ጤና ይስጥልኝ ጌታዬ!
ገረመው እባላለሁ፡፡ እሳት የላስኩ የፊንፊኔ ደላላ ነኝ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ መሆኔን ድሪባም ኩማም ያውቃሉ፡፡ ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› መሆኔን እግዜርም ሰይጣንም ያውቃሉ፡፡ ‹‹ላየን ባር›› ቤቴ፣ ‹‹ቴሌ ባር›› ግዛቴ ነው፡፡ ጥሎብኝ አልረጋም፡፡ ካዛንቺስ ነው ሲሉኝ ሳሪስ፣ ቀበና ነው ሲሉኝ ባምቢስ…ሄሄሄ ደላላ ምን ቀልብ አለው ብለው ነው!
ጌታዬ!
ይሄ የሊዝ ጉዳይ አስተዛዘበን እኮ! እኛ ምርጫው ብቻ መስሎን የሚጭበረበረው፡፡ ለካስ ሊዝም ይጭበረበራል፡፡ በ21ኛው የሊዝ መሬት ንግድ ላይ ወዳጄና ደንበኛዬ ጋሽ ሙሉጌታ ተፈራ መሬት ሲያጭበረብር ተያዘ ነው የሚሉኝ የማምናቸው ወዳጆቼ፡፡ ጌታዬ! መሬት ደግሞ እንዴት ይጭበረበራል ያሉኝ እንደሁ ነገሩን ከሥር መሠረቱ አስረዳለሁ፡፡
አያት አደባባይ ወደ ጣፎ በሚወስደው ጎዳና ሲጓዙ አስፋልት የሚያይ 1243 ካሬ ስፋት ያለው የተንጣለለ መሬት ይመለከታሉ? ማን? ጋሽ ሙሉጌታ፡፡ ቦታውን ሆቴል አፓርትመንት ለመገንባት የሰጠ እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ ማን? ጋሽ ሙሉጌታ፡፡ እጅግ ወደዱት፡፡ ሊያጡት አልፈለጉም፡፡ እንደማንም ከተጫረቱ ደግሞ መሸነፍም አለ፡፡ እርሳቸው ደግሞ ማሸነፍ ብቻ ነው የፈለጉት፡፡ እናም ዉስጥ ካሉ አጫራጮች ጋር በመመካከር አንድ ዘዴ ዘየዱ አሉ ሰውዬው፡፡ ኤህአዴግ ምርጫውን እንዳጭበረበረው ሁሉ ጨረታውን ማጭበርበር፡፡ 100 እጅ ማሸነፍ የሚቻለው እንዲያ ሲሆን ብቻ ነው፡፡
ቦሌ መድኃኒዓለም ከቢር ጋርደን ጎን ያን የመሠለ ሆቴል ያለው ሰው እንዲህ አይነት ተግባር ይፈጽማል ተብሎ አይገመትም፡፡ ሞናርክ ሆቴል የርሳቸው ነው እኮ፡፡ ሆኖም የፊንፊኔ መሬት አሳሳታቸው፡፡ አቶ ሙሉጌታ የሞከሩትን የማጭበርበር ተግባር በአጭሩ ከዚህ እንደሚከተለው አስረዳለሁ፡፡
ሊዝ ጨረታ የሚከፈተው ወትሮም በግልጽ ሕዝብ በተሰበሰበበት ነው፡፡ ተጫራቾች ለአንድ ካሬ የሚያቀርቡትን ዋጋ በግልፅ ፎርም ላይ መጻፍ ይኖርበቸዋል፡፡ የካሬውን ዋጋ በቦታው ስፋት አባዝተው በአሀዝና በፊደል ማስቀመጥም ግዴታ ነው፡፡ ‹‹የሞናርኩ ጌታ፣ ጋሽ ሙሉጌታ›› ግን ዋጋ የሚጻፍበትን የጨረታ ሰነድ ባዶ አድርገው አስገቡ፡፡ ለምን ቢባል እዚያ ዉስጥ ባሉ አጫራቾች ከፍ ያለ ዋጋ ያቀረበውን ሰው ተመርኩዘው አብላጫ ዋጋ በቅጽበት እንዲሞላላቸው ተስማምተው ያደረጉት ነው፡፡ ደግሞ እኮ ይህንን የሞከሩት በስማቸው በገዙት የጨረታ ሰነድ ብቻ ቢሆን ዘንግተውት ነው ይባላል፡፡ ልጃቸው ሜላት ተፈራ አልቀረች፣ ወንድ ልጃቸው ኤርሜያስ ተፈራ አልቀረ፣ ሌላው ጎረምሳ ዮናታን ተፈራ አልቀረ…፡፡ ቤተሰቡን ተሳስተው አሳሳቱት፡፡
ጌታዬ! ጋሽ ሙሉጌታን አይፍረዱባቸው፡፡ የፊንፊኔ መሬት እያደር እጸበለስ ሆኗል፡፡ ማንንም ያሳስታል፡፡ ለማንኛውም አቶ ሙሉጌታ ለጨረታ ማስከበርያ ዋስትና ያስያዙት 123ሺ 729 ብር መስተዳደሩ ወርሷቸዋል፡፡ ባለሀብቱን በማጭበርበር ሙከራ ክስ ወደ ፍርድቤት ለመውሰድም የድሪባ ጠበቆች በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ሰምቻለሁ፡፡
ጌታዬ!
