- ከሰሞኑ የህዝብ ትራንስፖርት ዋጋ ቅናሽ ተደርጎ ነበር
(ዋዜማ ራዲዮ)-የነዳጅ ዘይት ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቢያሽቆለቁልም… ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሽያጩ በቀድሞው ዋጋ ቀጥሎ ሠንብቷል። በትላልቅ ከተማዎች ለወራት የነዳጅ እጥረት ችግር ለመታየቱ የተለያዩ ምክንያቶች ይቀርባሉ። ከሰሞኑ ደግሞ የነዳጅ ዋጋ ላይ ቅናሽ መደረጉ ታውቋል። የቤንዚን ዋጋ በሊትር 82 ሳንቲም ቅናሽ መደረጉን “ከአህጉሪቱ ትልቁ ቅናሽ” መሆኑ በመንግስት ተጠቅሷል። ያለፉትን ጊዜያት የዓለም ነዳጅ ዋጋ አወራረድና የኢትዮጵያ መንግስት ተመን የተከታተሉ ወገኖች ደግሞ የነዳጅ ዋጋ በሊትር የሚሸጥበት 17 ብር ላይ ቢያንስ የ7 ብር ቅናሽ ማሳየት እንደነበረበት ያስረዳሉ። የነዳጅ ዋጋ ሲቀንስ የትራንስፖርት ታሪፍ መቀነሱ የተለመደ ሆኖ ቢዘልቅም… አሁን ግን በአዲስ አበባ የታክሲ ታሪፍ መጨመር የሚያስችል ጥናት መጠናቀቁን መረጃዎች ያመላክታሉ።
[ዳንኤል ድርሻ ያዘጋጀውን መሰሉ ንጉስ ታቀርበዋለች፡አድምጡት]
በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ መውጣት መውረድ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖው ቀላል አይደለም፡፡ የነዳጅ ገበያ መዋዠቅ ፤ በግብርና ምርት፣ በማዳበሪያ፣ በትራንስፖርት እና በሌሎችም ዘርፎች ላይ የዋጋ ለውጥ እንዲከተል አቢይ ሚና ይጫወታል ፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው ያለማቋረጥ እያሽቆለቆለ ሲሄድ ፤ በነበረበት የዘለቀው የኢትዮጵያ ነዳጅና የትራንስፖርት ዋጋ ከሰሞኑ ተከልሷል፡፡ አምና በዚህ ወቅት አንድ በርሜል ድፍድፍ ዘይት በአማካኝ ይሸጥ ከነበረበት ከ 60 ዶላር በግማሽ ወርዶ በአሁኑ ወቅት ወደ 30 ዶላር አካባቢ ወርዶ እየተሸጠ ነው ፡፡ ይሕ ከተገለጸ ከቀናት በኋላ ግን በአዲስ አበባ በቅርቡ እንደገና የታክሲ ትራንስፖርት ዋጋ ይጨምራል መባሉ ግን ግርታ ፈጥሯል፡፡
በ2006 በጀት ዓመት 10 የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች በመላ ኢትዮጵያ በሚገኙ 660 ማደያዎቻቸው 2.6 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ አከፋፍለዋል፡፡ በ2007 ደግሞ የሃገሪቱ ብቸኛ ነዳጅ አስመጪ ኢንተርፕራይዝ 2.8 ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ወደ ሃገር አስገብቷል፡፡ ከአጠቃላይ ፍጆታ 75 ከመቶ የሚሆነው ቤንዚን የሚገባው ከሱዳን ሲሆን፣ እንደ ኪሮዚንና የአውሮፕላን ነዳጅ የመሳሰሉ ምርቶች ግዢ ደግሞ ከኩዌት፣ ሳዑዲ አረቢያና ሌሎች የባሕረ ሠላጤው ሃገራት ይከናወናል፡፡ የነዳጅ ፍላጎት በ12 ከመቶ እየጨመረ መሄድ ከአቅርቦቱ ጋር አለመመጣጠኑ በየጊዜው ለሚስተዋለው የነዳጅ እጥረት በምክንትነት ይጠቀሳል፡፡
የነዳጅ ዘይት ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአንድ ዓመት ተኩል በማያቋርጥ ሂደት እያሽቆለቁል ሄዶ፣ አሁን ከ30 ዶላር አካባቢ ይሸጣል፡፡ ወደ ፊት 20 ዶላር ሊደርስ እንደሚችል የሚተነብዩም አሉ ፡፡ ዋጋው ከ18 ወራት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በሁለት ሦስተኛ መቀነሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ዋጋው በዓለም ደረጃ እንዲህ ሲቀንስ በዚያው መጠን