የተከበራችሁ የዋዜማ ራዲዮ ታዳሚዎች- የጦማሬ አንባቢዎች!
የተከበራችሁ ጭቆናን የሚቋቋም ደንዳና ትከሻ ባለቤቶች!
የተከበራችሁ የ40-60 ተመዝጋቢዎች!
የተከበራችሁ የ80-20 ነባር ተመዝጋቢዎች!
የተከበራችሁ የ90-10 የድሀ ድሃዎች!
ክቡራትና ክቡራን!
ኮንዶሚንየም እስኪደርሳችሁ የኢዮብን ትዕግስት ባስናቀ ሁኔታ ላለፉት አስር ዓመታት እየጠበቃችሁ ያለበት ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ገዢዎቻችሁም የናንተን ለከት የለሽ ትዕግስት አድንቀው ሕልማችሁን እውን ለማድረግ ተኝተው እንደማያውቁ እየነገሩ ሲደልሏችሁ እንደኖሩም ይታወቃል፡፡ አልፎ ተርፎም ‹‹የትም ዓለም ለዜጎቹ ቤት የሠራ መንግሥት የለም›› ሲሉ የሚታበዩባችሁ ባለሥልጣናት እንዳሉም ደርሰንበታል፡፡ ጌታዬ! ለመሆኑ እስከመቼ ነው በዚህ ሁኔታ ለመታገስ የወሰኑት? ሌላ 25 ዓመት? በዕድሜዎ ላይ ሌላ 25 ዓመት ሲጨምሩ እኮ ምናልባትም የኮንዶሚንየሙ መሠረት ሳይቀበር እርስዎ ሊቀበሩ ይችላሉ፡፡ የሆነ ነገር ማድረግ ያለብዎ አይመስልዎትም?
(ጦማሩ በድምፅ ተሰናድቶ እዚህ ያድምጡት አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ)
የተከበራችሁ የመንግሥተ-ኮንዶሚንየም ወራሾች!
የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ‹‹የቤት ባለቤት ልናደርግዎ ተቃርበናል›› ሲሉ ምን ማለታቸው ይመስልዎታል? ከርስዎ ባላውቅም፣ እንደኔ ትርጓሜ ግን ‹‹እርስዎ ተገዢ፣ እኛ ገዢ ሆነን አብረን ለዘላለሙ እናዝግም›› ማለታቸው ይመስለኛል፡፡
ለመሆኑ ይህንን ደረቅ ተስፋ ነጋ ጠባ የሚመግቧችሁ ገዢዎቻችሁ የኔ የሚሉት ቤት አላቸውን? ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ገዢዎቻችን ቤትስ አልነበራቸውም፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት የኪራይ ቤቶች አስተዳደር በቸርነቱ በለገሳቸው መለስተኛ ቪላ ቤቶች ዉስጥ ሲጉላሉ ነው የኖሩት፡፡ በስማቸው አንድም ጎጆ ኖሯቸው አያውቁም፡፡ በቤተዘመዶቻቸው እንጂ!
‹‹አሁንስ?›› አትሉኝም፡፡ አሁንማ በስማቸው ቤት እየገነቡ ነው፡፡ ‹‹እየገነቡ ነው›› አልኳችሁ? ይቅርታ አድርጉልኝ! ‹‹ገንብተው ጨርሰዋል›› ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ ታዲያ ቤት ቢሏችሁ ቤት ነው እንዴ? ፈረንጆቹ ‹‹ማንሽን›› የሚሉት አይነት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ትልቅ ቤት እኛ አገር ገና ስም አልወጣለትም፡፡ ለመግባባት እንዲያመቸን ግን ‹‹ማንሽን›› የሚለውን የፈረንጅ ቃል ‹‹የሚያምነሸንሽ- የሚያንፈላስስ-ቤተ ንጉሥ›› ብለን እንፈታዋለን፡፡ ወደ ታች አንድ ወለል የሚጠልቅ፣ ወደ ላይ 2 ወለል የሚመዘዝ፣ ሳሎኑ እንደ እስስት ከአየር ንብረት ጋር የሚለዋወጥ- ሲበርድ የሚያሞቅ፣ ሲሞቅ የሚያበርድ ‹‹ኤ.ሲ›› የተገጠመለት ቄንጠኛ መኖሪያ ነው፡፡
ውድ የ20-80 ተመዝጋቢዎች!
