ዋዜማ ራዲዮ-ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ ከስልጣን ካልተወገደ በኢትዮዽያ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሊኖር አይችልም የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ገዥው ቡድን ተገዶም ቢሆን ወደ ድርድር በመምጣት የሽግግሩ አካል ካልሆን ሀገሪቱ ወደ ሌላ ቀውስ ትሄዳለች የሚሉም ብዙ ናቸው። በእርግጥስ ኢህአዴግ የመፍትሄው አካል መሆን ይችላልን? ዝግጁስ ነው?
ሰሞኑን ለአራት ቀናት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ባደረገው ስብሰባ ግን ያሳለፈው ውሳኔ ድርጅቱ በቁልቁለቱ መንገድ ሊገፋበት እንዳሰበ የሚያመለክት ነው። ሀገር አቀፍ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ “እኔ ልክ ነኝ- ያሉትንም ችግሮች እኔው እፈታቸዋለሁ” እያለ ነው።
ባለፈው ሳምንት መገባደጃ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ህዝባዊ ተቃውሞው እንደሚቀጥል እና ወደሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም ሊዛመት እንደሚችል ያለውን ስጋት መግለፁ ይታወሳል፡፡ መንግስት በህዝብ ላይ የሚወስደው ኃይል ዕርምጃ በዚሁ ከቀጠለ ሀገሪቱ ልትበታተን ትችላች የሚለው ስጋትም እያየለ ነው፡፡ ሆኖም አሁንም ህዝባዊ አመፁ እና ግጭቱ ከዕለት ወደዕለት ከመጋጋሉ በስተቀር አንዳችም ተስፋ ሰጭ የመለዘብ አዝማሚያ ማየት አልተቻለም፡፡ ከመንግስት፣ ከፖለቲካ ድርጅቶች፣ ከሲቨል ማህበራት ወይም ከምዕራባዊያን አንዳችም አዲስ አዋጭ የመፍትሄ ሃሳብ አልቀረበም፡፡
ስለሆነም ህዝባዊ አመፁ በምን ውጤት ሊደመደም ይችላል? ተቃዋሚ ድርጅቶችስ ምን ምርጫዎች አሏቸው? ብሄራዊ መግባባትን ወይም ድርድርን ሊያመቻቹ የሚችሉት ሜዳው ውስጥ ያሉት ሲቪክ ማህበራትስ አሉ ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ከምንጊዜውም በላይ ወሳኝ ሆነዋል፡፡
[ቻላቸው ታደስ ይህን ጉዳይ የሚያፍታታ ተከታዩን ዘገባ አዘጋጅቷል በድምፅ ዘገባውን እዚህ ያገኙታል አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]
ብዙ ታዛቢዎች “የመንግስት የጭፍለቃ ርምጃ ግብታዊ ስር ነቀል ለውጥን ከማፋጠን ያለፈ ፋይዳ የለውም” ቢሉም መንግስት ግን በኃይል ርምጃው ገፍቶበታል፡፡ ስለዚህ ህዝባዊ አመፁ በዚሁ ከቀጠለ ሦስት ታሳቢ ውጤቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡
“ሀገራዊ ቀውስ እና ርስበርስ ግጭት ሊከተል ይችላል” የሚለው አንደኛው ታሳቢ ውጤት ነው፡፡ በስለላ መረጃ ትንተና ዝና ያተረፈው ስትራትፎር የተሰኘው ዓለም ዓቀፉ ድርጅትም ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ “ህዝባዊ አመፁ ተቀጣጥሎ በመቀጠሉ በሀገሪቱ ደም አፋሳሽ ብጥብጥ እየነገሰ ነው” ሲል ስጋቱን ጠቅሷል፡፡ የተራዘመ ግጭት ሊሰፍን እንደሚችልም ገልጧል፡፡ በተለይ በቅርቡ የአቶ ሌንጮ ለታ ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር እና ጠመንጃ ነሳው አርበኞች ግንቦት ሰባት ጥምረት መፍጠራቸውም የሰላማዊ ትግል ቀዳዳ እየጨለመ መሄዱን ያሳያል፡፡
