ዋዜማ ራዲዮ- በመላው ኦሮሚያ ቅዳሜ ሊካሄድ ለታሰበው የተቃውሞ ስልፍ ዝግጅት መጠናቀቁን ህቡዕ አስተባባሪ ቡድኑ ጠቆመ። የሰልፉ አስተባባሪዎች ለዋዜማ እንዲደርስ ባደረጉት መረጃ በሰልፉ ላይ ተይዞ የሚወጣው መፈክሮች እና የት የት ቦታ እንደሚወጡ፣ የመንግስትን ጫና መቋቋም የሚቻልበትን ብልሀት እና የመሳሰሉትን ምክር አዘል መመሪያዎች በተለያዩ ዘዴዎች ተሰራጭተዋል።
በጎንደር ላይ በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የጎንደር ሰልፈኞች ለኦሮሞ ህዝብ አጋርነታቸውን እንደገለጹት ሁሉ በመላው ኦሮሚያ በሚደረገው ሰልፍ ላይ ለወልቃይት የማንነት ጥያቄ የኦሮሞ ህዝብ አጋርነቱን ያሳያል ተብሏል።
በሰልፉ አላማና ግብ ላይ በኦሮሞ መብት ላይ የሚሰሩ ታዋቂ ግለሰቦች ምሁራንና አክቲቪስቶች ከሀሞስ ዕለት ጀምሮ በተለያዮ መድረኮችና በማህበራዊ ሚዲያ ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ።
የዋዜማ የኦሮምኛ ዴስክ ባሰባሰበው መረጃ በበርካታ የኦሮምያ ዋና ዋና ከተሞች ውጥረትና ፍርሀት የነገሰ ሲሆን መንግስት ስልፉን ለማምከን ግራ የተጋባ መሆኑን የሚያመልክቱ ፍንጮች ታይተዋል። በርካታ የኦህዴድ አባላት ስልፉ እንዲካሄድ ፍላጎት እንዳላቸው በተለያዩ መንገዶች እየገለፁ ሲሆን የፌደራል መንግስት ወታደሮች በዋና ዋና የመንግስት ተቋማትና መንገዶች ላይ ስፍረዋል።
ከሰልፉ አስቀድሞ የስልክ፣የትራንስፖርትና የኢንተርኔት አገልግሎት ሊቋረጥ እንደሚችል አንዳንድ የመንግስት ምንጮች ጠቁመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሞያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሙክታር ከድር በመላው ኦሮሚያ የተጠራውን ሰልፍ በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸው እንዳሉት ሰላማዊ ሰልፉን የሚያዘጋጀው አካል በህጉ መሰረት አልጠየቀንም፣ ፈቃድ ያገኘ ሰልፍ የለም ብለዋል። ከሰልፉ ጀርባ ሌላ ድብቅ አጀንዳ ያለው ኃይል እንዳለ ተናግረዋል።
አቶ ሙክታር አክለውም ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን ለመጠየቅ ማንም የማይወስድበት መብቱ ነው በማለት በሰላማዊ መንገድ ጥያቄዎችን ወጥቶ ማቅረብ እንደሚቻል መክረዋል። በኦሮምያ ዘጠኝ ወራት የዘለቀው ተቃውሞን ተከትሎ መንግስት በክልሉ ወታደራዊ ሀይል በማሰማራት ለበርካታ ሰዎች ሞት ሰበብ የሆነ የሀይል እርምጃ መውሰዱ ይታወቃል።