ለመሆኑ ሳሎን በስንት እንደሚከፈል ታውቃላችሁ? በአንድ ካላችሁ ተሳስታችኋል፡፡ ሳሎን በሦስት ነው የሚከፈለው፡፡ ባሕላዊ ሳሎን፣ ዘመናዊ ሳሎን፣ እና እንግዳ መቀበያ ሳሎን፡፡
ባህላዊ ሳሎን ማለት ከገጠር የመጣ እንግዳ እንደለብ የሚጋልብበት፣ ጫማ ቢያወልቅም ባያወልቅም ግድ የማይልበት፣ ስኒ ተደርድሮ ቡና የሚፈላበት፣ ቃና ቲቪና ሕብረትርዒት የሚከፈትበት፣ ጮክ ብሎ መሳቅና መንጫጫት የሚቻልበት ቦታ ነው፡፡
ዘመናዊ ሳሎን ሲባል ደግሞ ከግድግዳ ይልቅ መስታወት የሚበዛበት፣ የመጋረጃው ዋጋ ከመስታወቱ ዋጋ የሚበልጥበት፣ አጫጭርና ቄንጠኛ ከሰው ቆዳ የተሠሩ የሚመስሉ የሌዘር ሶፋዎች የሚደረደሩበት፣ የራሱ የመመገቢያ ማማ (Dinning) የተበጀለት፣ 60 ኢንችና ከዚያ በላይ የሆነ፣ ከወረቀት የቀጠነ ‹‹ፍላት ስክሪን›› ቲቪ የሚሰቀልበትና ዲኤስቲቪ የሚከፈትበት ቤት ነው፡፡
ሦስተኛውና የመጨረሻው የሳሎን አይነት በተለምዶ የ‹‹እንግዳ መቀበያ ሳሎን›› በሚል የሚታወቅ ሲሆን ብዙዉን ጊዜ ከውጭ አገር የሚመጡ እንግዶችን ለአጭር ጊዜ ተቀብሎ ለማስተናገድ፣ የቢዝነስ ጨዋታ ለማውጋት፣ ወደ ሰገነት የሚያይ ባልኮኒ ያለው፣ ውስኪ የሚደረደርበት ትንሽ የሳሎን ዉስጥ ባር ‘MINI-BAR’ ያለው የሳሎን ዓይነት ነው፡፡
ታዲያ እነዚህ ለሩብ ዓመታት እኛን በመርገጥ የተዳከሙ የኢህአዴግ ጡረተኛ ባለሥልጣናት ከላይ ከተዘረዘሩት የሳሎን አይነቶች የቱን ያስገነቡ ይመስላችኋል? አልተሳሳታችሁም! ሦስቱንም ነው ያስገነቡት፡፡ ባስገነቡት መኖርያ ዉስጥ ሦስቱም የሳሎን ዘሮች ተቆልለዋል፡፡ በአሉላ ጫካ- በ‹‹ጋራ ጉሪ›› ኮረብታ ሰሞኑን ተገንብተው ያተጠናቀቀቱት መምነሽነሻዎች ሦስቱንም የሳሎን ዓይነቶች አካተው የያዙ እንደሆነ ለመመልከት ችያለሁ፡፡ ቻል ያርጉት ጌታው! እርስዎም እኮ ከነርሱ መታጠቢያ ቤት ያልተናነሰ ስቱዲዮ ኮንዶሚንየም ሊደርስዎ ይችላል፡፡ ማን ያውቃል!
ውድ የ40-60 ተመዝጋቢዎች!
ማድቤት በስንት ይከፈላል? በአንድ ካላችሁ ተሳስታችኋል፡፡ ማድቤት በሁለት ነው የሚከፈለው፡፡ ዘመናዊና ባህላዊ፡፡ ዘመናዊ ማድቤት ፒዛ መጋገሪያ ማሽን የተገጠመለት፣ ኬክ መጋገሪያ ማሽን የተበጀለት፣ የቡና ማፍያ ማሽን የተገጠመለት፣ አሳ፣ ስጋና አትክልትን ለረዥም ጊዜ ማቆየት የሚችሉ ማቀዝቀዣዎች (deep freezer) ያለው፣ እንዲሁም መለስተኛ መመገቢያ ጠረጴዛ የሚዘረጋበት ሲሆን ለሽንኩርት መክተፊያ በእብነበረድ የተሠራ ዝርግ ጠረጴዛ ከነሲንኩ በማድቤቱ መሐል ለመሐል ሰንጥቆ የሚያልፍበት የማድቤት ዓይነት (Modern Kitchen) በመባል ይታወቃል፡፡
ባህላዊ ማድቤት የሚባለው ደግሞ የሞሶብ እንጀራ የሚቀመጥበት፣ እንጀራ መጋገሪያ ምጣድ የሚለኮስበት፣ የሀበሻ ወግ አይቅርብኝ የሚባልበት በመክተፊያና በቢላዋ የተሞላ ነው፡፡ Traditional Kitchen ይባላል፡፡
ላለፉት 25 ዓመታት ደከመን ሰለቸን ሳይሉ የገዙን መሳፍንት የቱን የማድቤት አይነት አስገነቡ ይበሉኛ! ሁለቱንም፡፡ የሚገርመው አሁን ቤቱን ገንብተው ባጠናቀቁበት ወቅት ሁለት ማድቤት እንደሚያንሳቸው በመግለጻቸው ሦስተኛ ማድቤት አዋቅረዋል፡፡ ይህ ዋናው የቤታቸው ፕላን ላይ ያልነበረ አዲስ የፕላን ለውጥ እንደሆነ ምንጮቼ ገልጸውልኛል፡፡ ሐሳቡ የመነጨው እንጀራ መጋገሪያው ከባህላዊ ማድቤት ተነጥሎ መገንባት አለበት ከሚል ቅዱስ ሐሳብ ሲሆን ሐሳቡን ያቀረቡት ደግሞ አስር አመታትን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እስክንሰለቻቸው ድረስ በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉን መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ እንደሆኑ ሰምቻለሁ፡፡ ከዚህም የተነሳ ዋናው ቪላ ውስጥ ከሚኖሩት አንድ ዘመናዊና አንድ ባሕላዊ ማድቤቶች በተጨማሪ ሶስተኛ ማድቤቶች በሸክላ ብቻ እየተሰሩ እንደሆነ ተመልክቻለሁ፡፡ ይህ ማድቤት ከጎኑ 4 ክፍሎች ተጨምረውበት ለጊዜው ‹‹የቤተሰብ ሰርቪስ ቤት›› የሚል ታፔላ ተለጥፎበታል፡፡ ከትናንት በስቲያ ስፍራው ተገኝቼ ለማየት እንደቻልኩት ይህ ሸክላ ቤት ወደ ቢጫ የሚያደላ ቀለም እየተቀባ ነበረ፡፡
ውድ የ10-90 የድሀ ድሀዎች!
የ‹‹ድሀ ድሀ›› የሚል አጥንት ድረስ የሚሰማ ስም የሰጧችሁ ባለሥልጣናት ገንብተው እየጨረሱት ያለው ቤት አምስት ሜትር የሚረዝም የራሱ የመብረቅ መከላከያ ተገጥሞለት ከወደላይ ሊመጣ የሚችለውንም ቁጣ ለመመከት በተጠንቀቅ የቆመ ይመስላል። 4 ሰዎችን በአንድ ጊዜ ይዞ የሚምዘገዘግ የራሱ አሳንሰርም አለው። በእንጨትና በአሉሚነም የተንቆጠቆጠው ውድ የመስኮት ፍሬምም ለተመልካች ያሳሳል። ይህን በአካል ተገኝቼ ያረጋገጥኩትን ነገር ስጽፍላችሁ ከብዕሬ ቀለም በላይ የእምባ ዛላዎቼ ብራናዬን እያረጠቡት መሆኑን እንድታውቁልኝ እሻለሁ፡፡
ዉድ የኮንዶሚንየም ምዝገባ ያመለጣችሁ ዜጎች!
