ጤና ይስጥልኝ ጌታዬ! የዋዜማ ራዲዮ ወዳጆች……ሌሎችም
ገረመው እባላለሁ፡፡ እሳት የላስኩ የፊንፊኔ ደላላ ነኝ፡፡ ምስጉን ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› ስለመሆኔ እግዜርም ሰይጣንም ያውቃሉ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ መሆኔን ድሪባም ኩማም ያውቃሉ፡፡ ዉሎ-አዳሬ ‹‹ብሔራዊ››፣ አመሻሼ ‹‹አብዮታዊ›› ሃሃ፣ ‹‹ላየን ባር›› ቤቴ፣ ‹‹ቴሌ ባር›› ግዛቴ፡፡
ጥሎብኝ አልረጋም፡፡ ካዛንቺስ ነው ሲሉኝ ሳሪስ፣ ቀበና ነው ሲሉኝ ባምቢስ…ሄሄሄ ደላላ ምን ቀልብ አለው ብለው ነው፤ጌታዬ!
ግን እንዴት ነዎት ባያሌው?
እርስዎም ጠንቅቀው እንደሚያውቁት ደንበኞቼ መልከ ብዙ ናቸው፡፡ እኔ ግን በጥቅሉ በሁለት ከፍዬ አያቸዋለሁ፡፡ ከርቸሌ የወረዱና ከርቸሌ ያልወረዱ፡፡
ብዙዎቹ ከርቸሌ የወረዱ ደንበኞቼ በዚህ ወቅት ጤና እየራቃቸው ስለመጣ ያሳዝኑኛል፡፡ ስለዚህ በቻልኩት አቅም ሁሉ እየሄድኩ እጠይቃቸዋለሁ፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም እኔን ሲያዩ ዐይናቸው ይበራል፡፡
‹‹ገረመው…አሁን አንተ እያለህ እኛ መታሰር ነበረብን?›› ይሉኛል፡፡ እንስቃለን፡፡
‹‹ገረመው…እንደው እሚፈቱን ይመስልሀል ግን?›› ይሉኛል፡፡ እተክዛለሁ፡፡
‹‹ገረመው! እባክህ ያን ሚኒስትር አንተ ትቀርበዋለህና ንገረው…ከቻልክ በጫወታ ጨወታ ዉለታዬን አንሳበት›› ይሉኛል፡፡ ቃል አገባለሁ፡፡
ብቻ አንጀቴን ነው የሚበሉት፡፡ ያን ሁሉ ሹም ቁጭ ብድግ ሲያስብሉ የነበሩ አሁን አንድ ዉሪ ወታደር ቁጭ ብድግ ሲያሰኛቸው ሳይ እንባዬ ይመጣል፡፡ አንዳንዶቹ ይነግዱ የነበሩት ከሚኒስትር ጋር አልያም ከሚኒስትር ቤተሰብ ጋር በዉስጥ ታዋቂ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ እንኳን ሊታሰሩ…የታሰረ የሚያስፈቱ ነበሩኮ፡፡ ምን ዋጋ አለው…ጊዜ ጣላቸው፡፡ ጊዜ ሲከዳ ደግሞ ርህራሄ የለውም፡፡
ነፍሳቸውን ይማርና እነ ጋሽ ገብረኪዳን በየነ (ሞሮኮ)፣ እነ አየለ ደበላ (አይኤምኤፍ) ሁልጊዜ እሁድ እሁድ ሳገኛቸው ‹‹ፀልይልን እስቲ ባክህ›› ይሉኝ ነበር፡፡ የሁልጊዜ ሕልማቸው በሕይወት ከከርቸሌ ወጥቶ አንድ መለኪያ ዉስኪ በነጻነት መጠጣት ነበር፡፡ አልተሳካም፡፡ ከታችኛው መንግሥት ፍርድ ወደ ላይኛው መንግሥት ፍርድ በድንገት ተሰናበቱ፡፡ በድጋሚ ነፍስ ይማር ብያለሁ!
ጓደኛሞቹ ከበደ ተሰራና ከተማ ከበደ (ኬኬ) ወዳጆቼ ነበሩ-አሁንም ናቸው በርግጥ፡፡ በአራት ኪሎና በብሔራዊ ቴአትር ጎዳና እንደገተሩት ሕንጻዎቻቸው እነርሱም ከርቸሌ በሰበሱ፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ከዛሬ ነገ እንፈታለን እያሉ ተስፋ ያደርጉ ነበር፡፡ አሁን አሁን ተስፋ መቁረጥ ጀምረዋል፡፡ መቼ ለታ ሳያቸው ጠቋቁረዋል፡፡ አንጀቴን በሉት፡፡ ስንቱን ሹም ሽንት በሽንት እንዳላረጉት ጊዜ ጣላቸው፡፡
እንደገባኝ እስር ቤት እንደ ጋሽ አያሌው አይነት የመንፈስ ጥንካሬን ይፈልጋል፡፡ ጋሽ አያሌው ተሰማ እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ እጅ አልሰጡም፡፡ ያን ሁሉ ሕዝብ ባለ መኖርያ ቤት አድርገው ሲያበቁ የእርሳቸው መኖርያ ቃሊቲ እንዲሆን በፍጹም አልፈቀዱም፡፡ ስለዚህ ለራሳቸው ጥብቅና ቆሙ፡፡
‹‹የአገሬን አይን ባበራሁ…›› ብለው ለፍርድ ቤት እንባ እየተናነቃቸው ለ2 ሰዓት ተኩል አወሩ፡፡ ተሳካላቸው፡፡ ፍርድ ቤት ነጻ ነዎት አላቸው፡፡ አሁን የሰላም አየር እየተነፈሱ፣ አያት ዞሮ መግቢያዬን እየቸበቸቡ ይኖራሉ፡፡
በአንጻሩ የእድሜ ባለፀጋው የካፒታል ሆቴሉ አለቃ አቦይ ገብረስላሴ በስተርጅና ቂሊንጦ ወርደው ይኖራሉ፡፡ አብሯቸው አንድ እስረኛ ጉድ ጉድ ሲል አየሁት፡፡ በሄዱበት ይሄዳል፡፡ ከጎናቸው ኩስ ኩስ ይላል፡፡ አስተናባሪያቸው ነው አሉኝ፡፡ ከእስረኞች አንዱን እዚያ በአገልጋይነት ቀጥረውታል ማለት ነው፡፡ ቁርስ፣ ምሳ፣ ዕራት የግል ንብረታቸው ከሆነው ከባለአምስት ኮከቡ ካፒታል ሆቴል እየመጣላቸው ይመገባሉ፡፡ አለቃ…ሲነሽጣቸው መላ እስረኛውን በሬ ጥለው ያበሉታል፡፡ ቁጡ ስለሆኑ ከኔ ጋር ብዙም ግብብት የለንም፡፡ የሩቅ ሰላምታ ብቻ! ልጃቸው የማነ ግን ነፍሴ ነው፡፡ ስንትና ስንት ብረት ያሻሻጥኩለት ባለዉለታው ነኝ፡፡ ሀብታም ሰው ይዘነጋል፡፡ እርሱ ግን ዘንግቶኝ አያውቅም፡፡ ቤቱ ጎራ ካልኩ ፈርሜ እንጂ ከፍዬ በልቼ አላውቅም፡፡
###
ጌታዬ!
አምላክ ሳይቸግረው ‹‹አውርተህ ብላ›› ብሎ የፈጠረኝ ዜጋ አይደሁ? ታዲያ ወፍራም ደላላ እንደመሆኔ ከርቸሌ ስለወረዱ ወፋፍራም ደምበኞቼ ባወሳ ምን ክፋት አለው?
አንድ ደንበኛዬ ከላይ ከዘረዘርኳቸው ሁሉ ይለያል፡፡ በገንዘብም፣ በአቅምም፣ በባህሪም፡፡
እኔ ‹‹ቀጭኑ ጌታ›› እያልኩ እጠራዋለሁ! እርሱ ገሬ ነፍሴ ይለኝ ነበር! ከመታሰሩ በፊት፡፡
‹‹ዬሐንስ ሲሳይ ሞላ›› ይባላል፡፡ አራት ዓመት አለፈው ከታሰረ፡፡ አሁን የፍርድ ቤት ቀጠሮው ተቃርቧል፡፡ ሰሞኑን ባገኘሁት የማያወላዳ መረጃ ይፈቱታል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ጆኒ ወዳጄ! ቅዱስ ዮሐንስ ካንተ ጋር ይሁን!
