- ቦታው ግማሽ ቢሊየን ብር የሚጠጋ ዋጋ አውጥቷል
ዋዜማ ራዲዮ- የሊዝ ክብረ ወሰን የሚለካው ለአንድ ካሬ በቀረበ ነጠላ ዋጋ ከሆነ በ15ኛው ዙር ኃይሌ ይርጋ የገበያ ማዕከል ጎን ለ240 ካሬ ቀርቦ የነበረውን ዋጋ የሚስተካከለው የለም፡፡ ያኔ ስኬት ኢንተርናሽናል የተባለ ድርጅት ለአንድ ካሬ 355ሺ 555 ብር ዋጋ አቅርቦ ነበር፡፡ ይህ ዋጋ ኪስ ቦታውን በ85 ሚሊዮን ብር ብቻ የራሱ እንዲያደርግ አስችሎት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ዛሬ ከሰዓት በኋላ (አርብ) ከወደ ማዘጋጃ ቤት የተሰማው ወሬ ግን ከዚህ ለየት የሚል ነው፡፡
የአዲስ አበባ ክብረወሰን ሆኖ ከቆየው የአንድ ካሬ ዋጋ በ55 ብር ብቻ ዝቅ የሚል ዋጋ ነው የቀረበው፡፡ ይህ ሁኔታ ላይ ላዩን ሲታይ የከተማዋ የሊዝ ክብረወሰን አልተሰበረም ብሎ ለመከራከር ያመች ይሆናል፡፡ የቦታው የካሬ ስፋት፣ የቦታው ድምር ዋጋና መስተዳደሩ ከቦታይ የሚያገኘው ቅድመ ክፍያ ሲሰላ ግን ዛሬ በሊዝ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ዉጤት ተመዝግቧል፡፡
አሜሪካን ግቢ ጃሊያ ትምህርት ቤት አካባቢ በኮድ ቁጥር LDR-AD.K-BUS-00012084 ለቀረበ 1380 ካሬ ስኩዌር ለሚሆን ቦታ ለአንድ ካሬ 355ሺ 500 ዋጋ መቅረቡ ተሰምቷል፡፡ ይህ ማለት የሊዝ ወለድ ግምት ዉስጥ ሳይገባ ግማሽ ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ቦታው ተሸጠ ማለት ነው፡፡
አሸናፊው ድርጅት ጋርደን ሪልስቴት የሚባል ሲሆን በማን ባለቤትነት እንደሚተዳደር የታወቀ ነገር የለም፡፡
ለዚህ ቦታ የቀረበው ሁለተኛ ዋጋ 352ሺ 333 ብር ሲሆን አቶ ሀይረዲን ኑር ከተባሉ ግለሰብ የተሰጠ ነጠላ ዋጋ ነው፡፡ ይህም በሊዝ ታሪክ 3ኛው ትልቁ ዋጋ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የዚህን ዙር ለየት የሚያደርገው፡፡ ለዚህ ቦታ የተሰጡት ዋጋዎች በሙሉ ከሁለት መቶ ሺ ብር በላይ መሆናቸው በስፋት እያነጋገረ ነው፡፡
እስከዛሬ በከተማዋ የሊዝ ጨረታ ታሪክ በርካታ ዉድ ዋጋዎች የቀረቡበት ይህ የ24ኛው ዙር ሲሆን ዛሬ ከረፋዱ ጀምሮ በአዲስ ከተማ ወረዳ 1 የቀረቡ ስድስት ቦታዎች፣ በቂርቆስ ወረዳ 6 የቀረቡ 2 ቦታዎች፣ እንዲሁም በልደታ ወረዳ 9እና 10 የቀረቡ 5 ቦታዎች ዉጠት ይፋ የሆነበት ነበር፡፡
አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ስሙ አሜሪካን ግቢ በሚባለው አካባቢ የቀረቡት ቦታዎች በቁጥር 6 ነበሩ፡፡ እነዚህ ቦታዎች የተገኙት በቅርቡ አካባው በልማት ምክንያት በመፍረሱ ነበር፡፡ በዚህ ሰፈር በቀረቡት በ6ቱም ቦታዎች የቀረቡ የማሸነፊያ ዋጋዎች እስከዛሬ በሊዝ ከቀረቡት ጋር ሲነጻጸር በዋጋ ዉድነት ከዉድ 10 ቦታዎች ዉስጥ የሚካተቱ ይሆናሉ፡፡
በኮድ ቁጥር LDR-AD.K-BUS-00012081 የቀረበና ስፋቱ 1038 ካሬ ስኩዌር የሆነ ቦታ ፌዛል ሪልስቴት 158ሺ 522 ብር በማቅረብ አሸንፏል፡፡ ሁለተኛ የሆኑት አቶ ሬድዋን ጀማል የተባሉ ባለሀብት ሲሆኑ ለአንድ ካሬ 154ሺ ብር አቅርበዋል፡፡
በኮድ ቁጥር LDR-AD.K-BUS-00012083 የተሰየመና ስፋቱ 376 ስኩዌር ካሬ ስኩዌር የሆነ ኪስ ቦታ አቶ አስቻለው ዓለሙ ነጋ የተባሉ ባለሀብት 150ሺ 500 ብር ለአንድ ካሬ በማቅረብ አሸናፊ ሲሆኑ አቶ አብዱል ሀፊዝ ሱልጣን የተባሉ ሌላ ባለሀብት 150ሺ ብር በማቅረብ በ500 ብር ብልጫ ተሸንፈው ሁለተኛ ሆነዋል፡፡