ይህ ትግርኛ ተናጋሪ በሆኑ ደርጎች እየተመራ ወደ ኅብረ ብሔራዊ ጨቋኝ ግንባር የተለወጠው ፓርቲ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እንዴት ወደ ቅንጦት ዓለም ለመሸጋገር ወሰነ ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ 13 ሚሊዮን ዜጋ በተራበበት፣ 77 ቢሊዮን ብር በባከነበትና የኮንዶሚኒየም ሕንጻዎች እንደጉም በበነኑበት በዚህ ወቅት የነዚህ ቅንጡ ቤቶች ዜና ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይዛመት ብዙ ተሞክሯል፡፡
ቤቶቹ የሚገኙበት አካባቢ ማንኛውም ፀጉረ ልዉጥ ዝር እንዳይልና ቤቶቹ በሞባይል ፎቶ እንዳይነሱ 13 ለሚሆኑ የቤቱ ጠባቂዎች ጥብቅ መመሪያ ተላልፎ ነበር፡፡ ሆኖም ዘመነ ፌስቡክን መቆጣጠር ምንትስን እንደመቆጣጠር ቀላል አልሆነም፡፡
ለማንኛውም! መሬቱ 10 ሚሊዮን፣ ግንባታው 15 ሚሊዮን፣ የማጠናቀቂያ ወጪው 18 ሚሊዮን በድምሩ ወደ 40 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ግምት የሚሰጠው ይህ የኢህአዴግ መሳፍንት መምነሽነሻ ‹‹ማንሽን›› ለ6 ሹማምንት የተበረከተ የፓርቲው ስጦታ ነው፡፡ ስጦታው ለምንድነው ካላችሁኝ- ስጦታው እኔና እናንተን በታማኝነትና በቅንነት ሰጥ ለጥ አድርገው ላለፉት 25 ዓመታት ስለገዙን የተበረከተላቸው ሽልማት ነው እላችኋለሁ፡፡ በቅርቡም ለሌሎች ተጨማሪ 6 ባለሥልጣናት ይኸው ስጦታ ሊበረክትላቸው የአፈር ምርመራ ለማካሄድ ምክክር ተጀምሯል፡፡
ወገኖቼ!
የግንባታውን አግባብነትና የሚያስወጣውን ወጪ በተመለከተ ከዚህ በፊት በተለያዩ ሚዲያዎች የተዘገበ በመሆኑ እኔ አሁን የምለው የለኝም፡፡ በወቅቱ ሸገር ሬዲዮ የሚመለከታቸውን ባለሥልጣን በማናገር የቤቶቹን ግምት ወደ 25 ሚሊዮን ብር ዝቅ ቢያደርገውም ይህ ግማሽ ዋጋ እንጂ ሙሉ ዋጋው እንዳልሆነ በድህነቴ ልምልላችሁ እችላለሁ፡፡ አንዱ ቤት አሁን በተጠናቀቀበት ሁኔታ ስንት ያወጣል ያላችሁኝ እንደሆን ከ40 ሚሊዮን ብር የማያንስ ግምት እንዳለው ልነግራችሁ እችላለሁ፡፡
ዉድ ጣሪያው የሚያፈስ ኮንዶሚንየም ለመረከብ ያሰፈሰፋችሁ ዜጎች!
ስለምን ታደርቀናለህ? የባለሥልጣኖቻችን ቤቶች ግንባታስ ለኛ ምናችን ነው? እንደምትሉኝ እገምታለሁ፡፡ በኔ እምነት ግን ማወቅ አይከፋም አላለሁ፡፡ ቤቶቹ የደረሱበትን ደረጃና እንዴት እየተፋጠኑ እንደሆነ ብገልጽላችሁ ቢያንስ የኮንዶሚንየም ተስፋችሁን ያለመልመዋል የሚል እሳቤ አለኝ፡፡ ይህንንም ለናንተ በማሰብና በቅንነት ያደረኩት እንደሆነ ልብ እንድትሉልኝ እሻለሁ፡፡
ለማንኛውም አንድ እዚህ ግባ የማይባል ኮንዶሚንየም ለመገንባት ድፍን አስር ዓመት አይወስድም፡፡ ያውም የሚፈርስና የሚያፈስ ኮንዶሚንየም፡፡ አሃ! ይኸው አየና! ስድስት ዉስብስብና ቅንጡ ቤተመንግሥት ለመገንባት የፈጀው ጊዜ 9 ወራት ብቻ እንደሆነ አየና፡፡ ዋናው ከልብ ማልቀስ ነው፡፡
በነገራችሁ ላይ ቤቶቹ ለነዚህ ባለሥልጣናት የሚበረከቱት እንደኪራይ ቤት ቪላ ኖረው ኖረው ከዕለታት አንድ ቀን እንዲለቁት እንዳይመስላችሁ፡፡ እነዚህ ቤቶች ከኢህአዴግ የተበረከቱ ‹‹የዘላለሜ ነሽ›› ስጦዎች ናቸው፡፡ እንኳን ኖረው- ሞተውም የነርሱ ነው፡፡ ለቤተሰቦቻቸው አውርሰውት ሊያሸልቡ መብታቸው ነው፡፡ ይገባቸዋል! እኛን የመሰለ አስቸጋሪ ሕዝብ ሳይሰለቹ ለሩብ ምዕተ ዓመት ያቀኑ እነርሱ አይደሉምን?