‹‹ጆኒ ደግሞ ማን ነው?›› ነው ያሉኝ ጌታዬ? ጆኒማ የቬኑሱ ነጋዴ ነዋ! ባለራዕዩ! ታላቁ…ዕውቁ…ምጡቁ የመርካቶ አራዳ! የፋብሪካው ጌታ! ጅንኑ…ቀጭኑ…
ከአንድ ከ3 ወር በፊት ይመስለኛል…ጆኒ ምን እንደተባለ ልንገርዎ፡፡ ያኔ ነው የርሱን አቅም የሚረዱት፡፡
የመብራት ክፈል ተባለ፡፡ ያውም የታሠረበት እስር ቤት ድረስ የኤልፓ ሂሳብ ሠራተኞች ሄደው ‹‹የመብራት ክፈል›› አሉት፡፡ ‹‹ስንት ቆጠረብኝ?›› አላቸው፡፡ 25 ሚሊዮን ብር አሉት፡፡ እውነቴን እኮ ነው፡፡ 25 ሚሊዮን ብር የመብራት ዉዝፍ ክፈል ተባለ፡፡ ከፈላቸው፡፡ አሃ ልክ ነዋ! ጆኒ ቀጭን ጌታ…ፋብሪካዋ ዉስጥ የራሷን ግልገል ጊቤ የተከለች ጉደኛ ናት እኮ፡፡ እርስዎ የመብራት በወር ስንት ነበር የሚከፍሉት?
ከ4 ዓመት በፊት ደግሞ ልክ በዛሬው ወር ይመስለኛል…ግብር ክፈል አሉት፡፡
‹‹የምን ግብር?››
‹‹ዓመታዊ ግብር››
‹‹እሺ ታዛዥ ነኝ! ስንት መጣብኝ?›› አላቸው፡፡
ለአንድ ቢሊዮን 2መቶ ሚሊዮን የጎደለው ሂሳብ አመጡበት፡፡ ስምንት መቶ ሚሊዮን ብር ማለት ነው፡፡ ግብር መሆኑ ነው፡፡ ደነገጠ፡፡ ጆኒ ለመጀመርያ ጊዜ ደነገጠ፡፡ እንዴት አይደንግጥ ጎበዝ! አንድ ዜጋ እንዴት አንድ ቢሊዮን ብር አምጣ ይባላል፡፡ ለካንስ ያኔ ነገር እየፈለጉት ነበር፡፡ ‹‹ዘቅዝቃችሁ ፈትሹኝ ዱዲ የለኝም›› አላቸው ዐይኑን በጨው አጥቦ፡፡ ቢሉት ቢሠሩት ወይ ፍንክች! ዘብጥያ ወረወሩት፡፡
###
ጌታዬ!
እርግጥ ነው ዮሐንስን የሚያህል ጀግና ነጋዴ በፊንፊኔ ምድር እንደሌለ በአስር ጣቴ እፈርማለሁ፡፡
ደግሞ ስወደው! ዮሐንስ ሲሳይ ሞላ ብዬ በሙሉ ስሙ ጠርቼው እንኳ አላውቅም እኮ፡፡ ‹‹ጆኒ ቀጭን ጌታዬ›› እያልኩ ነው የማንቆለጳጵሰው፡፡ እሱም እንደዚያው ነው፡፡ ያቀርበኛል፡፡ ሲቸግረኝ አንዳንድ ነገር ሸጎጥ ያደርግልኛል፡፡ ሳይበዛ ነው ታዲያ፡፡ ብዙም ጊዜ የለውም፡፡ ገንዘብ ቆጥሮ ለመስጠት የሚተርፍ ጊዜ የለውም፡፡ ስለዚህ ዘግኖ ነው የሚሰጠው፡፡ ሲለው ደግሞ ለስሙኒ ይከራከራል፡፡ ጆኒ እንደዚያ ነው፡፡ የማይጨበጥ!
