ዋዜማ ራዲዮ- የኢፌዲሪ ርዕሰ ብሔር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከኢዮቤልዩ ብሔራዊ ቤተመንግሥት በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ዉስጥ እንዲለቁ ይደረጋል፡፡ አዲሱ መቀመጫቸው ስድስት ኪሎ መነን ከፍ ብሎ ሽሮ ሜዳ ከአሜሪካን ኤምባሲ አጎራባች የሚገኘው የቀድሞው የልዑል መኮንን ኃይለሥላሴ ግቢ ይሆናል፡፡
ላለፉት ሦስት ዓመታት በግንባታ ላይ የነበረው አዲሱ ቤተመንግሥት አሁን ላይ የማጠናቀቂያ ግንባታዎችና የማስዋቢያ ሥራዎች ብቻ ቀርተውታል፡፡ ዛምራ ለጠቅላላ ግንባታዉ 144 ሚሊዮን ብር ተስማምቶ ሥራውን ጀምሮ የነበረ ቢኾንም ከጊዜ በኋላ ለተጨማሪ የማስዋብያ ሥራዎችና ከግንባታ ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ከሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ እንዲጠይቅ ኾኗል፡፡ የፕሮጀክቱ አማካሪ አልትሜት ፕላን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሲኾን በስካሁኑ ሥራ የጠቅላላ ግንባታው 95 ከመቶ ተጠናቋል ተብሏል፡፡
በድንጋይ ከተሠራውና ከፍ ያለ የሥነ ሕንጻ ዉበት ከተላበሰው ዋናው ሕንጻ ጎን ሦስት ባለ ሁለት ወለል የእንግዳ ማረፊያ ቤቶች፣ ለሠራተኞች የሚኾኑ መቆያና ማብሰያ ቤቶች፣ ባለጥላ ኮሪደሮችና አንድ ተጨማሪ የአስተዳደር ሕንጻን የያዘው ይህ ፕሮጀክት ወጪው የተሸፈነው በኢፌዲሪ በቤተመንግሥት አስተዳደር ቢሮ ነው፡፡
አዲሱ ቤተመንግሥት በአንጻሩ ለርዕሰ ብሔሩ መቀመጫነት ከመታሰቡ በፊ የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት ኾኖ አገልግሏል፡፡ በወታደራዊው መንግሥት ወቅት ደግሞ የአብዮታዊ ኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር (አኢሴማ) ቢሮ እንደነበር ይነገራል፡፡
ከግዮን ሆቴል ጋር የሚጎራበተው የእዩቤልዩ ቤተመንግሥትን ወደ ሙሉ የሕዝብ ፓርክና ሙዝየምነት የመለወጥ እቅድ ተይዞለታል፡፡ ኾኖም የቤተመንግሥት አስተዳደራዊ የቢሮ ሥራዎች በዚያው ግቢ የሚከነወኑ ይኾናሉ ተብሏል፡፡ ለዚህ አገልግሎት የሚዉል ባለ 5 ወለል የአስተዳደር ሕንጻ በ60 ሚሊዮን ብር ወጭ ፍልዉሀ አቅጣጫ በሚገኘው የግቢው ክፍል እየተገነባ ይገኛል፡፡ ይህን ዉብና ማራኪ ግቢ አስተዳደራዊ አገልግሎት እየሰጠ ወደ ፓርክነት መለወጥ የተሻለ እንደሆነ ስለታነበት ነው አሁንም በግቢው ግንባታዎች እየተካሄዱ የሚገኙት፡፡ ግዮን ሆቴልን ለግል ባለሐብት በሽያጭ የማዘዋወሩ ሐሳብ ለረዥም ዓመታት እየተደናቀፈ ከቆየ በኋላ መንግሥት ሐሳቡን እርግፍ አድርጎ በመተው በፍልዉሀና ከብሔራዊ ቤተ መንግሥት ጋር በማቆራኘት ደረጃውን የጠበቀ የሕዝብ ፓርክ የሌላትን አዲስ አበባን ለመታደግ እየተሞከረ ነው፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ጉምሩክ የደረሱት የአዲሱ ቤተ መንግሥቱ የቤት እቃዎች ሙሉ በሙሉ የተገዙት ከስፔንና ጣሊያን ሲኾን ከፍተኛ ጥራት ያላቸውና የአገርን ገጽታ የማያበላሹ ናቸው ተብሏል፡፡ እቃዎቹ ምን ያህል ወጪ እንዳስወጡ ግን ማወቅ አልተቻለም፡፡
የታኅሳስ ግርግርን ተከትሎ ግንባታው ለ25ኛ ዓመት መታሰቢያ በመድረሱ በተለምዶ የእዩቤልዩ ቤተመንግሥት ተብሎ የሚጠራው ታችኛው ቤተ ቤተ ደርግ ብሔራዊ ቤተመንግሥት ሲል ሰይሞት ነበር፡፡ በቅጥሩ ትገኝ የነበረችው የደብረ ገነት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተክርስቲያን በንጉሡ ዘመን ለግል ጸሎት ማድረጊያነት ትውል እንደነበረ ሲነገር ከደርግ መምጣት ጋር ተያይዞ ግን እንድትዘጋ ኾና ቆይታለች፡፡ የመንግሥትና የኃይማኖት መለያየትን ተከትሎም ይህች አነስተኛ ቤተክርስቲያን የእቃ ማስቀመጫ ግምጃ ቤት ኾና ቆይታለች፡፡ ኾኖም በቀድመው ፕሬዚደንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የግል ፍቃድና በቀድመው ጳጳስ አቡነ ጳውሎስ ግፊት ይህች ቤተ ክርስቲያን ዳግም እንድትከፈትና አገልግሎት እንድትሰጥ ተደርጓል፡፡ ቤተ መንግሥቱ ወደ ፓርክነት ሲቀየር የቤተ ክርስቲያኗ እጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚለው እስካሁን አልለየለትም፡፡
የእዮቢልዩ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከአጼ ኃይለሥላሴ ጀምሮ የነበሩ ንጉሣዊ አልባሳትን፣ ከልዩ ልዩ አገራት የተበረከቱ ስጦታዎችን፣ የዱር እንሰሳት ማቆያ፣ ቤተ መጻሕፍትን እንዲሁም የትም የማይገኙ ታሪካዊ ቁሳቁሶችን የያዘ ሲሆን ለሙዝየምነት የሚያበቃ በቂ ክምችት እንደያዘ ይነገርለታል፡፡
የአሁኑ ርዕሰ ብሔር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የግል መኖርያቸው የሚገኘው ፈረንሳይ ቤላ ሲኾን ይህን መኖርያ ቤታቸውን በአሁኑ ሰዓት ለንግድ ባንክ አከራይተውት ይገኛሉ፡፡