የዙሩ ሌላው ከፍተኛ ዋጋ የተመዘገበው በኮድ LDR-AD.K-BUS-00012085 የተሰየመና ስፋቱ 964 ስኩዌር ካሬ ለሆነ ቦታ የተሰጠ ዋጋ ሲሆን ኢንጀሮ ኢምፖርት የተባለ ድርጅት ለአንድ ካሬ 311ሺ 500 ብር በማቅረብ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ይህ ዋጋ በከተማው የሊዝ ታሪክ 3ኛው ትልቁ ዋጋ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ዛሬ አርብ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ ይፋ መደረግ የጀመሩት የሦስት ክፍለ ከተሞች የጨረታ ዉጤቶች አንድም ቦታ ከ50ሺ ብር በታች ዋጋ ሳይቀርብባቸው መጠናቀቃቸው ከእስከዛሬዎቹ ሁሉ ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡ በልደታ “ፍሊንስቶን ልደታ መርካቶ” ብሎ በሰየመው አዲስ የገበያ ማዕከል አቅራቢያ፣ በአፍሪካ ኅብረት የምስራቅ በር አቅራቢያ፣ በገነት ሆቴል ወደ ቄራ በሚወሰድው መንገድ የቀኝ አቅጣጫ፣ ጆኒ ሕንጻ ጎን፣ ከጠማማው ፎቅ አቅራቢያ፣ በልደታ ደሴ ሆቴል ፊት ለፊት ገባ ብሎ ቀርበው በነበሩ ሰፋፊ ይዞታዎች ለአብዛኛዎቹ የተሰጠው ዋጋ ከ80ሺ እስከ 195ሺ ብር ለአንድ ካሬ ነበር፡፡ ይህም ዙሩ ምን ያህል ዉድ ዋጋ የቀረበበት እንደነበር ማሳያ ነው፡፡
አገሪቱ ቀውስ ዉስጥ በነበረችበት የ23ኛው ዙር የሊዝ ጨረታ በአመዛኙ መጠነኛ የዋጋ መረጋጋት ታይቶ እንደነበረና ከዚያም አልፎ ተጫራች ያጡ ቦታዎች ጭምር መመዝገባቸው አይዘነጋም፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በከተማዋ አንጻራዊ መረጋጋት በመስፈኑ ይመስላል የሊዝ ዋጋ ወደነበረበት ንረት ተመልሷል፡፡
የዙሩ አሸናፊዎች ስማቸው በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ በተገለጸ በአስር ቀናት ዉስጥ ቀርበው ያሸነፉበትን ዋጋ 20 በመቶ በሲፒኦ ገቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን ማሟላት ካልቻሉ ግን ሁለተኛ የወጣው ተወዳዳሪ አንደኛ በወጣው ተወዳዳሪ ዋጋ ቦታውን እንዲወስደው ይጋበዛል፡፡
በ11ኛው ዙር የሊዝ ጨረታ መርካቶ በተለምዶ በርበሬ ተራ ከስታር ቢዝነስ ግሩፕ መጋዘን ጎን የሚገኝ ኪስ ቦታ የወቅቱ ክብረወሰን የተባለለት ዋጋ ቀርቦበት ነበር፡፡ ለአንድ ካሬ 305ሺ ብር አቅርበው የነበሩት የዝዋይ ኢንተርናሽናል ግሩፕ ባለአክሲዮኖች የተሰጠው ዋጋ እጅግ ዉድ ነው በሚል ቦታዉን ሳይረከቡት መቅረታቸው ይታወሳል፡፡ በድርጅቱ ባለአክስዮኖች ዘንድም ዉዝግብ ተፈጥሮ እንደነበር ፎርቹን የተባለ ሳምንታዊው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ በወቅቱ ዘግቦት ነበር፡፡ ፓልም ኢትዮጵያ፣ በሱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርና ነጻ ትሬዲንግ እንዲሁም የአልሳም ድርጅት ባለቤት የሆኑት የአቶ ሳቢር ሚስት ዝዋይ ኢንተርናሽናልን በባለቤትነት የመሰረቱ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
በዚህ ዙር ከፍተኛ ዋጋ ያቀረቡ ድርጅቶች የሚፈለግባቸውን ክፍያ ከፈጸሙ በኋላ ቦታውን ከከፍለከተማ ተረክበው በአንድ ዓመት ዉስጥ ግንባታ እንዲጀምሩ ይገደዳሉ፡፡ የሚገነቡት የወለል ከፍታም ከ19 ፎቅ መብለጥ አይኖርበትም፡፡