? የሚለው አጽእኖት ተሰጥቶ ዉይይት ተካሄዶበታል፡፡ የመዝናኛ ክፍል ኃላፊውም ነገሩ ከታሰበው በላይ መስመር ስቶ ሊራገብ የቻለው በማኅበራዊ ሚዲያው አማካኝነት እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡ ‹‹እኛ መጀመርያዉንም ቀለል ያለ የ10 ደቂቃ ፕሮግራም የዘፋኙን ፕሮፋይል ለመስራት ነበር እቅዳችን፡፡ ነገሩን ያቀድነው ከአልበሙ መለቀቅ ቀደም ብሎ ነበር፣ ይህ ይመጣል ብለን በጭራሽ አላሰብንም›› ሲሉ ይቅርታ መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡ [የድምፅ ዘገባው ከታች ተያይዟል]
ኢቢሲ በመዝናኛው ዘርፍ 24 ጋዜጠኞችን ይዞ የሚሠራ ሲሆን ከነዚህ ዉስጥ 13ቱ በእሑድ መዝናኛ የሚሰሩ ናቸው፡፡ እሑድ መዝናኛን ጨምሮ አርሂቡና የጥበብ ዳሰሳ የተሰኙ ፕሮግራሞች በመዝናኛ ዘርፍ ከሚካተቱ መርሀግብሮች መካከል ዋንኞቹ ናቸው፡፡ የዚህ ፕሮግራም የቅርብ አለቃ አቶ አሰፋ ሲሆኑ ለፕሮግራሞቹ ጥቅል ይዘት የድርጅቱ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ክትትል አይለየውም፡፡
የጣቢያው ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቤል አዳሙ በበኩላቸው ‹‹ቃለ መጠይቁ እንዲፈቀድ የተጠየቅኩበት ሁኔታ ጥድፊያ የበዛበትና ሁኔታውን ለማገናዘብ የተመቸ ስላልነበረ ስህተት ሰርቻለሁ›› ሲሉ ግለ ሂስ ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡
“የከፍተኛ ማኔጅመነት ስብሰባ ላይ ነበርኩ፡፡ ከስብሰባው ጠርተው ቴዲ አፍሮ ለኢንተርቪው ፍቃደኛ ሆኗል፣ በ30 ደቂቃ ዉስጥ አሁኑኑ ድረሱ ብሎናል‹‹ አሉኝ፣ አጣዳፊ ስብሰባ ላይ ስለነበርኩ ብዙም ሳላገናዝብ ፈቀድኩላቸው” ሲሉ ከስተቱን አብራርተዋል ተብሏል፡፡
የቴዲ አፍሮን ፕሮፋይል የመሥራት ዝግጅት የተጀመረው አልበሙ ከመውጣቱ ቀደም ብሎ እንደነበረና ኾኖም ሙዚቀኛው ከአልበሙ በፊት ቃለመጠይቅ ለመስጠት በወቅቱ ፍቃደኛ እንዳልነበረ የተገለጸ ሲሆን በድምጻዊው ሥራ አስኪያጅ በአቶ ጌታቸው ማንጉዳይ አማካኝነት ሀሳቡን እንደቀየረ ለጉዳዩ ቅርብ ነን የሚሉ ምንጮች ይናገራሉ፡፡
ኾኖም ቴዲ አፍሮ ቃለመጠይቅ ሲደረግ አቶ ጌታቸው ማንጉዳይ ምንም አይነት ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎች እንዳይቀርቡለት፣ እርሱም ከግል ሕይወቱ ጋር በተያያዘ ምላሽ እንዳይሰጥ በቀረጻ መሐል ጣልቃ እየገቡ ጭምር ያስቆሙ እንደነበረና ቃለ ምልልሱ በአልበሙ ዙርያ ብቻ እንዲያጠነጥን ይቆጣጠሩ እንደነበር በቦታው የነበሩ ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡
ከኢቢሲ የመዝናኛ ክፍል ለቴዲ አፍሮ ሥራ አስኪጅ ለአቶ ጌታቸውን ማንጉዳይ ስልክ የተደወለላቸው ከወራት ቀደም ብሎ እንደነበረ ስሟ እንዲገለጽ ያልፈለገች አንድ የመዝናኛ ክፍሉ ባልደረባ ትናገራለች፡፡