በሀገር ውስጥ እንዲቀንስ አለመደረጉ በሕዝብና በሃገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ማስከተሉን ኢኮኖሚስቶች በተለያዩ ጊዜያት ተናግረዋል ፡፡ በሌላ በኩል ግን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ እንደሚሉት መንግስት በነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ ላይ ያደረገው የዋጋ ማስተካከያ መረጋጋት እንደፈጠረ፣ በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ መሸጫ ዋጋም በአፍሪካ ዝቅተኛ የሚባል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የንግድ ሚኒስቴር ከየካቲት 2008 መግቢያ ጀምሮ የ1 ሊትር ቤንዚን መሸጫ ከ17 ብር ከ43 ሳንቲም ወደ 16 ብር ከ61 ሳንቲም መውረዱን አሳውቋል፡፡ በግልጽ እንደሚስተዋለው የተደረገው ቅናሽ የ82 ሳንቲም ቢሆንም፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ባሰራጨው መግለጫ ግን የገለጸው በቤንዚን ላይ የ1 ብር ከ35 ሳንቲም ቅናሽ መደረጉን ነው ፡፡ በተመኑ መሰረት ነጭ ናፍጣ (በሊትር) 14 ብር ከ16፣ ኪሮሲን 12 ብር ከ43፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 12 ብር ከ42፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ 11 ብር ከ77 ሳንቲም ይሸጣሉ፡፡
የትራንስፖርት ባለሥልጣንም የትራንስፖርት ታሪፍ መቀሱን ገልጿል፤ 1 ብር ከ 40 ሳንቲም የነበረው አጭር ርቀት የከተማ ሚኒባስ ታሪፍ ወደ 1 ብር ከ35 ሳንቲም ሲቀንስ፣ 4 ብር ከ80 ይከፈልበት ለነበረው ርቀት የ20 ሳንቲም ቅናሽ ተደርጎበታል፤ 1 ብር ከ 95 ሳንቲም የነበረው የሚዲ ባስ ዋጋ ወደ 1 ብር ከ 85 ሳንቲም ወርዷል፤ 4 ብር ከ80 ሳንቲም የነበረው አራት ብር ከ60 ሳንቲም ሆኗል። አንበሳ አውቶቡስ እስከ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር ርቀት 1 ብር ከ50 የነበረው የ10 ሳንቲም ቅናሽ ሲደረግበት፣ 8 ብር ከ75 ሳንቲም ይከፈልበት የነበረው ርቀት ላይ ሃምሳ ሳንቲም ተቀንሷል፡፡
የሃገር ውስጥ የነዳጅና የትራንስፖርት ታሪፍ ቅነሳ መረጃው ከተነገረ ከጥቂት ቀናት በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ የታክሲ ታሪፍ የሚጨምረው ከነዳጅ ዋጋ ጋር በተያያዘ አይደለም ተብሏል፤ የታክሲ ባለንብረቶች ማሕበራት አቅርበውታል ለተባለው የጭማሪ ጥያቄ የመኪና መለዋወጫዎች እና የጎማ ዋጋ መወደድ የመሳሰሉ ጉዳዮች ተጠቅሰዋል፡፡
በ2002 ዓ.ም የተመሰረተው የአዲስ አበባ ታክሲ ባለንብረቶች ማህበር በአምስት ዞኖች የተዋቀሩ 13 ማህበራት አሉት። ማሕበራቱ የገዢው ፓርቲ ፖለቲካ ማስፈጸሚያ ከመሆን ባለፈ፣ የከተማይቱን ትራንስፖርት ችግር መቅረፍ አለመቻሉም ይነገራል፡፡ በከተማዋ ከ 11 ሺህ ባላይ -ከ12 ወንበር በላይ ያላቸው አውቶቡሶች እና ከ 23 ሺህ የሚበልጡ -ከ11 ወንበር በታች ያላቸው ታክሲዎች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ 12 ሺህ ባለንብረቶችን በአባልነት ይዘው የነበሩት ማሕበራት በአሁኑ ወቅት ከስድስት ሺህ የማይበልጡ ሰዎችን ብቻ ነው በአባልነት የያዙት፡፡ አብዛኛዎቹ ማሕበራት በስድስት ዓመት ቆይታቸው አንድ ጊዜ እንኳ ኦዲት ሳይደረጉ ሕልውናቸው አለማክተሙ በመንግስት በክፉ ላለመታየታቸው እንደ አብነት ይቀርባል፡፡ እነዚህ ማሕበራት የ“ጎማና መለዋወጫ ዋጋ ተወደደብን” ጥያቄ፣ ለታሪፍ ጭማሪ ጥናት ተቀባይነት ማግኘቱ “ያልተለመደ” መሆኑም ተወስቷል፡፡