ደግሞ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ፎቅም የለውም፡፡ ፎቅ ብቻም ሳይሆን ስጋም የለውም፡፡ አጥንት ነው፤ ንፋስ ነው፡፡ ረዥም ቀጫጫ፡፡ ደግሞ ይሰለባል፡፡ አሁን እዚህ ጋር አይተውት ዞር ሲሉ የለም፡፡ መርካቶ ዉስጥ በስም እንጂ በመልክ የሚያውቀው ስለሌለ እንደልቡ በእግሩ ምናለሽተራን፣ ጆንያ ተራን፣ ሰሀን ተራን ይዞራል፡፡ ራሱ ያመረተውን ዕቃ ተከራክሮ ይገዛል፡፡ ዋጋ ያጣራል፡፡ ጆኒ ቀጭን ጌታ! ጆኒ ነፍሴ!
እርሱ ከነጋዴዎች ሁሉ የላቀው ነው፡፡ ከመርካቶ ወጥቶ ‹‹የሱ›› የተባለ ቆርቆሮ ፋብሪካን ‹‹ሸበል›› በሚል ኩባንያ ስም በግማሽ ቢሊዮን ብር ገላን ላይ ሲያቋቁም ‹‹አበደ›› ያላለው አልነበረም፡፡ እኔ ራሱ ‹‹ተው›› ብዬዋለሁ፡፡ ሰው አይሰማም፡፡ ‹‹እሺ›› ይላል ግን ሰው አይሰማም፡፡ በሐሳቡ ገፋበት፡፡ ‹‹የሱ›› ፋብሪካ ምርት ሲጀምር ‹‹ደረጃ›› የሚባል በጥራቱ እዚህ ግባ የማይባል ቆርቆሮ ማምረት ጀመረ፡፡ ምድረ ዉሪ ደላላ ሁላ ‹‹ጆኒ ወደቀች-አበቃላት›› ሲል አሟረተ፡፡ እሱ በነገሩ ገፋበት፡፡ ደረጃ መዳቢም ዝም አለው፡፡ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉዳዩ በበድሩ አደም በኩል በፓርላማ ሲቀርብላቸው ‹‹እዚህ የግለሰብ ጉዳይ እያነሳን አንፈተፍትም›› ብለው የሕዝብ እንደራሴዎችን አሳቁ፡፡ ዉሪ የግል ጋዜጣ ሁላ ‹‹ኡ ኡ›› አለ፡፡ ቀጭኑን ጌታ ጆኒ ሲሳይ ሞላን ግን የመለሰው አልነበረም፡፡ ገለባ ቆርቆሮ ማምረት ጀመረ፡፡ ምርቱ እንደ ቆሎ መሸጥ ጀመረ፡፡ ዛር ቆመለት፡፡ ብር ሰገደለት፡፡ ያልተጣራ ዕለታዊ ትርፉ 1.5 ሚሊዮን ብር ደረሰ ተባለ፡፡ ልብ ይበሉ! የወር አላልኩም፡፡ የዕለት ትርፍ ነው የማወራው፡፡ የርስዎ የዕለት ገቢ ስንት ነበረ ጌታዬ?
ጆኒ ቀጭን ጌታን እኔና እኔን የመሰሉ ወፍራም የፊንፊ ደላሎች ካልሆንን ብዙ ሰው በመልክ እንኳ አያውቀውም፡፡ ቅጥነቱ የማራቶን ሯጭ እንጂ ነጋዴ አያስመስለውም፡፡ አለባበሱ ተመጽዋች እንጂ መጽዋች እንዳይመስል ረድቶታል፡፡ እሱ ግን ዋረን ቡፌት ነገር ነው፡፡ ሲመጸውት ዐይን የለውም፡፡ ጌታዬ! በመረጃ ነው የማወራዎ! ጆኒ ለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብቻ ስንት ብር እንደለገሰ ያውቃሉ? ካላወቁ ‹‹አላውቅም›› ይበሉ! 82 ሚሊዮን ብር፡፡ በሟቹ አቡነ ጳውሎስ በኩል ነበር ጥሬ ብሩን የላከው፡፡ በጆንያ አስጭኖ! አንድ ጊዜ የመጸወተው የገንዘብ መጠን ነው ታዲያ ይሄ፡፡ በየጊዜው ሸጎጥ የሚያደርግላቸውን ሊቀ መላዕክቱ ይቁጠሩት፡፡ በቀደም ለታ ፋይል ሳገላብጥ ሟቹ ፓትሪያርክ የጻፉለትን የምስጋና ደብዳቤ ቅጂ አገኘሁት፡፡ ‹‹ልጄ ዮሐንስ! እግዚአብሔር ከማይጎድለው ፀጋው አብዝቶ ይስጥህ›› ይላል፡፡
የፓትሪያርኩ ‹‹ምርቃት›› ደረሰ መሰለኝ ይኸው ቃሊቲ ወርዶም ንዋይ እንደመና ይዘንብለታል፡፡
ጆኒ የት ነው ያለው?