ሁለተኛው ውጤት ህዝባዊ አመፁ ግብታዊ የመንግስት ለውጥ አስከትሎ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሊደረግ የሚችልበት ዕድል ሊፈጠር ይችላል የሚለው ነው፡፡ ርግጥ ነው፣ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ባጭር ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ቀዳዳ ስለመገኘቱ አስተማማኝ ዋስትና ባይኖርም ግብታዊ መንግስታዊ ለውጥ ላለመምጣቱ ግን በድፍረት መናገር አይቻልም፡፡ በአሜሪካ መንግስት ፖሊሲ አውጭዎች ደህና ግምት የሚሰጠው ስትራትፎርም በሰሞኑ ግምገማው ህዝባዊ ጥያቄዎች በህወሃት የበላይነት የተያዘው አገዛዝ እንዲያከትም ወደመጠየቅ ማደጋቸው አመፁ ወደማይቀለበስበት ደረጃ መድረሱን ጠቋሚ መሆናቸውን ገልጧል፡፡ ታሪካዊ ተፎካካሪ የሚባሉት የአማራ እና ኦሮሞ ብሄሮች ጥምር ተቃውሞ ማንሳታቸው “ህወሃት የበላይነቱን አስጠብቆ ሊቀጥል የሚችልበትን ጊዜ ያሳጥረዋል፤ ፀጥታ ኃይሎችም ጥምር አመፁን ሊቋቋሙት ይቸግራቸዋል” ለሚል ድምዳሜ አብቅቶታል፡፡
ሦስተኛው ታሳቢ ውጤት መንግስት ከእስካሁኖቹ ህዝባዊ አመፆች አዝማሚያ ተምሮ ፈጣን የፖለቲካ ማሻሻያዎችን ሊያደርግ ይችላል የሚለው ነው፡፡ አመፁ ከተጀመረ ወዲህ ግን መንግስት በራሱ መድረኮች “ህዝብን እያወያየሁ ነው” ቢልም ከተለመደው ድርጅታዊ ጥርነፋ ያለፈ መድረክ አላመቻቸም፡፡ የተባበሩት መንግስታት ሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣሪ ኮሚሽን በግጭቶቹ የንፁሃን ዜጎችን መገደል በገለልተኝነት ለማጣራት ቢጠይቅም መንግስት አልቀበልም ብሏል፡፡ በራሱ መንገድም አጣርቶ ይፋ ማድረግ አልፈለገም፡፡ ሰሞኑን ደሞ ሰላማዊ ተቃውሞውን ሁሉ ከትምክህትና ጠባብነት ጋር ማስተሳሰር መጀመሩ ያው ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ ዓይነት ባህሪውን ጠቋሚ ነው፡፡ ምሁራን ለብሄራዊ ዕርቅ መነሻ ይሆናሉ ከሚሏቸው ርምጃዎች መካከል ዋነኞቹ እስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞችን፣ ተቃዋሚዎችንና ሃይማኖት መሪዎችን መፍታት እና ጨቋኝ ህጎችን መሰረዝ ቢሆኑም መንግስት ግን እያጠበቀ ሲሄድ እንጂ ሲለሳለስ አይታይም፡፡
ኢህአዴግ–መራሹ መንግስት በሀገሪቱ ላይ ያለው ቁጥጥር ሙሉ በሙሉ ከመሸርሸሩ በፊት ለውይይት ወይም ድርድር ሊቀመጥ የሚችለው በመልካም ፍቃዱ፣ በህዝባዊ አመፁ ተገድዶ ወይም በምዕራባዊያን አጋሮቹ ተፅዕኖ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ እስካሁን ግን በየትኛውም በኩል አንዳችም ፍንጭ አልታየም፡፡ ምናልባት ለድርድር በሩን ከከፈተ ግን ዋነኛ ገፊ ምክንያቱ የሚሆነው ህዝባዊ አመፁ ይመስላል፡፡
በርግጥ የአሜሪካ መንግስት ኢህአዴግ ሁሉን ዓቀፍ ብሄራዊ ውይይት ወይም ድርድር እንዲጀመር በሩን እንዲከፍት መጠየቅ አልፈለገም እንጂ ቢጠይቅ ኖሮ ግን ማርሽ ዘዋሪ መሆን በቻለ ነበር፡፡ እስካሁን ሲያስተላልፍ የቆየው መልዕክት ግን ጥንቃቄ ከተሞላበት ዲፕልማሲያዊ ጨዋታ ያለፈ አልሆነም፡፡ የአሜሪካ መንግስት የተለሳለሰ አቋም ሲነሳ ሰሞኑን ክፍለ አህጉራዊው ድርጅት ኢጋድ ባሰራጨው ማስጠንቀቂያ አልሸባብ ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች መጠነ-ሰፊ ሽብር ጥቃት ለመፈፀም ተዘጋጅቷል ማለቱን ታሳቢ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ መግለጫው በተወሰነ መልኩ የኦባማ አስተዳደር በኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ላይ ተፅዕኖ ከማድረግ ይልቅ እሹሩሩ እያለው እንዲቀጥል የሚጋብዝ ነው፡፡ አልሸባብ ፍፁም ተዳክሞ በሙት ሽረት ትግል ላይ መሆኑን የሚናገረው ኢጋድ እንዲህ ዓይነቱን ያልተጠበቀ መግለጫ ባሁኑ ጊዜ ማውጣቱም አነጋጋሪ መሆኑ አልቀረም፡፡