የታሪፍ ክለሳውን ያጠናው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ነው ፡፡ ጉዳዩን ለውሳኔ ወደ ፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን እንደላከውም ታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፍ አስተዳደር እና ቁጥጥር ሥራን በበላይነት የሚመራው ይኸው የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ነው፡፡ ከባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የተገኘ ሠነድ፣ የታክሲ ታሪፍ ክለሳ በሶስት ነጥቦች ላይ ብቻ መመስረቱን ያረጋግጣል፡፡ የነዳጅ ዋጋ፣ የተሽከርካሪው ሰው የመጫን ልክ እና ከመነሻ እስከ መድረሻ ያለ ርቀት፡፡ ለ“ሠንደቅ” ጋዜጣ ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ “እስከዛሬ የታክሲ ዋጋ የነዳጅ ታሪፍን መሰረት ባደረገ መንገድ ብቻ እንደነበር” በመጠቆም በሠነዱ የተጠቀሰውን አሰራር ትክክለኛነት አረጋግጠዋል፡፡ አቶ ያብባል አክለውም የዋጋ ጭማሪው አይቀሬ መሆኑን፣ በፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን በሚወሰንበት ወቅት፣ ጭማሪው በተጠቃሚው ህዝብ ላይ አለበለዚያም ደግሞ መንግስት ላይ ሊያርፍ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ አስተያየት ሠጪዎች ደግሞ መንግስት ወጪውን የመሸከም ፍላጎት ቢኖረው መረጃው አደባባይ እንዲወጣ ባላደረገ ነበር ይላሉ፡፡ የዓለም ነዳጅ እየቀነሰ ሲሄድ የሚገባውን ታሪፍ ቅነሳ ያላደረገው መንግስት፣ አሁን ሊጨምረው ያቀደው የታሪፍ ጭማሪ አሳማኝ ምክንያት የማይቀርብበት መሆኑም ተነግሯል፡፡
በ marketwatch.com መረጃ መሰረት በሕዳር 2006 ድፍድፍ ነዳጅ በበርሜል ከ80 እስከ 90 ዶላር ይሸጥ ነበር ፡፡ በጥር 2007 ግን ወደ 52 ዶላር ወርዷል፡፡ ከጥር 2007 አንስቶ እስካለፈው ወር ድረስ የቀጠለው የሃገር ውስጥ ነዳጅ መሸጫ ታሪፍ ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ተመሳሳይ እንደነበር ተጠቅሷል፤ ከአምስት ዓመት በፊት የዓለም ነዳጅ ዋጋ በበርሜል 100 ዶላር ነበር፤ ያኔ አንድ ሊትር ቤንዚን በ17 ብር ከ88 ሣንቲም ይሸጥ ነበር፡፡ እስካለፈው ወር ድረስ የዓለም ገበያ ዋጋ ከ30 እስከ 35 ዶላር ሆኖም፣ በአገር ውስጥ ቤንዚን በሊትር 17 ብር 43 ሣንቲም ሲሸጥ ቆይቷል፡፡
ዋጋው ባሽቆለቆለበት ወቅት መንግስት ቢያንስ የነዳጅ ዋጋን በሊትር እስከ 9 ብር ማውረድ እንደነበረበት ያስረዱ ዓለም አቀፍ ተቋማት መንግስት በእነዚህ ጊዜያት ከነዳጅ ሽያጭ ከፍተኛ ትርፍ እንደሰበሰበ አጋልጠዋል፡፡ በዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ መውረድ መጠን ከታየ፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ በሊትር በ5 እና በ6 ብር መሸጥ እንደነበረበት የሚያብራሩ አካላት እንደገና የታሪፍ ጭማሪ ከማድረግ ይልቅ “ትክክለኛ የነዳጅ ቅናሽ ማድረግ አለያም ለታክሲዎች ብቻ የልዩ ቅናሽ የነዳጅ ኩፖን ማዘጋጀት መሰል አማራጮች መታየት አለባቸው” የሚል ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