የተከበርከው የአዲስ አበባ ሕዝብ ሆይ!
ልክ ልክህን ልንገርህ፡፡ በቤት ኪራይ መሰቃየትህ የሚያበቃበት ጊዜ አልተቃረበም፡፡ ነጻነትህ በእጅግ ነው፡፡ የምትሰሩትን ቤት አቁማቹህ የኛን ቤት አጠናቁልን በል፡፡ ዝም ካልካቸው ያፈርሱሀል፡፡ ባለኝ መረጃ መሰረት መስተዳደሩ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የአዲስ አበባን አንድ ሦስተኛ ነባር ሰፈሮች ለማፍረስ ምስጢራዊ እቅድ ይዟል፡፡
የዚህ የመፍረስ ጭንቅ ከሚያሰቃያቸው ዜጎች መካከል ግንባር ቀደሞቹ የየካ ተራራ ቀደምት ነዋሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ በክፉ ጊዜ እንደ ሽፍታ ተራራ ዉስጥ መሽገው የኖሩ ዜጎች በባለሥልጣናቱ ወደዚህ ጋራጉሪ አሉላ ጫካ መጠጋት ፍርሃት ለቆባቸዋል፡፡ ፍርሃታቸው ምክንያት አለው፡፡
ለጊዜው ባለሥልጣናቱ የተገነቡት ቤተመንግሥቶች ቁጥር 6 ብቻ ነው፡፡ ቴኒስና የዋና ቦታዎችን ጨምሮ የተመደበላቸው የቦታ ስፋት ደግሞ 22ሺ ካሬ ብቻ ነው፡፡ የባለሥልጣናቱ ፍላጎት ደግሞ በዚህ የሚቆም አይደለም፡፡ ይለጠጣል፡፡ ግቢያቸው ዉስጥ ‹‹ሜክሲኮ አደባባይ›› ካልተሰራልን ሊሉ ይችላሉ፡፡ በዚህን ጊዜ የሚፈናቀሉት የቅርብ ጎረቤት የሆኑት የ ‹‹ጋራጉሪ›› ነዋሪዎች ናቸው፡፡ የባለሥልጣናቱ ፍላጎት ምን ማቆሚያ አለው ብላችሁ ነው!
ለምሳሌ ቤቱ ይለገሳቸዋል ተብለው ከሚገመቱት ጄኔራሉ ሳሞራ ዩኑስ አንዱ ናቸው፡፡ ጄኔራል ፕሮፌሰር ሳሞራ፡፡ እሳቸው ደግሞ ጥሎባቸው ጎልፍ ይወዳሉ፡፡ እንዴት አንድ ታጋይ ጎልፍ ሊያፈቅር እንደቻለ ግልፅ ባይሆንም በቀን ዉስጥ ጎልፍ ሳይጫወቱ ከዋሉ እንቅልፍ አይወስዳቸውም ይላሉ፡፡ ለዚያም ነው ዉሎና አዳራቸው ጎልፍ ክለብ የሆነው፡፡ እኚህ የአገር ባለ ውለታ የሆኑ ጄኔራል አሉላ ኮረብታ ላይ በተገነባላቸው ቪላ ዉስጥ ጎልፍ መጫወቻ ይሠራልኝ ካሉ የጋራጉሪ ነዋሪዎች ጉድ ፈላባቸው ማለትም አይደል?
ከሁሉም የሚያሰጋው ደግሞ አሁን ከተገነቡት 6 የጡረተኛ ቤተ መንግሥቶች ሌላ ተጨማሪ 6 ቤቶች ሊገነቡ በጀት ተበጅቶ ማለቁ ነው፡፡ የሕዝብ ሮሮን ለማስቀረት ነገሩ በምስጢር እንዲያዝ ተብሏል፡፡ ከ22ሺ ካሬ ሜትር ቦታ የተረፈው ደግሞ 6 ቤቶችን የሚያሰራ አይደለም፡፡ ስለዚህ የጋራ ጉሪ ነዋሪዎች ተጠጋጉ መባላቸው የማይቀር ነው፡፡ ምን እንደሚሻላቸው እንጃ! ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ነበር ተረቱ…
ዉድ ታጋሽ አንባቢዎቼ!
