- ክስተቱ በገቢ እቃዎች ዋጋ ላይ ጉልህ ተጽእኖ ሊፈጥር ይችላል
ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ ለገቢ ንግድ የሚቀርቡ የዉጭ ምንዛሬ ጥያቄዎችን የምታስተናግድበት አቅም ከጊዜ ወደጊዜ እየተመናመነ መምጣቱን ተከትሎ አስመጭ ነጋዴዎች ግብይት የሚያደርጉት ከጥቁር ገበያ በሚገዙት የውጭ ምንዛሪ ብቻ እየኾነነው፡፡ ይሁንና አገር ዉስጥ ከጥቁር ገበያ የተገዛን የውጭ ምንዛሪ ከአገር ይዞ መውጣት ከባድ ወንጀል በመሆኑ ከፍ ያለ መጠን ያለው የዶለር ግዢ የሚካሄደው በአመዛኙ በጥቁር ገበያ የሀዋላ ቅብብሎሽ ነው፡፡
ከዚህም የተነሳ አሁን አሁን ማንኛውንም የገቢ ንግድ ለማካሄድ በሀዋላ ቅብብሎሽ የሚገኝ የዉጭ ምንዛሬ ጉልህ ድርሻ እየያዘ መጥቷል፡፡ የነጋዴው ማኅበረሰብ ሁነኛ የዶላር ምንጭም ይኸው ስልት ብቻ እየኾነ ነው ይላሉ ታዛቢዎች፡፡የጥቁር ገበያ ሀዋላ ቅብብሎሽ ግብይት የሚፈጸመው በዋናነት ዱባይ፣ ቱርክና ቻይና ተቀማጭነታቸውን ባደረጉ ኢትዮጵያዊያን ባለሐብቶች ምክንያት ገንዘብ በጥሬ ብር አገር ውስጥ ላሉ ወኪሎቻቸው እየተሰጠ በምትኩ ተመጣጣኙንየውጭ ምንዛሬ ለአስመጪው በዉጭ አገር በዶላር እንዲከፈል በማድረግ ነው፡፡
ከሰሞኑ ከፍተኛ ጭማሪ አሳየ የተባለውም ለዚሁ ሕገወጥ ግብይት ማስፈጸሚያ የሚከፈለውና በዶላር የሚሰላው የኮሚሽን መጠን ነው፡፡ ይኸው የኮሚሽን መጠን ከሰሞኑ በአንድ ዶላር የሦስት ብር ጭማሪ ማሳየቱ ለአስመጪ ነጋዴዎችስጋት ፈጥሯል።
ምንም እንኳ ይህ የውጭ ምንዛሪን በሀዋላ የመቀባበል ሥርዓት በሕጋዊ መንገድ የውጭ ምንዛሪ የማግኘቱ ጉዳይ አስቸጋሪ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ለረዥም ጊዜ በአስመጪ ነጋዴዎች ዘንድ ሲሠራበት የቆየ ኢመደበኛ ሥርዓት ቢሆንምለአገልግሎቱ ይከፈል የነበረው ዋጋ ይህን ያህል የተጋነነ አልነበረም፡፡ ይህ ክፍያ ዶላር አገር ዉስጥ በጥቁር ገበያ ከሚገዛበት ዋጋ አንጻር ሲታይም ብዙ መራራቅ አልነበረውም፡፡ አሁን ግን በቅብብሎሹ ሰንሰለት የአንድ ዶላር ዋጋ ከአንድ ወርበፊት ከነበረበት የ24 ብር ተመን በአንድ ጊዜ ወደ 27 ብር አድጓል፡፡
ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ወቅት ኢትዮጵያ ዉስጥ በጥቁር ገበያ አንድ ዶላር የመሚገዛበት ዋጋ 26.20 ሳንቲም ደርሷል፡፡ በአንጻሩ አንድ ዶላር ከባንክ የሚገዛበት ተመን 22 ብር ከ20 ሳንቲም ብቻ ነው፡፡ ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሪውን ከሐዋላአቀባባዮች ሲቀበሉ ግን አንድ ዶላር የሚመነዘረው በ27.07 ብር ነው፡፡ አስመጪዎች ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በ24 እና በ25 ብር ገደማ ይገዙት የነበረው ዶላር አሁን በአንድ ጊዜ አስደንጋጭ ጭማሪ በማሳየት ከመደበኛው የዶላር ዋጋ 4. 87ብር ልዩነት አሳይቷል፡፡ ይህ አሀዝ ዶላር ከብር ጋር ያለውን እውነተኛ የለውጥ ተመን የሚያመላክት ነው ይላሉ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ታዛቢዎች፡፡