ለማንኛውም አሁን ማዘጋጃ ቤት ነው ያለሁት፡፡ ለ22ኛው ዙር የመሬት ችብቻቦ፡፡
የአዲስ አበባ ቴአትርና ባሕል አዳራሽ በደንበኞቼ ተሞልቷል፡፡ ከመጋረጃ ጀርባ ባለ አንድ ገቢር ተውኔት እየታየ ነው፡፡ ተመልካቾቹም ተዋናዮቹም የመሬት ቀበኛ የሆኑ ባለሐብቶች ናቸው፡፡ ፊንፊኔ ለ22ኛ ጊዜ የቸረቸረችውን መሬት ላሸነፉ ባለሐብቶች እየሸለመች ነው፡፡ በፀረ ልማት ቋንቋ ነገሩን እንግለጽ ከተባለ- ‹‹ፊንፊኔ ከድሀ ገበሬ የነጠቀችውን መሬት ለልማታዊ ባለሐብቶች በፍጥነት እየስተላለፈች ነው››፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ስሙ አያት ‹‹ፈረስ ቤት›› አካባቢ የሚገኙ 145 ኪስ ቦታዎችን በአዲስ ልሳን ጋዜጣ አስጥታ ሸጣ ከበላች ገና ሁለት ወር አልሆናትም፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ 110 ቦታዎችን ከዚያው ሰፈር ለገበያ አቅርባቸዋለች፡፡ ከነዚህ ዉስጥ 3ቱ ብቻ በቂ ተጫራች ባለመቅረቡ ወደ መሬት ባንክ ተመላሽ እንዲደረጉ ተደርገዋል፡፡ ወደፊት በ23ኛው ዙር በድጋሚ ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ጌታዬ!
እርስዎ ተከራይ ኖት ወይንስ መሬት ይዘዋል? ተከራይ ከሆኑም ብዙ አይዘኑ፡፡ ፊንፊኔ ራሷ የኦሮሚያ ቤት ተከራይ ሆና የለም እንዴ፡፡ ይኸው አከራይዋ አንዲት ቆሻሻ ከኔ ደጅ እንዳትደፊ ብላት መከራዋን እየበላች ነው የሰነበተችው፡፡ ለማንኛውም እንዴትም ብለው ከተከራይነት ራስዎን ነጻ ያውጡ፡፡ በዚያ በዚህም ብለው ቦታ ይያዙ፡፡ ካለመያዝ መያዝ ሳይሻል አይቀርም፤ ዘንድሮ የሚሆነው አይታወቅማ፡፡ ለመሆኑ ይህ የሚረግጡት መሬት የማን ነው?
ጌታዬ!
አያት ፈረስ ቤትን ያዉቁታል? የአዲስ አበባ የምሥራቅ ድንበር ነው፡፡ መሬቱ ተሸጦ ተሸጦ ድንበር ተደረሷል እኮ፡፡ እዚያ ሰፈር ግምቱ ግማሽ ቢሊዮን የሚያወጣ፣ 30ሺ ሕዝብ የሚይዝ ዘመናዊ ስታዲየም ሊገነባ ዉል ተይዟል፡፡ ከማን ጋር አሉኝ? ከ‹‹ዛምራ›› ነዋ፣ ሌላ ከማን ይሆናል ብለው ነው፡፡ ዛምራ የስቴዲየም ቀብድ በልቷል፡፡ ኾኖም ቦታውን አጥሬ ለማስከበር ሲሞክር የገበሬ ተቃውሞ ገጥሞት የወደፊቱን ስቴዲየሙ ለጊዜው በችካል ምልከታ አኑሮታል፡፡ ጎረቤት ሰንዳፋ ቆሻሻ አላስደፋም ብላ ፊንፊኔ ተግማምታ ነው የሰነበተችው ብዬዎት የለም? ፊንፊኔ በራሷ መሬት ስቴዲየም መገንባትም የምትችል አልሆነችም፡፡ የቆረጠ ገበሬ እያስደነበራት ነው፡፡ ጉድ ፈላ ማለት ይሄኔ ነው ጎበዝ፡፡ለመሆኑ የሚረግጡት መሬት የማን ነው?
