ዋዜማ ራዲዮ- የጉለሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ይዞታ አስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊ (ስማቸው የተሸሸገ) ከተቀጣባቸው የግድያ ሙከራ ያመለጡት በስራ ባልደረቦቻቸው ርብርብ ነው፡፡ አርብ ማለዳ እንደወትሮው በሥራ ገበታቸው ላይ የነበሩት ኃላፊው ያልጠበቁት ዱብዕዳ የገጠማቸው በገዛ ቢሯቸው ሳሉ ነበር፡፡ ለረዥም ጊዜያት የሚመላለሰው ባለጉዳይ ወደ ቢሯቸው ዘው ብሎ ሲገባ ፀሐፊያቸው እንኳን በቦታዋ አልነበረችም፡፡ ግለሰቡ ወዲያውኑ ከኮቱ እጀታ የሸሸገውን ስለት መዞ በማውጣት ሰውየው ከቦታቸው እንዳይንቀሳቀሱ ያዛቸዋል፡፡ ቀጥሎም በአነስተኛ ጄሪካን የያዘውን ቤንዝል ላያቸው ላይ አርከፍክፎ ከጨረሰ በኋላ ክብሪት ከኪሱ በማውጣት ለመለኮስ በዝግጅት ላይ ሳለ ዕይታን በማይጋርደው ቢሯቸው ማዶ የነበሩ ባለጉዳዮች ደርሰው ታድገዋቸዋል፡፡
ኃላፊው ይህ ሁሉ ሲሆን አንድም የይድረሱልኝ ድምጽ ለምን ለማሰማት እንዳልቻሉ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ምናልባት በሁኔታው ክፉኛ ሳይደናገጡ እንዳልቀረና እየሆነ ያለው ነገር ሊገለጥላቸው እንዳልቻ ይገመታል፡፡ ባለጉዳዮች እንዲሁም ጥቂት የሥራ ባለደረቦቻቸው በፍጥነት በሩን ሰብረው መግባት ባይችሉና ባይታደጓቸው ኖሮ የከፋ አደጋ ይደርስ እንደነበረ የዋዜማ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
የግድያ ሙከራ ፈጻሚው ለረዥም ጊዜያት የካርታ ይታተምልኝ ጥያቄ ሲያቀርብ እንደቆየና ምላሽ እንዳላገኘ የተናገሩት ምንጮች ሆኖም ግን ኃላፊው ዘንድ አንድም ጊዜ ገብቶ እንደማያውቅና እርሳቸውም ለጉዳዩ እንግዳ እንደነበሩ ተመልክቷል፡፡ ግለሰቡ ከቢሯቸው ተይዞ ከወጣ በኋላ የጥበቃ ባልደረቦች ተኩስ ማሰማታቸውን እንዲሁም በግለሰቡ ላይ ከፍተኛ ድብደባ ማድረሳቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ባለጉዳይ በሚበዛባቸው በተለይም በጉምሩክ፣ በወረዳና በክፍለከተሞች አካባቢ ከፍተኛ የሕዝብ እሮሮ የሚሰማ ሲሆን የመልካም አስተዳደር እጦት የሚያስከትለው ብሶት መልኩን እየቀረ እንደመጣ ማሳያ ሆኖ የሚወሰድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በአራዳ ክፍለከተማ ወረዳ 3 አንድ ባለጉዳይ የጽሐፈት ቤቱን ኃላፊ ‹‹ለ3 ዓመታት ያለአግባብ አንከራቶኛል›› በማለት በሽጉጥ ለመግደል ሙከራ ሲያደርግ ኃላፊው በመስኮት ዘለው መትረፍ ችለው ነበር፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ የቀርሳና ኩንተማ ነዋሪዎች ሊያነጋግራቸው የመጣውን የወረዳ 1 አስተዳዳሪ ደብድበው መግደላቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ እነዚህን ክስተቶች ተከትሎ በወረዳና ክፍለከተማ መዋቅር ያሉ ኃላፊዎች ጥበቃ እንዲጠናከርላቸው ባሳለፍነው ሳምንት ለከንቲባው የድርጅት ኃላፊ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ከጥያቄ አቅራቢዎቹ መካከል ሰፊ የማስፋፊያ ቦታዎች ባለቤት እንደሆነ የሚነገርለትን የአቃቂ ቃሊቲ መሬት አስተዳደር ኃላፊ እንደሆነ የገለፀ የመሬት ባለሞያ እንዳለው ‹‹በየጊዜው ከገበሬዎች ዛቻና መስፈራሪያ እየደረሰብኝ ነው፡፡ እስከመቼ ነው በዚህ ዉጥረት ሥራዬን የምሰራው- ወይ አስታጥቁን፣ ወይ ጠበቃ መድቡልን›› በማለት አስተያየት መስጠቱን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ መስተዳደር ሕገወጥ ግንባታ በሚል ምክንያት ከሚፈርሱ ቤቶች ጋር ተያይዞ በነዋሪዎችና በኃላፊዎች መካከል ከፍተኛ ውጥረት ሲፈጠር እንደቆየ የሚታወስ ነው፡፡