ኾኖም እርሳቸው በኢቢሲ ፍጹም ደስተኛ እንዳልሆኑ በወቅቱ መግለጻቸውንም ታስታውሳለች፡፡ በተለይም አድዋ ከተሰኘው የጂጂ ሙዚቃ ጋር በተያያዘ ‹‹እናንተ የልጁን ሙዚቃ ክሊፕ እየሰረቃችሁ በሌላ ሰው ዘፈን አጅባችሁ ማቅረባችሁ መልካም አይደለም›› ሲሉ በወቅቱ ወቀሳ እንዳቀረቡ አብራርታለች፡፡ ያም ሆኖ አልበሙ ሲለቀቅ ሙዚቀኛው ቃለ ምልልስ ለመስጠት ፍላጎት ካሳየ ቅድሚያ እሰጣችኋለሁ የሚል ቃል እንደሰጧቸው ባልደረባዋ ጨምራ አብራርታለች፡፡
ጋዜጠኛዋ እንደምትለው የአልበሙን መለቀቅ ተከትሎ ከቴዲ ሥራ አስኪያጅ ድንገት ወደ መዝናኛ ክፍል ስልክ መደወሉንና ቴዲን ማቅረብ ከፈለግን ያንኑ ዕለት እስከ 5‹30 ድረስ ለገጣፎ ቴዲ አፍሮ መኖርያ ቤት በፍጥነት መድረስ እንዳለብን እንደተነገረ ገልጻለች፡፡
በወቅቱ ምንም ሥራ ካልነበራቸው የመዝናኛ ክፍሎ ጋዜጠኞች መካከል ጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለና ሌላ አንዲት ሴት ጋዜጠኛ ከካሜራ ባለሞያዎች ጋር በመሆን በጥድፊያ መንገድ መጀመራቸውንና ኾኖም ያን ከማድረጋቸው በፊት ምክትል ሥራ አስፈጻሚውን ከስብሰባ መሐል አስጠርተው ‹‹ቴዲ በ30 ደቂቃ ዉስጥ ቤት ድረሱ›› እንዳላቸው መናገራቸውን አብራርታለች፡፡
በወቅቱ ነገሩን በፖለቲካ ዐይን የተመለከተው አንድም ኃላፊ አልነበረም፤ የመዝናኛ ኃላፊውም ሆነ ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ነገሩን አቅልለው ነበር የተመለከቱት የሚለው ሌላው የጣቢያው ሠራተኛ ማኅበራዊ ሚዲያው ያስነሳው አቧራ የበላይ አለቆችን አስቆጥቶ ፕሮግራሙ እንዳይተላለፍ ሳያደርግ እንዳልቀረ ይናገራል፡፡
የመዝናኛ ክፍል ባልደረባና ያለፉትን አራት አመታት በድርጅቱ ያገለገለው ጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለ ከቴዲ አፍሮ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደይተላለፍ መከልከሉን ተከትሎ ስራ መልቀቂያ ማቅረቡን ተናግሯል።
በሐሙሱ ስብሰባ ግን ለጣቢያው ስም መጉደፍ ምክንያት ሆነዋል ተብለው በአመራሮችና ከተወነጀሉ ጋዜጠኞች መካከል ሥራ መልቀቂያ ያስገባው ወጣት ብሩክ እንዳለ ሳይኖርበት እንዳልቀረ ይገመታል፡፡
የቃለ ምልልሱ ለጊዜውም ቢኾን እንዳይተላለፍ እግድ ከወጣበት በኋላ ጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለ ለሙዚቀኛው ስልክ በመደወል ለተፈጠረው ነገር በግሉ ይቅርታ እንደጠየቀና ቴዎድሮስ በበኩሉ ጋዜጠኛው ራሱን ችግር ዉስጥ እንዳያስገባና ደህንነቱን እንዲጠብቅ እንዳበረታታው ባልደረቦቹ ነን የሚሉ የጣቢያው ሠራተኞች ለዋዜማ መስክረዋል፡፡