ጆኒ ቀጭን ጌታ ዛሬ መገኛው ቃሊት ነው፡፡ ከቂሊንጦ ወደ ቃሊት የተዛወረበት ታሪክ በራሱ ሌላ ጥራዝ ይወጠዋል፡፡ የዛሬ 4 ዓመት ግድም ቂሊንጦ ሳለ ልጠይቀው ሄጄ ነበር፡፡ እዛም ነግሷል፡፡ የእስረኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አርገው ሾመውታል፡፡ እዚያ አሳሪዎችም ታሳሪዎችም ይሰግዱለታል፡፡ ምን ቢያደርግ ነው ይህ ሁሉ ሽርጉድ ብለን ጠየቅን፡፡ ለቂሊንጦ 300 ሰው የሚይዝ አዳራሽ በራሱ ወጪ ሠርቶ አስረክቧል አሉን፡፡ ኃላፊዎች ወደዱት፡፡ ወደውት አላበቁም፡፡ በሳምንት 2 ቀናት ቢሮ በአጃቢ ሄዶ ሥራ እንዲሠራ በዛም በዚም ብለው አስፈቀዱለት፡፡ ጆኒ በዚህ አልረካም፡፡ ‹‹በየቀኑ በአጃቢ እየወጣሁ ማታ ማታ ብቻ ለአዳር ብመጣስ?›› አላቸው፡፡ ‹‹ይሄማ የማይሞከር ነው አቶ ዮሐንስ፣ እንኳን አንተ ገብረዋዕድም እንዲህ አላለ…›› አሉት፡፡ እንዲህ የሚሉት እኮ ደደቢት የታገሉ የእስር ቤቱ ከፍተኛ አስተዳዳሪዎች ናቸው፡፡
‹‹የማይሞከር ነውማ አትበሉኝ፣ ደርግን የጣላችሁ ሰዎች፣ መቀሌ እስር ቤት በአንድ ኦፕሬሽን ስንት ሺ እስረኛ ያስፈታችሁ ሰዎች እኔን አንድ ነፍስ ከዚህ ማውጣት እንዴት ይሳናችኋል?›› ብሎ አሳቃቸው፡፡ ከትከት ብለው ከልባቸው ሳቁ፡፡ ሳቃቸው ሲያባራ…
‹‹እስቲ የምንችለውን እንሞክራለን›› ብለውት ሄዱ፡፡
እርሱም ዝም አላለም፡፡ ለሦስቱም የእሥር ቤቱ አለቆች በየስማቸው አንድ አንድ ቤት፤ ለሚስቶቻቸው አንድ አንድ መኪና በምስጢር አበረከተ፡፡ ደነገጡ፡፡ ‹‹ይሄ ሙስና አይደለም፣ ስጦታ ነው›› አላቸው፡፡ ፈገግ ብለው ደነገጡ፡፡ ያልጠበቁት ሲሳይ ቢዘንብላቸው ጆኒን ሳይታወቃቸው ማምለክ ጀመሩ፡፡ የታማሚ ካርድ ከጥቁር አንበሳ አስመጡለት፡፡ በየቀኑ በአጃቢ ወጥቶ ማታ እንዲገባ ተደረገ፡፡ ‹‹የአልጋ ቁራኛ ነው›› እየተባለ ወፍ ሳይንጫጫ ተንከብክቦ ከእስር ቤት ይወጣል፡፡ ደሳለኝ ሆቴል ይሄዳል፡፡ ብዙ ሠርቶና ጥቂት ተዝናንቶ ቂሊንጦ አመሻሽቶ ይመጣል፡፡
ይህ ከሆነ ከስንት ጊዜ በኋላ የበታች ፖሊሶች እርስበርስ ተጣሉ፡፡ የፀቡ መነሾ ‹‹ጆኒን ለማጀብ ተራው አልደርስ አለን›› የሚል ፉክክር ነበር፡፡ ነገሩ ተካረረና ጠቅላላ ግምገማ ተጠራ፡፡ የማረሚያ ቤቱ አለቆች በሙሉ ተገመገሙ፡፡ ግምገማ ግለት ነው፡፡ የበታች ፖሊሶች የጆኒን ጉዳይ አፍረጠረጡት፡፡ 3ቱ የሕወሓት ነባር ታጋዮች በጆኒ ጦስ ከስራቸው ላልተወሰነ ጊዜ ታገዱ፡፡ ጆኒም ወደ ቃሊቲ ተዛወረች፡፡ ቃሊት ከተዘዋወረ በኋላ እኔም ጠይቄው አላውቅም፡፡
ጌታዬ! ከኔ ጋር ነዎት?