አስመጪ ነጋዴዎች በሕጋዊ መንገድ ከባንኮች የሚፈቀድላቸው የዶላር መጠን ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ እየቀነሰ መጥቶ አሁን ጨርሶውኑ የለም በሚባልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የዶላርን ተፈላጊነት በሀዋላ ገበያበእጅጉ ሳያንረው አልቀረም፡፡ አሁን የታየው ጭማሪም ምናልባት የዚህ ክስተት ተያያዥ ዉጤት ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል፡፡
በዚህ ወቅት ይቅርና ወትሮም ዶላር በተሻለ ፍጥነትና መጠን ከባንኮች በሚገኝበት ዘመን ወደ ሀዋላ ቅብብሎሽ ዘዴ መሄድ የተለመደ እንደነበር የሚናገሩ ነጋዴዎች ባንኮች ዶላር መስጠት በማቆማቸው የጥቁር ገበያው ዋጋ ከዚህም በላይ እንዳይንር ስጋት ገብቷቸዋል፡፡ ብዙዉን ጊዜ ነጋዴዎች ወደ ሐዋላ ጥቁር ገበያ ፊታቸውን የሚያዞሩት ዕቃ ለማስመጣት የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብ መጠን ከሕጋዊ ባንኮች መቶ በመቶ ተሟልቶ ስለማይሰጣቸው ነው፡፡
በአንጻሩ ከመንግስት ጋር ቅርርብ ያላቸው ጥቂት አስመጪዎች ወደ አገር ዉስጥ ለሚያስገቡት ዕቃ ከብሔራዊ ባንክ የዋስትና ሰነድ (Letter of Credit) በመክፈት ሲነግዱ ይታያል ፡፡ ኾኖም የሚያስመጡት ዕቃ የውጪ ምንዛሪውን ገበያ ከፍናዝቅ ከማድረጉም በላይ በልዩነቱ የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሬ በሕገወጥ መንገድ ከአገር እንዲወጣ በማድረግ ገንዘቡን ለጥቁር ገበያ የሐዋላ የዶላር ቅብብሎሽ ሲያውሉት ይታያል፡፡ ይህ የዉጭ ምንዛሬን ከአገር ማሸሽ (Capital Flight)ይበልጥ የሚስተዋለው አገሪቱ መረጋጋት በራቃት ጊዜ ከባለሥልጣናት ጋር እጅና ጓንት ኾነው በሚሰሩ ነጋዴዎች ዘንድ እንደሆነም ይታማል፡፡
ለዋዜማ ጥቆማቸውን የሰጡ መደበኛ አስመጪዎች እንደሚሉት ከዚህ ቀደም ወደ ሕገወጥ የሐዋላ ቅብብሎሽ የሚኬደው የጎደለ የዉጭ ምንዛሬ ለማሟላት ብቻ ስለነበር እንደአሁኑ የተጋነነ ፍላጎት ሳይከሰት ቆይቷል፡፡ ለአገልግሎቱየሚጠየቀው መጠንም እንደአሁኑ ከፍ ያለ አልነበረም፡፡ አሁን በአንድ ጊዜ ከፍ ያለ የዶላር መጠን ከብዙ ነጋዴዎች ወደ ሀዋላ አቀባባዮች ዘንድ መቅረቡ የኮሚሽን ንረቱ እንዲፈጠር ምክንያት እንደሆነ ይገምታሉ፡፡
ዋዜማ በስልክ ያነጋገረቻቸው አገር ቤት የሚገኙ የአስተላላፊ ወኪሎች ጭማሪው ለምን እንደተከሰተ የተሟላና አጥጋቢ ምላሽ ለመስጠት ተቸግረዋል፡፡ ከፊሎቹ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ የተፈጠረ ጊዜያዊ ችግር እንደሆነና ፖለቲካዊ መረጋጋት ሲፈጠር ስሌቱም አብሮ እንደሚረጋጋ ይገምታሉ በአንጻሩ ገንዘባቸውን እያሸሹ ያሉ ባለሐብቶች በመበርከታቸው የተፈጠረ ችግር አድርገው የሚቆጥሩትም ነጋዴዎች አሉ። ነጋዴዎቹ እንደሚሉት ውጭ አገር የሚገኙ ዶላር አቀባባዮች በቁጥር ውስን በመሆናቸው በተመሳሳይ ወቅት በርካታ የውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎች ከአገር ቤት ሲጎርፉባቸው ፍላጎቱን ለሟሟላት ሲሳናቸው ይስተዋላል፡፡ ይህም የሚሆነው የአቀባባዮቹ አቅም ከሚፈለገው የውጭ ምንዛሪ መጠን ጋር ሲነጻጸር ውስን በመኾኑ ምክንያት እንደኾነ አስመጪዎቹ ይናገራሉ፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን የሰጠ አንድ የቡና ባንክ የምጣኔ ሀብት ባለሞያ በበኩሉ የኮሚሽን ንረቱ ምክንያት የዉጭ የሀዋላ አስተላላፊዎች የፍላቱን መጨመር ተከትሎ የሚፈጥሩት ጊዜያዊ ችግር እንደሆነ ይገምታል፡፡ እነሱ ዶላርለሚጠይቋቸው ነጋዴዎች የሚከፍሉት የዉጭ ምንዛሬ ባነሳቸው ቁጥር ትርፋቸውን በመቆለል ጥያቄዉን ለማስታገስ ይሞክራሉ የሚል ግምት አለው።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ ዉስጥ ማንኛውም አስመጪ እቃ የሚገዛው የተመን ቅናሽ (UnderInvoice) በማስደረግ ነው፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ገቢን ደብቆ የቀረጥ ተመንን ለማሳነስ ብቻ ሳይሆን የተጠየቀውን ያህል የዉጭምንዛሬ በተፈለገው ጊዜ ማግኘት ፈጽሞ ስለማይቻል ነው፡፡
“አንድ ኮንቴይነር ሙሉ ዕቃ በ10 ሺህ ዶላር አስመጣሁ ትላለህ፡፡ዕቃው ከመቶ ሺህ ዶላር በላይ እንደሚፈጅብህ ግን አንተም መንግሥትም ታውቃላችሁ፡፡ የተፈቀደልህ ዶላር 10ሺህ ብቻ እንደሆነ መንግሥት እያወቀ “ቀሪዉን ዶላር ከየትአምጥተህ ነው ይህን ሁሉ እቃ የገዛኸው? ብሎ አይጠይቅህም፡፡” ይላል ለዋዜማ አስተያየቱን የሰጠ አንድ የወረቀት አስመጪ፡፡
“ዞሮ ዞሮ መንግሥት እውነታውን እያወቀ የተደነገገውን የዋጋ ተመንን በማመሳከር ብቻ ገቢዎችና ጉምሩክ ይቀርጥኻል፡፡ ለእያንዳንዱ እቃ አነስተኛ የትርፍ ተመን አስቀምጦ ከዚያ በታች እንዳትሸጥ ይመክርሃል፡፡ በዚያ የትርፍ ምህዳርእንደማትሸጠው ግን አንተም መንግሥትም በልቦናችሁ ታውቃላችሁ፡፡” ሲል የድብብቆሹን ርቀት ያብራራል፡፡
“መንግሥት የዶላር እጥረት የለብኝም ይላል፡፡ እኔ የሕብረት ባንክ ተበዳሪ ነኝ፡፡ ለምንዛሬ ካመለከትኩ ስድስት ወር አልፎኛል፡፡ የጠየቅኩትን ዶላር ሩቡን እንኳ አልሰጡኝም፡፡ ተበዳሪ ምንዛሬ ወረፋ ላይ ቅድሚያ እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡ካልነገድኩና ነግጄ ካላተረፍኩ የተበደርኩትን መመለስ እንደማልችል ያውቃሉ፡፡ ዶላር የማይሰጡኝ ስለሌላቸው ነው፡፡ ዶላር ቢኖራቸው ከማንም በፊት ለኔ እንደሚሰጡኝ አውቃለሁ” ይላል ዋዜማ ያነጋገረችው ይኸው አስመጪ፡፡
የዶላር ሀዋላ ቅብብሎሹን በተመለከተ ሲያስረዳም “መቶ ሺህ ዶላር ለገቢ ንግድ የፈለገ ነጋዴ 10ሺህ ዶላር በሕጋዊ መንገድ ከባንክ ቢያገኝ የተቀረውን 90ሺ ዶላር ማግኘት የሚችለው ከሀዋላ አስተላላፊዎች ብቻ ነው” ይላል፡፡ “ለዚህ ነው በእምነት ላይ ብቻ ለተመሰረተ የገንዘብ ምንዛሬ ልዉዉጥ አገር ቤት በብር ከፍተኛ ኮሚሽን መክፈል የሚኖርበት” ካለ በኋላ እቃውን ለማስገባት ማግኘት ያለበትን 90ሺህ ዶላር ለማግኘት ከ ሦስት መቶ ሺህ ብር በላይ ለአስተላላፊዎችበኮሚሽን መልክ ለመክፈል እንደተገደደ ይዘረዝራል፡፡ ባንክ የጠየቅኩትን ምንዛሬ ቢያቀርብልኝ ኖሮ ይህን 3መቶ ሺህ ብር ማዳን እችል ነበር ይላል፡፡