የኮንዶሚንየም ተመዝጋቢ ጆሮ ይደፈንና ስድስቱ ቤተ መንግሥታት የማጠናቀቂያ ሥራቸው የሚያስገርም ነው፡፡ በዉድ የእንጨት ቅብ አሉሚነም አጊጠው፣ የመብረቅ መከላከያ ቀስት ተወድሮላቸው፣ 10ሺ ሊትር የሚይዝ ታንከር ተሰቅሎባቸው፣ በአሁኑ ሰዓት የቤት ዉስጥ ዕቃዎቻቸው ከቱርክና ከጣሊያን እየተጫኑላቸው መሆኑን ሰምቻለሁ። ወደ ቤቶቹ የሚወስደውም ጊዜያዊ ጥርጊያ መንገድ ጥቂት ሚሊዮን ብር ፈሶበት ከሰሞኑ መሠራቱንም ለጉድ በተሰራው ዐይኔ ተመልክቻለሁ፡፡ ጥርጊያ መንገዱ እንዳይናድ የሚያደርግ 150 ሜትር ኮንክሪት ፣ ሰባት ሜትር ከፍታ ያለው ዉድ የኮንክሪት ሙሊት (shear Wall) የተካሄደ ሲሆን የዚህ ወጪ በትንሹ አስራ ሦስት የኮንዶሚንየም ብሎኮችን ገንብቶ እንደሚጨርስ ተረድቻለሁ፡፡
የ6ቱ ቤቶች ግንባታ ሙሉ በሙሉ በተክለብርሃን አምባዬ የተጠናቀቀ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በቀን በሁለት ፈረቃ በሚውሉበት የሴት ሠራተኞች ጉልበትም የቤቶቹ ሁሉም ክፍሎች ወለል እየጸዳ እንደሚገኝም ተመልክቻለሁ፡፡ የሚገርመው በቦታው በማንኛውም ሰዓት የሚያልፍ ሰው ቤቶቹ በብዙ ሴቶች ርብርብ እየፀዱ መሆናቸውን መመልከቱ ልዩ ትንግርት ላይኾንበት አይችልም፡፡
አንዳንድ የአካባቢው ሀብታሞች ነገሩ ግራ አጋብቷቸው ፎቶ ለማንሳት በመሞከራቸው ከጥበቃዎች ጋር እንካሰላንቲያ ዉስጥ መግባታቸው ተነግሮኛል፡፡ ይህ ጽዳት ላለፉት 2 ወራት የቀጠለ ተግባር እንደኾነም ተነግሮኛል።
ወደ ቤቶቹ የሚያስገባው መንገድ ተራራማ በመሆኑ ለአስፋልት ግንባታ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኾኖም ጀግናው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ እንዲገነባው ስምምነት ተደርጓል መባሉን ሰምቻለሁ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አፋር ክልል ወደ ዳሎል የሚወስደውን አስቸጋሪ አስፋልት አስቸጋሪውን የአየር ንብረት ተቋቁሞ የሠራው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡
ክቡራትና ክቡራን!
መኖርያ ቤቶቹ ለየትኞቹ ባለሥልጣናት ነው የሚታደሉት የሚለውን መልስ ለማግኘት ባደረኩት ያላሰለሰ ጥረት ብዙም የሚያስመካ መረጃ ባላገኝም፥ ከሁለት ሳምንታት በፊት ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ከታች በስም የተዘረዘሩት ባለሥልጣናት ቤቶቹን ለመጎብኘት በሁለት ዙር መጥጠው እንደነበር አንድ ትልቅ ሰው ሹክ ብለውኛል፡፡ የመጡት ሁሉ የቤቶቹ ባለቤት ናቸው ማለት እንዳልኾነ ማሳሰብ እሻለሁ፡፡
1ኛ. ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ
2ኛ. አቶ አዲሱ ለገሰ
3ኛ. አቶ በረከት ስምኦን
4ኛ. መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ
5ኛ. አቦይ ስብሐት ነጋ
6ኛ. ወይዘሮ አዜብ መስፍን
7ኛ. አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ
8ኛ. አምባሳደር ስዩም መስፍን
9ኛ. አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ
10ኛ. አምባሳደር ካሱ ኢላላ (ዶክተር)
======================
አውግቸው ቶላ ነኝ
ለዋዜማ ራዲዮ