የሚገርመኝ…ጆኒ ታይታ አለመውደዱ ነው፡፡ ሰማያዊ ቱታዋን ለብሳ በቂሊንጦ ማረሚያ ግቢ ሲንጎራደድ ላየው የነሐስ ሜዳሊያ ያመጣ ሚስኪን የማረሚያ ቤት አትሌት እንጂ ታራሚ አይመስልም፡፡ ጆኒ ታይታ ብቻ ሳይሆን ፎቅም አይወድም፡፡ በአንደበቱ እንደነገረኝ ፎቅ የሚሠራ ሀብታም ይፀየፋል፡፡ ‹‹ፎቅ የሚሠራ ሀብታም ብር እንጂ ጭንቅላት የሌለው ነው›› የሚለው ነገር አለው፡፡ አንድ ቀን በቦሌ ጎዳና እርሱ መቼም በማይለውጣት ከርካሳ ፒክአፑ እየሄድን ሳለ በግራና በቀኝ የተገተሩ ፎቆችን አየና-
‹‹ገረመው! ይሄ ሁሉ የአእምሮ ድሀ በከተማው እንዳለ አላውቅም ነበር፣ ለመሆኑ ያንተስ ፎቅ የቱ ነው?›› ብሎ ቀለደብኝ፡፡ ሳቅኩኝ፡፡ ሃብታም ቀልዶ አለመሳቅ ዋጋ ስለሚያስከፍል ሳቅኩኝ፡፡
ጆኒ ፎቅ መስራትን የራስን ምስል በትልቁ ሳሎን ግድግዳ ላይ እንደመስቀል አድርጎ ይመለከታል፡፡ የሱ ሱስ ፋብሪካ መገንባት ነው፡፡ ለዛም ነው ፋብሪካውን ‹‹የሱ›› ብሎ የሰየመው፡፡ ለመዝናናት ሲፈልግ ሸራተን አይሄድም፤ ወደ ፋብሪካው እየበረረ ይሄዳል፡፡ ሞተር ሲጮህ፣ የማሽን መዘውር ሲንጣጣ፣ የጉልበት ሠራተኛ ሲረባረብ ያኔ ነፍሱ ሀሴት ታደርጋለች፡፡
ጆኒ ቀጭን ጌታ! ሲበዛ ተጠራጣሪ ናት፡፡ ራሱ የከፈተውን አምቦ ዉኃ አያምነውም፡፡ አንዴ ከተጎነጨለት በኋላ ሌላ አዲስ አምቦ እንጂ ቢሞት የጀመረውን አይጠጣም፡፡ ቂሊንጦ ሻወር ይወስድ የነበረው ሁለት መቶ የማዕድን ዉኃ ታሽጎ ገብቶለት ነው፡፡ ከቤት ታሽጎ የሚመጣለትን ምግብ አንድም ሰው እንዲነካበት አይፈልግም፡፡ ‹‹ሞሳድ ይከታተለኛል›› እያለ ያስቀን ነበር ድሮም፡፡ ለምን ያን እንደሚያደርግ ግን ዛሬም ድረስ አይገባኝም፡፡ እኔን ካልገባኝ ደግሞ ማንንም አይገባውም ማለት ነው፡፡
ጌታዬ! ከኔ ጋር ኖት?