ሀገሪቱ ወደ ቀውስ ማምራቷ ከሞላ ጎደል የሚያግባባ ቢሆንም ከኢህአዴግ በኋላስ ምን ትሆናለች? ምንስ መሆን ይገባታል? የሚለው ጥያቄ ግን ገና በቅጡ መፍታታት አለጀመረም፡፡ ሀገሪቱ የሚያስፈልጋት ጥገናዊ ለውጥ ነው? ስር ነቀል ለውጥ ነው? ወይንስ ብሄራዊ ዕርቅ እና መግባባት? በሚለው ዙሪያም ገና ሀገር ዓቀፍ ውይይት ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት የለም፡፡ እዚህ ላይ ግን በተካረረ ብሄር-ተኮር ፖለቲካ ስትናጥ የኖረችው ኢትዮጵያ ግብታዊ እና መጠነ-ሲፈ ህዝባዊ አመፅን እያስተናገደች ህልውናዋን መጠበቅ ትችላለች ወይ? የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑ አልቀረም፡፡ ግብታዊ እና ሀገር ዓቀፍ ህዝባዊ አመፅ የሚያሰጋቸው ወገኖች የ1966ቱ አብዮት ሀገሪቱን የከተተበትን ውጥንቅጥ በማስረጃነት ይጠቅሳሉ፡፡
ዛሬም ድረስ የመገንጠል ዓላማ ያነገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች ክፍተቱን ተጠቅመው የሀገሪቱን ህልውና ሊፈታተኑ ይችላሉ የሚለው ስጋትም ለእነዚህ ወገኖች አይሎ ይታያቸዋል፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀም አዳዲስ የመገንጠል ጥያቄችም ሊያጎነቁሉ እንደሚችሉ ስጋት አላቸው፡፡ መገነጣጠሉ በተግባር አስቸጋሪ ቢሆን እንኳ ለብሄር ማንነት ቅድሚያ በሚሰጡ እና ህብረ ብሄራዊ ማንነትን ብቻ በሚያቀነቅኑ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለው ያልለዘበ ውጥረት ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያው ስርዓት የሚፈጠርበትን ቀን ሩቅ ሊያደርገው ይችላል፡፡
ኢህአዴግ ድርድር ወይም ውይይትን ጠረጴዛው ላይ ቢያስቀምጥ እንኳ ተቃዋሚ ድርጅቶች በተቀናጀ መንገድ ደህና የፖለቲካ ትርፍ ለመዛቅ ዝግጁ አይመስሉም፡፡ መንግስት ራሱን ለድርድር ካዘጋጀ ግን ምዕራባዊያን አጋሮቹ ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡት ጥርጥር የለውም፡፡ የሆነው ሆኖ እንደ 1966ቱ ሁሉ ዛሬም ህዝባዊ ተቃውሞው ከፖለቲካ ልሂቃን ዝግጅት ቀድሟል፡፡
ምንም እንኳ ኢህአዴግ ሃሳቡን በደምሳሳው ቢያጣጥለውም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያ አንድነት መድረክ እና ኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግሬስን የመሳሰሉ የሀገር ውስጥ ተቃዋሚ ድርጅቶች ብሄራዊ መግባባት ተፈጥሮ ብሄራዊ አንድነት መንግስት እንዲመሰረት ጥሪ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በውጭ ያሉ ሌሎች ኃይሎች ደሞ ሃሳቡን እንደ ስልጣን ክፍፍል ስለሚያዩት ስር ነቀል ለውጥ ፈላጊ መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ሰላማዊ ሽግግር ቢኖር እንኳ ልክ በኢሠፓ ለይ እንደሆነው ሁሉ ኢህአዴግም በወደፊቷ ኢትዮጵያ ድርሻ ሊኖረው አይገባም የሚል ጠንካራ አቋም ያላቸው ኃይሎችም አይጠፉም፡፡ በርግጥ የመንግስት የኃይል ጭፍለቃም ቢሆን በዚሁ ከቀጠለ በሂደት ህዝቡ አመፁን ከመቀጠል ውጭ ለድርድር እና ውይይት ጥሪ ጆሮ እንዳይኖረው ማድረጉ የሚቀር አይስልም፡፡ የሀገሪቱን መፃዒ ዕጣ ፋንታ የሚያደላድሉ ገለልተኛ ሲቪክ መድረኮች ባለመኖራቸው ህወሃት/ኢህዴግ በማንኛውም መንገድ ስልጣን ይልቀቅ እንጂ ሌላው በኋላ ይታሰብበታል የሚለው አስተሳሰብ ገናና እየሆነ መሆኑን መታዘብ ይቻላል፡፡
