- አስመራና አዲስ አበባ በስብሰባ ተጠምደዋል
- ኤርትራ በግጭቱ ዙሪያ የተብራራ መግለጫ ልትሰጥ ነው
ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር የተቀሰቀሰው ግጭት ጋብ ቢልም አሁንም የከባድ መሳሪያ ተኩስ አልፎ አልፎ እንደሚሰማ ምንጮች ለዋዜማ ገለጹ፡፡ በፆረና ድንበር አቅራቢያ በሚገኙ ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎች ትናንት ለሊቱን ከኢትዮጵያ ወገን የሚተኮሱ ከባድ መሳሪያዎችን ሲሰሙ እንዳደሩ ተናግረዋል፡፡
በአስመራ የኤርትራ መንግስት ወታደራዊና ሲቪል ባለስልጣናት በውቅታዊ ሁኔታ ላይ ምክክር ማድረጋቸውንና ኢትዮጵያ ሙሉ ወረራ ብትፈፅም መወሰድ ባለበት እርምጃ ላይ ዕቅድ አውጥተዋል። አሁን ከተፈፀመው ግጭት ጋር በተያያዘ በኤርትራ በኩል የተፈጠረውን ግርታ ለማረጋጋት ሰፊ የህዝብ ግንኙነት ስራ መሰራት እንዳለበትና የተብራራ መግለጫ እንዲሰጥ ተወስኗል።
በዚህ ሰሞን በስደት ላይ ህይወታቸውን ያጡ ኤርትራውያን መርዶ የመዲናይቱን የማስታወቂያ ስሌዳ ያጨናነቀው መሆኑ የፈጠረው የብሶት ስሜት የአስመራን ባለስልጣናት ስጋት ላይ ጥሏቸዋል። ይህን በሀገር ቤት ያለ ብሶት ለማረጋጋት በመገናኛ ብዙሀን የማረጋጋት ስራ እንዲስራ ዕቅድ ወጥቷል።
በኢትዮጵያ በኩል በየዕዙ ላሉ ባለማዕረግ ወታደራዊ መኮንኖች በሶማሊያ አልሸባብ የፈፀመውን ጥቃት ጨምሮ ከኤርትራ ጋር ስለተፈጠረው ግጭት ገለፃ መደረጉን ለዋዜማ የደረስው መረጃ ያመለክታል። በጠቅላይ ሚንስትር ፅህፈት ቤትም የወታደራዊ ደህንነት ክፍልን ያካተተ ስብሰባ ዛሬ መደረጉን ተገንዝበናል፣ ዝርዝሩን ለማግኘት እንሞክራለን።
በድንበር አካባቢ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ፣ ዛሬ ንጋት እና ጠዋቱን ረገብ ያለው ተኩስ ወደ ሶስት ሰዓት ግድም መልሶ እንዳገረሸበት ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ አካባቢው በተረጋጋ ሁኔታ ለሰዓታት ቢቆይም ከሰዓት ወደ ስምንት ሰዓት ገደማ የከባድ መሳሪያ ተኩስ እንደገና መሰማት እንደጀመረ ያስረዳሉ፡፡ ወደ 10 ሰዓት አካባቢ ግን ተኩሱ ጋብ ማለቱን ለዋዜማ አብራርተዋል፡፡
ዛሬ ረፋዱ ላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጋዜጠኞችን በጽህፈት ቤታቸው ጠርተው መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በኢትዮጵያ በኩል ያለው “ኦፕሬሽን” የቆመው “ትናንት ቀትር ላይ ነው” ባይ ናቸው፡፡ በድንበር አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ኤርትራ ዘልቀው ገብተው “ቁልፍ ቦታዎችን” መቆጣጠራቸውን ቢናገሩም ሚኒስትሩ ይህን አስተባብለዋል፡፡
“ወታደሮቻችን ተልዕኳቸውን ፈጽመው በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ወደሚገኘው ካምፓቸው ተመልሰዋል” ሲሉ አቶ ጌታቸው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