ያው እንደሚያውቁት የወሬ ሱስ አለብኝ፡፡ አንዳንድ ሰው ደግሞ የሲጃራ ሱስ አለበት፡፡ ጆኒ ደግሞ የፋብሪካ ሱስ ነው ያለበት፡፡ በአንድ ወቅት ታዲያ የፋብሪካ ሱሱን ለመወጣት የአገሪቱን ትልቁን የብረት ፋብሪካ ዱከም ላይ ለመገንባት ጫፍ ደረሰ፡፡ የከተማዋን ጎዳና ተዳዳሪ በሙሉ አንድ ግቢ ሰብስቦ ‹‹የወዳደቀ ብረት ካመጣችሁልኝ በጥሩ ብር እገዛችኋለሁ›› አላቸው፡፡ ወዲያውኑ በከተማዋ የሚገኘው የቆራሌው ቁጥር በመቶ እጥፍ ጨመረ፡፡ ለሁለት ዓመት ድረስ የወዳደቀ ብረት ሲከምር ዱከም የሚገኘው ግቢው የብረት ተራራ ሆነ፡፡ ጆኒ አበደ ተባለ፡፡ እርሱ ግን ጌታዬ! የሚሰራውን የሚያውቅ ጮሌ ነበር፡፡ የስታፋ ብረትን ጨምሮ የብረት ዘር ዋጋን መሬት ሊያስነካው ጫፍ ሲቃረብ ከዛም ከዚም ብለው ከርቸሌ ከረቸሙት፡፡ ምስኪን ጆኒ!
አሁን መንግሥት ጆኒን አንቆ ይዞታል፡፡ ስምንት መቶ ሚሊዮን ብር ክፈለኝ እያለው ነው፡፡ አሁን ጆኒ ለመንግሥት መክፈል ያለበት እዳ ከነወለዱ 3.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ጌታዬ አልተሳሳቱም፡፡ ያነበቡት ‹‹ቢሊዮን›› የሚል ቁጥር ነው ፡፡ ይህ ማለት ዘንድሮ መንግሥት ለሰራተኞች ያደረገውን የገቢ ግብር ማሻሻያ፣ እንዲሁም ለመምህራን ያደረገው የደመውዝ ጭማሪ ሲደመር እኩል ይሆናል የጆኒ እዳ -እንደማለት ነው፡፡ ይህ ማለት የአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድ ወጪ ማለት ነው፡፡ ይህን ከከፈለ ዛሬዉኑ ከእስር ሊፈቱት ይችላሉ፡፡ ጆኒ ግን ብትሞት እሺ አትልም፡፡ ይህን ብር ከምትከፍል መቶ ዓመት ብትታሰር ትመርጣለች፡፡ ‹‹የምትሉት አይነት ብር የለኝም፡፡ፋብሪካውን ስገነባ ብዙ ብር አውጥቻለሁ፤ ባይሆን ቀንሱልኝና በአገር ዋጋ ልክፈል›› እያላቸው ነው ይባላል፡፡ ይሰሙታል ብለው ነው? አይሰሙትም፡፡ ለምን በሉኝ…
አንድ ወቅት ከአሁኑ ታሳሪና ከቀድመው የገቢዎች አለቃ ለአቶ ገብረዋእድ ጋር መለኪያ ይዘን ስንጨዋወት ጆኒ ለቤተክርስቲያን የሰጠውን 82 ሚሊዮን ብር ነገርኳቸው፡፡ ከት ብለው ከሳቁ በኋላ ‹‹ ስማ ገረመው! የቄሳርን እዳ ሳይከፍል የእግዜርን እዳ መክፈሉ አግባብ ነው ትላለህ?›› ብለው አሳቁኝ፡፡ ዛሬ በመሳቄ አፀፀታለሁ፡፡ በወቅቱ ግን እርሳቸው ቀልደው እኔ አለመሳቅ አልችልም ነበር፡፡ አሁን ግብር ጠያቂም፣ ግብር ተጠያቂም አንድ ቤት ገብተዋል-ቃሊቲ፡፡ እዛው ሂሳባቸውን ያወራርዱ እንግዲህ…
ጌታዬ! አሰለቸዎት እንዴ! ጆኒ እንዴት እንደተነሳ አውርቼልዎ ባበቃስ?