የቡና ባንክ የምጣኔ ሀብት ባለሞያው በበኩሉ “ይህ የምትለው አይነት ጭማሪ በጥቁር ገበያ በእውን ተከስቶ ከሆነ ተጽእኖው በጊዜ ሂደት የሸቀጦች ዋጋ ላይ መታየት አለበት” ይላል፡፡ “ነጋዴዎች ይህን ወጪ የሚያካክሱት ትርፋቸውንበመቀነስ ሳይሆን በሸማቾች ላይ ዋጋ በመቆለል እንደሆነ አስረግጦ ከተናገረ በኋላ “ምናልባት ነገሮች ካልተሻሻሉ መንግሥት የዉጭን ንግድን ለማበረታታት ከዚህ ቀደም አድርጎት እንደነበረው ብር ከዶላር ጋር ያለውን ልዩነት ለማስፋትመገደዱ አይቀርም” ይላል፡፡
በርካታ የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች እንደሚያምኑት ኢመደበኛ የዉጭ ምንዛሬ ግብይቶች መስፋፋት የአንድን አገር ምጣኔ ሀብት አለመረጋጋት ሊጠቁም ይችላል፡፡ በተለይም በጥቁር ገበያና በመደበኛው የዉጭ ምንዛሬ ግብይት መካከልያለው ልዩነት እየተራራቀ መሄድ መልእክቱ ጥሩ ዜናን ይዞ የሚመጣ አይደለም፡፡
ለምሳሌ ጥቁር ገበያው ተጽእኖ እያየለ ሲመጣ የባንኮችን የገንዘብ ክምችት አደጋ ላይ ስለሚጥል አሳሳቢነቱን ያጎላዋል፡፡ ሰዎች የዉጭ ምንዛሬን ለማግኘት ባለው ኢመደበኛ መንገድ ሁሉ በመሄድ፣ የተጋነነ ክፍያ ጭምር በመፈጸም ዶላርንማሳደድ ይጀምራሉ፡፡ ይህን ለማድረግ በባንክ ያከማቹትን ገንዘብ ለማውጣት ይገደዳሉ፡፡ ይህም የባንኮችን ካዝና ያመናምናል፡፡ የባንኮች ጥሪት ሲመናመን ደግሞ የብድር አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ስለሚኖረው ኢንቨስትመንትንይጎዳል፡፡
የዉጭ ምንዛሬ ግብይቱ ወደ ጥቁር ገበያው እያመዘነ መሄድ ባንኮች ላይ የሚኖረው ተጽእኖው በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ወደ አገር ዉስጥ የሚገባ የዉጭ ምንዛሬ መደበኛውን መስመር ስለማይከተል ባንኮች ከዉጭ ምንዛሬ ሊያገኙት ይችልየነበረውን ጥቅም ይጎዳባቸዋል፡፡ እንደማሳያም ከዓመታት በፊት የግል ባንኮች ከሚያገኙት ትርፍ ከፍተኛውን እጅ ይይዝ የነበረው ከዉጭ ምንዛሬ ሽያጭ የሚገኝ ገቢ ነበር፡፡ ከሰሞኑ የትርፍ መጠናቸውን ይፋ ያደረጉ በርካታ የግል ባንኮችመረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ ገቢያቸው ካለፉት ዓመታት ቅናሽ ሊያሳይ የቻለው የቋሚ ወጪዎቻቸው መጨመርና የዉጭ ምንዛሬ ግብይት መቀዛቀዝ በመኖሩ ነው፡፡ ባንኮች ከጥቂት ዓመታት በፊት ለአክስዮን አባሎቻቸው ይከፍሉትየነበረው የትርፍ መጠን ከ40 በመቶ በላይ የነበረ ሲሆ አሁን ግን ወደ 27 በመቶ ወርዷል፡፡
ለዚህ አስደንጋጭ ነው ለተባለለት የዶላር የሐዋላ ቅብብሎሽ የኮሚሽን መጠን ማሻቀብ ከሰሞኑ በአገር ዉስጥ የጥቁር ገበያ ነጋዴዎች ላይ የተካሄደው ዘመቻ ሌላው ምክንያት እንደሆነ የሚጠረጥሩም አልጠፉም፡፡ የፌዴራል ፖሊስከሳምንታት በፊት ጥቁር ገበያ ላይ ተሳትፎ እንዳላቸው በሚታመኑ ግለሰቦችና አካባቢዎች ላይ ድንገተኛ አሰሳ ማካሄዱ አይዘነጋም፡፡