ጌታዬ! ወደ ጨረታው ልመልስዎ!
እኒህ በዚህ 22ኛ ዙር ጨረታ ለልማታዊ ባለሐብቶች የሚተላለፉት 110 ኪስ ቦታዎች ታዲያ ይህንን ምናባዊ ስታዲየም አጅበው የሚገኙ ናቸው፡፡ አካባቢው አሁንም ገበሬ እያረሰው ይሁን እንጂ መሠረተ ልማት የተሟላለት ነው፡፡ ከጎኑ ከ3ሺ የሚልቁ የ40-60 ቤቶች እየተገነቡ ይገኛል፡፡ በአገሪቱ ትልቁ የ40-60 ፕሮጀክት በዚህ አካባቢ ወረዳ 10 ነው የሚገኘው፡፡ ከወደ ደቡብም ከወደ ሰሜንም አካባቢውን የሚያዋስኑ 30 ሜትር የአስፋልት መንገዶች ይገኛሉ፡፡ ከፈጣን መንገዱ የሚገናኝ 50 ሜትር መንገድም በቅርቡ ግንባታው ይጀመራል ተብሏል፡፡ ሜድሮክ ከምዕተ ዓመት በፊት ጀምሮ መጨረስ ያቃተው ሌላ የአስፋልት መንገድ ሰፈሩን አቋርጦ ያልፋል፡፡
ጌታዬ!
ይህ ሁሉ መሠረተ ልማት የተሟላለት ሰፈር ነው እንግዲህ ለ22ኛ ዙር ገበያ የወጣው፡፡ ኾኖም የተጠበቀውን ያህል ዋጋ ሳያወጣ መቅረቱ እንደኔ ያሉ ወፍራም ደላሎችን ሳያስገርም አልቀረም፡፡ የወትሮው የተጋነነ የመሬት ዋጋ ሳይቀርብ ዙሩ ተጠናቋል፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ብዬ ራሴን ጠይቂያለሁ፡፡ አንዱ ምክንያት የመሬት ቀበኛ ባለሐብቶች በሰኔ ግብር በመወጠራቸው ነው፡፡ ነፍስ ዉጭ ነፍስ ግቢ ላይ ነበሩ፡፡ ሁለተኛው ምክንያት የ22ኛው ዙር የዋጋ መረጋጋት ከኦሮሚያ የገበሬ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የመጣ ጊዜያዊ ክስተት ነው የሚሉም አልጠፉም፡፡ ዞሮ ዞሮ ከፊንፊኔ አጎራባች ከተሞች የሚዋሰኑ ሰፈሮች የመሬት ዋጋቸው እያደር እየተቀዛቀዘ ነው የመጣው፡፡ አያት አንዱ ማሳያ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ጌታዬ! እርስዎም እንደሚያስታዉሱት ወትሮ ለፊንፊኔ መሬት ለአንዲት ካሬ ከ20ሺ ብር በታች ዋጋ መስማት ብርቅ ሆኖ ቆይቶ ነበር እኮ፡፡ በዚህ የ22ኛ ዙር እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ በተከፈቱ ፖስታዎች አንድም ቦታ ከ18ሺ ብር በላይ አልቀረበበትም፡፡ ብዙዎቹ የተጠናቀቀቱት በ12ሺ ብር አማካይ ሂሳብ ነው፡፡ እርግጥ ነው አቶ ፋሲል ንጉሴ የተባሉ ሰው 22ሺ ለካሬ ሰጥተው አሸንፈዋል፡፡ ኾኖም የተጫረቷት መሬት የበሬ ግንባር የምታህል ናት፡፡ 195 ካሬ፡፡