ላለፉት ሁለት ቀናት በሁለቱ ሀገራት መካከል ሲካሄድ የነበረውን የተኩስ ልውውጥ “ግጭት” እንጂ “የለየለት ጦርነት” እንዳልሆነ ሚኒስትሩ ቢገልጹም ከተራ ቁርቋሶ ያለፈ እና “ከፍተኛ ውጊያ” እንደነበር ግን አልካዱም፡፡ በኢትዮጵያ በኩል የተወሰደውን እርምጃ “አጸፋዊ” እና “ተመጣጣኝ” በማለት በተደጋጋሚ ሲጠሩት ተስተውለዋል፡፡
“በአስመራ ለሚገኘው አገዛዝ በቂ እና ግልጽ የሆነ መልዕክት ልከናል” በማለት ባለፉት ሁለት ቀናት ከተወሰደው እርምጃ የኤርትራ መንግስት በቂ ትምህርት እንደሚወስድ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡ የኤርትራ መንግስት ይህን ግጭት የቀሰቀሰው “በተሳሳተ ስሌት ላይ ተመስርቶ ነው” የሚሉት አቶ ጌታቸው በኢትዮጵያ መንግስት የተወሰደው አጸፋዊ እርምጃ በኤርትራ ዘንድ “ያልተጠበቀ” እንደነበር አስረድተዋል፡፡
“በእነሱ ስሌት መሰረት የእኛ ኃይሎች እዚህም እዚያም በተከሰቱ ተግዳሮቶች ስለተወጠሩ ከአስመራ መንግስት የሚሰነዘር ማንኛውንም ዓይነት ትንኮሳ የመመለስ አቅም የላቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት እርምጃ መውሰደን ነበረብን” ሲሉ ለግጭቱ መንስኤ ነው የሚሉትን ምክንያት ጠቅሰዋል፡፡ ከሁለቱ ሀገራት ማን ቀድሞ ጥይት እንዳስጮኸ ለተጠየቁት “ኢትዮጵያ ቀድማ እንዳልተኮሰች” በመግለጽ ኤርትራን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ የኤርትራ መንግስት እሁድ ምሽት እና በዛሬው ዕለት ባወጣቸው መግለጫዎች ግን “ግጭቱን የቀሰቀሰችውኢትዮጵያ ነች” ሲል ከሷል፡፡
በሁለቱ ቀናት ግጭት በሁለቱም ወገኖች ሰዎች መጎዳታቸውን ያመኑት ሚኒስትሩ የሟቾቹን እና የቁስለኞችን ቁጥር ከመናገር ታቅበዋል፡፡ በድንበር አቅራቢያ ባሉ ከተሞች ግን በግጭቱ ውስጥ ተሳትፎ ያልነበራቸው ኢትዮጵያውያን ሲቪሎች ላይ ጭምር ጉዳት መድረሱ በስፋት እየተናፈሰ ይገኛል፡፡
በግጭቱ የሚደርሰውን ጉዳት በመፍራት በድንበር አቅራቢያ በሚገኙ እንደ እገላ ባሉ አነስተኛ ከተማዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው በሌላ ቦታ ወዳሉ ዘመዶቻቸው እና ጓደኞቻቸው ጋር ሄደው ነበር፡፡ በእገላ ያሉ የዋዜማ ምንጮች እንደተናገሩት አካባቢውን ለቅቀው የነበሩ የመንግስት ሰራተኞች ዛሬ ወደ ስራ ገበታቸው ተመልሰዋል፡፡ ግጭቱ ጋብ ማለቱን ሰሙ ሌሎች ነዋሪዎችም ወደ ቦታው በመመለስ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ወደ መኖሪያ ስፍራቸው በሚለሱም በድንበር አካባቢ ያለው ውጥረት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ለጊዜው ወደ ለየለት ጦርነት የማምራት አዝማሚያ ባይታይበትም ኢትዮጵያ ግን ጥቃት ከተፈጸመባት ምላሽ ከመስጠት ወደ ኋላ እንደማትል አስጠንቅቃለች፡፡ “ቀጣዩ ሂደት ሙሉ ለሙሉ የሚወሰነው አስመራ በሚገኘው አገዛዝ ነው” ስትልም በኮምኒኬሽን ሚኒስትሯ በኩል አሳውቃለች፡፡
“እኛ የለየለት ጦርነት የማካሄድ አቅም አለን” የሚሉት አቶ ጌታቸው “ይህንን የማናደርገው ግን ስላልመረጥነው ነው” ሲሉ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክታቸውን ለኤርትራ መንግስት አስተላልፈዋል፡፡