ጆኒ ሰርቆ አይደለም እዚህ የደረሰው፡፡ በአቋራጭም አይደለም፡፡ መርካቶ ኮንጎ ጫማ ቸርችሮ ነው፡፡ መርካቶ ኮምቦርሳቶ ደርድሮ ነው፡፡ እርግጥ ነው አባቱ አቶ ሲሳይ ሞላ (ነፍሳቸውን ይማርና) ትጉህ ነጋዴ ነበሩ፡፡ 7ኛ አካባቢ ጠጅ ቤት ነበራቸው፡፡ መርካቶም እንደነገሩ ይሞካክሩ ነበር፡፡ ሆኖም እድሜ ተጫናቸውና ሥራውም ተቀዛቀዘ፡፡ ጆኒ አባቱ በተኙበት አንድ የሰንበት ማለዳ የአባቱን ፔጆ አስነስቶ ወደ ሞያሌ ኬንያ ነዳ፡፡ ወደ ኬንያ ተሻግሮ ከአንድ የፕላስቲክ ፋብሪካ ጋር ተደራድሮ ተመለሰ፡፡ በወጣትነቱ ሲበዛ ደፋርና ቆራጥ ነበር፡፡ አባቱ ለቀናት በእግር ስላስኬዳቸው ገሰፁት፡፡ እርሱም ሁሌም እንደሚያደርገው እግር ስሞ ይቅርታ ጠየቀ፡፡
ያቺ ዕለት ጆኒና ቤተሰቡን ከተራ ሀብታምነት መንጭቃ አወጣችው፡፡ ከኬንያ በገፍ የፕላስቲክ ዉጤቶች መግባት ጀመሩ፡፡ በተለይም የኬንያ ባልዲ የመርካቶን ገበያ አስጨነቀው፡፡ ሁሉም የፕላስቲክና የችፑድ ነጋዴ ለነጆኒ እጅ ሰጠ፡፡ ያኔ ነው ጆኒ ሞቅ ያለ ንግድ ዉስጥ የገባው፡፡ ያኔ ነው ሐብቱ እንደባልዲ አፍ እየሰፋ የመጣው፡፡
እየቆየ ሲሄድ አይን ዉስጥ ገባ፡፡ መንግሥት አይን ዉስጥ፡፡ አማራጭ አልነበረውም፡፡ ከሰዎቹ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ለመቆይት ተገደደ፡፡ ለኢህአዴግ ክብረበዓል ማድመቂያ ብር ይቀበሉታል፡፡ ለወጣቶች ሊግ ስብሰባ ብለው ብር ይቀበሉታል፡፡ ለየካቲት 11 ብር ‹‹ትንሽ በጥስ›› ይሉታል፡፡
ለምሳሌ የሕዳሴው ግድብ የቦንድ ግዢ በግለሰብ ደረጃ በመግዛት ከሜድሮክ ቀጥሎ ክብረወሰን የሰበረው ጆኒ ነው፡፡ 30 ሚሊዮን ብር ከፍሏል፡፡ ለአማራ ልማት ማኅበር ስንትና ስንት ሚሊዮን ብር ካልሰጠከን አሉት፡፡ ‹‹አትጨቅጭቁኝ በቃ ዉሰዱ›› ብሎ የጠየቁትን ስንትና ስንት ሚሊዮን ብር የሠጠ የልማት ጀግና ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው ኪሱን አራቁተው አሠሩት፡፡ የሚራቆት ኪስ ባይኖረውም ቅሉ፡፡
ጆኒ ይሄን ሁሉ ዓመት ስንትና ስንት ብር ገቢ ለራሱም ለመንግሥትም ሲያስገባ ሚስት እንኳን አላገባም፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ እስር ቤት ያገኘሁት ቀን ምን አለኝ መሰለዎ! ‹‹…ገረመው! ምክርህ የገባኝ አሁን ነው…እንደተፈታሁ…ሚስትም አገባለሁ…ፎቅም እገነባለሁ…››
ጌታዬ! ይበሉ ይበርቱልኝ፡፡ ንብረት አፍርቶ ከርቸሌ ከመከርቸም ይሰውርዎ!!
ገረመው ነኝ፣ ከላዮን ባር