ጌታዬ! ለምን እንደሆን አላውቅም አያት ወረዳ 10 ለሊዝ ጨረታ የቀረቡት አንድ መቶ አስሩም ቦታዎች አገልግሎታቸው ቅይጥ ተብሎ ነው የወጣው፡፡ ይህም ማለት አሸናፊዎቹ በአካባቢው የሚያካሄዷቸው ግንባታዎች መኖርያ ቤትና ንግድን ማዛመድ ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ለቅይጥ ግንባታ የሚቀርቡ መሬቶች አሸናፊዎቹ ስማቸው በአዲስ ልሳን ጋዜጣ በተገለፀ በ10 ቀናት ዉስጥ ያቀረቡትን ዋጋ 20 በመቶ ለአስተዳደሩ ገቢ ማድረግ አለባቸው፡፡ ለመኖርያ የሚያሸንፉ ባለሐብቶች ግን ገቢ ማድረግ የሚገደዱት የዚህን ግማሽ ነው፡፡ መስተዳደሩ ብዙዎቹን ቦታዎች ቅይጥ እያደረገ የሚያወጣው ሳንቲም ቸግሮት እንደሆነ እኛም እነርሱም ያውቃሉ፡፡ ለሰንዳፋ ቆሻሻ መድፊያ የወጣው አንድ ቢሊዮን ብር ቀልጦ መቅረቱ እንዳስጨነቃቸው እኛም እነርሱም ያውቃሉ፡፡
ለማንኛውም በዚህ ዙር የቀረቡት ቦታዎች ብዙዎቹ ከ400 ካሬ በላይ ስፋት ያላቸው ናቸው፡፡ ወትሮ እየቆነጣጠረ ሊዝ የሚያወጣው የፊንፊኔ መስተዳደር እንዲህ ሰፋፊ ይዞታዎችን ለጨረታ ማቅረቡ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ የብዙዎቹ አስገዳጅ የግንባታ ከፍታ ከወለል በላይ 4 ፎቅ ነው፡፡
እንዲህ እንዲያ እያልን እዚህ ደርሰናል፡፡ 22ኛ ዙር ፡፡ በዚህ ዙር ዝቅተኛ የመሬት ዋጋ የቀረበው አቶ ኑረዲን ኢሳ በተባሉ ባለሀብት ሲሆን ለ500 ካሬ ቦታ 6667 ብር አቅርበው ታሪክ ሰርተዋል፡፡ ኾኖም የዙሩ አማካይ ዋጋ ከረዥም ጊዜ በኋላ ስክነት ታይቶባል ተብሏል፡፡ መሬት ሲሰክን ገቢው የሚቀንሰው መስተዳደሩ ከሰሞኑ አንዳንድ እርምጃዎችን ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
22ኛ ዙር ጨረታ ዉጤት አርብ ዕለት ቀጥሎ የዋለ ሲሆን በአቃቂ ቃሊቲና በንፋስ ስልክ ክፍለከተሞች የቀረቡ በጣት የሚቆጠሩ ቦታዎች ለአሸናፊዎች ተላልፈዋል፡፡ በተለይም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የቀረበው መሬት ልዩ ትኩርት ሲሰጠው ቆይቶ በመጨረሻ አሸናፊው ተለይቷል፡፡ ለነገሩ ይህ ክፍለ ከተማ በዚህ ዙር ያቀረበው መሬትም ይኸው ብቻ ነው፡፡ በኮድ LDR-NIF-IDS-00011950 ስም የቀረበው ይህ ልዩ ቦታ ለኢንደስትሪ አገልግሎት ብቻ የሚውል ነው፡፡ ስፋቱም 7ሺ ስምንት መቶ ሦስት ካሬ ሜትር እንደሆነ ተገልጧል፡፡ አዲሱ ማስተር ፕላን በዚህ የኢንደስትሪ ቦታ እንዲገነባ የሚያዘው የሕንጻ ከፍታ ከ9- እስከ 19 ፎቅ ብቻ ይሁን እንጂ አጫራቾቹ ‹‹ቦታው ለኢንደስትሪ ስለወጣ ባለሐብቱ የሻውን ከፍታ መገንባት ይችላል›› ብለዋል፡፡
የዚህ ግዙፍ ቦታ አሸናፊ ዲሰንት ኢንደስትሪያል ግሩፕ ሲሆን ለካሬ 11900 ብር አቅርቦ ጠቅላላውን በ92 ሚሊዮን 820ሺ ብር ጠቅልሎታል፡፡