የጣቢያው ባልደረቦች እንደሚገምቱት ቃለ ምልልሱ እንዲካሄድ የፈቀዱት የጣቢያው ምክትል ሥራ አስፈጻሚ በቀጣይ ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚችል የሚጠበቅ ሲሆን ጉዳዩን ከጣቢያው ሥራ አስፈጻሚ አልፎ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩን ትኩረት እንደሳበ ተመልክቷል፡፡
‹‹ የሚገርምህ ሁለቱም የጣቢያው ኃላፊዎች ነገሩ ወደ ፖለቲካዊ አውድ መቀየሩ ያስደነገጣቸውና ይህን ተከትሎ ከበላይ አለቆች የሚመጣውን ቁጣ ለመቋቋም የሚጸልዩ እንጂ በራሳቸው አንዳችም ነገር መወሰን የሚያስችል ስልጣን የላቸውም›› ይላል ዘለግ ላለ ጊዜ በጣቢያው የፕሮግራም አዘጋጅ ኾኖ የሰራ ባልደረባ፡፡
በኢቢሲ ዉስጥ ለ8 ዓመታት እንዳገለገለ የሚናገር ሌላ ጋዜጠኛ ‹‹ጣቢያው የቴዲን ቃለምልልስ ቢያስተላልፍ ምንም አያጣም፣ ምንም አያገኝም ነበር፡፡ ባለማስተላለፉ ግን ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ቀይ ስትራቴጂካዊ ስህተትን ሠርቷል›› ብሎ ያምናል፡፡
በቴዲ አፍሮ ቃለመጠይቅ ሳቢያ በህዝብ ፊት የተጋለጠው የቴሌቭዥን ድርጅቱ ስር የሰደደ ሳንሱር ብቻ ሳይሆን ከድርጅቱ ባሻገር በገዥው ፓርቲ ውስጥም የከፍተኛ ቁርቁስ መነሻ ሆኗል።
በኣማራ ክልል ከተነሳው ተቃውሞ በኋላ እንደነገሩ የሆነው የብአዴንና የህወሀት ሽኩቻ ላይ ተጨማሪ ቤንዚን ሆኖ መሰንበቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ነግረውናል። የህወሀት አመራሮች በዚህ ጉዳይ ጣልቃ ገብተው ማስፈራሪያም ጭምር አክለው ቃለምልልሱ እንዳይተላለፍ መከልከላቸውን ያነጋገርናቸው ሁሉ በአንድ ድምፅ ይስማማሉ።
“ነገሩ በአጋጣሚ የተፈጠረ ነው፣ አንድም ድርጅታዊ ጣልቃ ገብነት አልነበረውም። የህወሃት ጭፍን ወጣቶችና አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች ነገሩን ሌላ ገፅታ ስጥተው ሊያጠቁን መሞከራቸው አሳሳቢም አሳዛኝም ነው” ሲሉ ለመገናኛ ብዙሀን ቅርበት ያላቸው የብአዴን አመራር ነግረውናል።
“ኢትዮዽያ ተብሎ ሲዘፈን የመጀመሪያ አይደለም፣ ደሞስ ምን ችግር አለው?” ሲሉ ይጠይቃሉ አመራሩ።
“ከሁሉ የሚያሳፍረው ጉዳዩን በአግባቡ ተነጋግሮ ከመተማመን ይልቅ ተሽቀዳድመው ይቅርታ የጠየቁ የቴሌቭዥን ጣቢያው አመራሮች ናቸው” ሲሉ ያክሉበታል።
“በሚዲያ ተቋሙ ላይ ብአዴን ሳይሆን ህወሀት ረጅም እጅ እንዳለው አስይቶናል፣ አስፈራርቶናልም፣ ይህ ደግሞ ፍፁም ድርጅታዊ ምግባር አይደለም” ብለው እንደሚያምኑም እኚሁ ግለሰብ ያስረዳሉ።
የቴዲ አፍሮ ውዝግብ ከምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ጅምሮ ብዙዎችን ያሳተፈ ከመጋረጃ ጀርባ ሽኩቻ የደራበት እንደነበርም ከተለያዩ ስዎች ስምተናል።

https://youtu.be/yTP3I5lVl_A