ዋዜማ – በዚህ ሳምንት ማገባደጃ ላይ ኢትዮጵያ በፀጥታ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ሁለት ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ስብሰባዎችን ታስተናግዳለች። ሀሙስ እና አርብ በአዲስ አበባ እንደሚደረግ የሚጠበቀው ሙኒክ ሰኪዩሪቲ ኮንፍረንስ (Munich Security Conference) በአፍሪካ መሬት ላይ ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ቅዳሜ እና እሁድ ባህር ዳር ላይ የሚከትመው የጣና ፎረም ደግሞ በተከታታይ መካሄድ ከጀመረ አምስት አመት ደፍኗል።
የአዲስ አበባው ስብሰባ ከተመሰረተ ግማሽ ምዕተ ዓመት በሆነው የሙኒክ ሰኪዩሪቲ ኮንፍረንስ (Munich Security Conference) አዘጋጆች አማካኝነት የሚደረግ ነው። በሙኒክ (ጀርመን) በየዓመቱ የሚካሄደው ኮንፍረንስ በውጭ ጉዳይ እና ፀጥታ ፖሊሲዎች ዙሪያ ከሚመከርባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ሁነኛ የሚባል ነው። እ.ኤ.አ ከ2009 ጀምሮ ደግሞ በተለያዩ ሀገራት ባሉ ዋና ከተሞች ጥቂት ግን ወሳኝ ሰዎች የሚሳተፉባቸው ተመሳሳይ መለስተኛ ስብሰባዎች መካሄድ ጀምረዋል።
አዲስ አበባ የምታስተናግደውም እነዚህን “Core Group Meetings” በመባል ከሚታወቁት እና በየአካባቢው ባሉ አሳሳቢ የፀጥታ ጉዳዩች ላይ ከፍተኛ አመራሮችን በአንድ ጠረጴዛ ከሚያሳትፉ መለስተኛ ስብሰባዎች አንዱን ነው። ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሞስኮ፣ ቤይጂንግ፣ ዶሃ፣ ኒው ዴልሂ፣ ቬይና እና ቴህራን መሰል ስብሰባዎችን ያስተናገዱ ከተሞች ናቸው።
ከሁለት ወር በፊት በዋናው የሙኒክ ስብሰባ ዋና አጀንዳ የነበረው እና አውሮፓን ሰቅዞ የያዛት የስደተኞች ጉዳይ በአዲስ አበባውም ስብሰባ ዋና መነጋገሪያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በስብሰባው የስደተኞችን ፍልሰት መከላከል እና መቆጣጠር ጉዳይ ከሽብርተኝነት እና ፅንፈኝነትን መዋጋት እኩል ቀዳሚ ትኩረት አግኝቷል።
ከአፍሪካ፣ አውሮፓ እና አሜሪካ የተውጣጡ ወደ ስድሳ ግድም ከፍተኛ አመራሮች ይሳተፉበታል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሃኖም ትወከላለች። ዓመታዊውን ኮንፍረንስ የጠነሰሰችው ጀርመን የቀድሞ ፕሬዝዳንቷን ሆረስት ኮህለርን፣ የቻንስለር ሜርኬል የአፍሪካ ጉዳዩች ሹም ጉንተር ኑክ፣ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ማርከስ ኤደረርን እና በጀርመን ፓርላማ የውጭ ጉዳዩች ኮሚቴ ሊቀመንበር ኖበርት ሮትገንን ትልካለች።
በስብሰባው ይገኛሉ ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥ የጋና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የማሊ እና ቻድ መከላከያ ሚኒስትሮች፣ የሞሮኮ ካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር፣ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል እና በዓለም የወንጀል ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ህግ የሆኑት ካሜሮናዊቷ ፋቶ ቤንሱዳ ይገኙበታል።
የሙኒኩ ስብሰባ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ከፍተኛ ስራ የሰሩት በአፍሪካ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው የጣና ፎረም የቦርድ አባላት እንደሆኑ ምንጮች ይጠቁማሉ። የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ ከእነዚህ መካከል ይጠቀሳሉ። የባህር ዳሩ የአዲስ አበባውን ተከትሎ እንዲከናወን መደረጉም ለዚያ ነው።
በየዓመቱ ጣና ሀይቅ ዳር ለስብሰባ የሚቀመጡት እነ ኦባሳንጆ ለዚህ ዓመት የመረጡት መወያያ አፍሪካ ከዓለም አቀፍ የፀጥታ አጀንዳ አንፃር እንዴት ትታያለች የሚለውን ነው። የአፍሪካ የፀጥታ ተግዳሮቶች ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቦ ሳለ አህጉሪቱ በጉዳዮቹ ላይ ያላት አተያይ እና ልምድ በበቂ ሁኔታ ጥቅም ላይ ያለመዋሉ ምክንያት የስብሰባው ማጠንጠኛ ጭብጥ ይሆናል።
“በጭብጥ ደረጃ የዚህ ዓመቱ ስብሰባ እስከዛሬ ከነበሩት ሳቢ ነው” ትላለች ባለፉት አራት ዓመታት በፎረሙን የተሳተፈች ባለሙያ።
ቅዳሜ በሚከፈተው ስብሰባ ዋና ተናጋሪ እንደሚሆኑ የሚጠበቁት የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ ኮፊ አናን ናቸው። ከእርሳቸው በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ጨምሮ ስምንት የመንግስታት መሪዎች ጣና ፎረምን እንደሚታደሙ ማረጋገጫ መስጠታቸውን የዋዜማ ምንጮች ይገልጻሉ።