ታዋቂ ግለሰቦች፣ ሃይማኖት መሪዎች እና ምሁራንም ስለ ብሄራዊ ዕርቅ ወይም ብሄራዊ መግባባት ሃሳባቸውን በተናጥል ከማካፈላቸው በስተቀር ሀገሪቱን ከውጥንቅጥ ለማዳን በተቀናጀ መንገድ የጀመሩት አዲስ ጥረት ስለመኖሩ አልተሰማም፡፡ በዚህ ረገድ ብሄራዊ መግባባትን ለማመቻቸት ወይም ፖለቲካዊ ድርድርን ለማስጀመር የሚችሉ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠሩ፣ ሁሉንም የፖለቲካ አመለካከቶች አካታች የሆኑ እና ሰፊ ማህበራዊ መሰረት ያላቸው የጋራ ምክክር መድረኮች አለመኖራቸው አንዱ ችግር ሆኗል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ብሄር ስብጥር ባላት ጎረቤት ኬንያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በምርጫ ውዝግብ ሳቢያ በተከሰቱት ግጭቶች የሲቪል ማህበራት እና ሃይማኖት መሪዎች የነበራቸው የአደራዳሪነት እና አስታራቂነት ሚና ምትክ አልባ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በውጭ ሀገር በተቃዋሚ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማህበራት እና ግለሰቦች ጥምረት ከተቋቋመው የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ በስተቀር እምብዛም ድምፁ የሚሰማ ሰፊ የጋራ ምክክር መድረክ የለም፡፡ “የአፍሪካ ሰላም፣ ድርድር እና ዕርቅ ተቋም” የተባለው በፊታውራሪ መኮንን ዶሪ የሚመራው አህጉራዊ ድርጅት ግን በመጭው ህዳር ወር ሀገር ዓቀፍ የዕርቅ ጉባዔ እንዲካሄድ ለተባበሩት መንግስታት፣ አውሮፓ ህብረት እና ለኢትዮጵያ መንግስት ጥሪ መበተኑን ይናገራል፡፡ ሆኖም ከመንግስት አወንታዊ ምላሽ አለማግኘቱን ገልጧል፡፡በሀገር ውስጥም በጨቋኙ ሲቪል ማህበራት አዋጅ ሳቢያ ሲቪክ ማህበራት ጨርሶ ተዳክመዋል፡፡
ከተራ ግልሰቦች መካከልም የቀድሞው ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ተንሳይ እና የቀድሞው አየር ኃይል አዛዥ ጄኔራል አበበ ተክለ ኃይማኖት መፍትሄ ያሉትን በፅሁፍ ደጋግመው ከመግለፃቸው ውጭ ሌሎች ድምፆች ፀጥ ረጭ እንዳሉ ነው፡፡
አሁን ሀገሪቱ ብዙ ውጥንቅጥ ገጥሟታል፡፡ የጥላቻ ንግግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉ መሄዱን የሚናገሩ ምሁራንም አሉ፡፡ አንጋፋው ምሁር እና ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም በሀገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተማሪዎች መካከል ብሄር ለይተው የሚካሄዱትን ግጭቶች አደገኛ አዝማሚያዎች መሆናቸውን ሲጠቁሙ ኖረዋል፡፡ ገበሬዎችም በማንነታቸው ብቻ እየተለዩ ከደቡብ እና ቤንሻንጉል ክልሎች መፈናቀላቸው ዘረኝነት እና ዓለማቀፋዊ ሰብዓዊ ወንጀል መሆኑን፣ ቂም እና ቁርሾም ማሳደሩን አበክረው ያስረዳሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ብሄር የለዩ የጥላቻ ንግግሮች ስር መስደድ መጀመራቸው በጥናቴ ደርሸበታለሁ ብሏል፡፡ በወልቃይት እና ጎንደር በሚከሰቱ ግጭቶች ደሞ መንግስት ራሱ ተቃውሞ ያነሱ ዜጎችን በዘረኝነት እና ጥላቻ ድርጊት ከሳሽ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡
ከዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ መውጫው ምን ይሆን? መንግስትስ በያዘው የኃይል መንገድ ይቀጥላል ወይንስ ነባራዊ ሁኔታውን አጢኖ በሳል ርምጃ ወስድ ይሆን ከየትኛው ወገንስ አዋጭ መፍትሄ ይመጣ ይሆን? በዚህም አለ በዚያ አሁንም ቢሆን ሀገሪቱን ከመጠነ-ሰፊ ቀውስ ለማዳን ጊዜው የመሸ አይስልም፡፡