EU Africa leaders

  • የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኙ ስደተኞችን ወደ መጡበት መመለስ እጅግ አደገኛ ለሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚዳርጋቸው ሲሆን ኢትዮዽያን ጨምሮ አንዳንድ የአፍሪቃ መሪዎች ግን ስምምነቱን በደስታ ተቀብለውታል።
  • ከሀገራቱ ጋር በተናጠል ስምምነት ይደረጋል።

 

ከስልሳ በላይ የአፍሪካ እና አውሮፓ ህብረት መሪዎች በማልታ ተሰብስበው የአፍሪካዊያን ስደተኞች ሰብዓዊ ቀውስን መፍታት ስለሚቻልበት ሁኔታ ለሁለት ቀናት መክረው ሀሞስ ዕለት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ አውሮፓ ህብረትም ለአፍሪካ ሀገራት አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የተስማማ ሲሆን ጥገኝነት የማያገኙ ስደተኞችን ወደ መጡበት የመመለስና መልሶ የማቋቋም ጉዳይም መጨረሻ በፀደቀው መርሃ ግብር ውስጥ ከአምስቱ የስምምነቱ ዓላማዎች አንዱ ሆኖ ፀድቋል፡፡ እጅጉን አወዛጋቢ የሆነው ይህ ጉዳይ አፍሪካዊያን ስደተኞቻቸውን ተቀብለው እንደገና ማቋቋም እንዲችሉ የሚያግዝ ዝርዝር አፈፃፀምም ወጥቶለታል፡፡

(ቻላቸው ታደሰ በድምፅ የተሰናዳ ዝርዝር አለው አድምጡት)

አውሮፓ ህብረት የመደበው የአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዩሮ አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ ለስልጠና፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ንግዶችን ለመደገፍ እንዲሁም የምግብ እጥረት፣ ፍልሰትን፣ አክራሪነትንና ግጭትን ለመከላከል የሚውል እንደሆነ ተነግሯል፡፡ አዲሱ የገንዘብ ድጋፍ አውሮፓ ህብረት ላለፉት ሶስት ዓመታት ኤርትራንና ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሃያ ስምንት የአፍሪካ ሀገሮች በየዓመቱ ሲሰጥ ከቆየው ሃያ ቢሊዮን ዩሮ የልማት ዕርዳታ ተጨማሪ መሆኑ ነው፡፡

Migrants arrival
ሆኖም አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች አውሮፓ ህብረት ባቀረበው ሃሳብ ሲበሳጩ ሌሎች ግን ደስተኞቸ መሆናቸውን የዋዜማ ምንጮች ይገልፃሉ፡፡ የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል አውሮፓ ህብረት ለሶሪያዊያን ጥገኝነት ፈቅዶ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ስደተኞች አፍሪካዊያን እንዳልሆኑ እየታወቀ ጥገኝነት ያላገኙ ይመለሱ ማለት ግልፅ አድልዎ ነው በማለት ሃሳቡን መኮነናቸው ተዘግቧል፡፡ በእርግጥም አምስቱ ከፍተኛ ስደተኛ አመንጭ ሀገሮች ሶሪያ፣ አፍጋኒስታን፣ ኢራቅና ፓኪስታን እና የምዕራብ ባልካን ሀገሮች መሆናቸውን መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡
ለማልታው ስብሰባ መነሻ የሆነው ባለፈው ሚያዚያ በሜዲትራኒያን ባህር የሰጠሙት ስምንት መቶ አፍሪካዊያን ስደተኞች ቢሆኑም የአውሮፓዊያን የአሁኑ ትኩረት ግን በስደተኞች መጥለቅለቃቸው የፈጠረባቸው ውስጣዊና አህጉራዊ ቀውስ እንደሆነ በግልፅ ታይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አውሮፓ ህብረት አብዛኛዎቹን አፍሪካዊያን ስደተኞች እንደ ስራ ፈላጊ የማየት አዝማሚያ አዳብሯል፡፡

ምዕራብ አፍሪካ ሀገሮችን የወከሉት የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት እንዲያውም የአፍሪካዊያንን ሀብት በተጭበረበረ መንገድ ይዘርፋሉ ያሏቸውን ዓለም ኣቀፍ ድንበር ተሸጋሪ ኮርፖሬሽኖች ለችግሩ ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

ጥገኝነት ያላገኙ ስደተኞችን ወደ አፍሪካ መመለስ የሚባለውን ሃሳብ ግን በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች እንደተቃወሙት ዓለም ዓቀፍ በመገናኛ ብዙሃን ዘገቡ ሲሆን አንዳንድ ታዛቢዎችም ስብሰባውን ህገወጥ ስደተኞች የሚባሉትን አባል ሀገራት መልሰው እንዲልኩ አረንጓዴ ምልክት ለመስጠት የተቀነባበረ ሴራ አድርገው አይተውታል፡፡
አሁን የቀረው ዋናው ጥያቄ ከዚህ በኋላ ምን ይከሰታል? የሚለው ነው፡፡ ጉዳዩን የሚከታተሉ ተንታኞች እንደሚሉት ከዚህ በኋላ አውሮፓዊያን ሀገሮች ከአፍሪካዊያን መንግስታት ጋር ሚስጢራዊ ሁለትዮሽ ስምምነቶችን በማድረግ ለመንግስታቱ የገንዘብ ድጋፍ እየሰጡ ህገወጥ የሚሏቸውን ስደተኞች ሊመልሱ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም በሂደቱ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊጋለጡ ይችላሉ የሚል ስጋት ሰፍኗል፡፡ እዚህ ላይ ያለው ተቃርኖ ግን አፍሪካዊያን መንግስታት ለአነስተኛው የአውሮፓዊያን ገንዘብ ድጋፍ ብለው ከውጭ የሚገባው ሪሚታንስ መጠን እንዲቀንስባቸው በር መከፈታቸው ነው፡፡

ገንዘቡ እንደ ስደተኞች ብዛት ለየሀገሮቹ የሚከፋፈል በመሆኑ በስደተኞች ቁጥር ከፍተኛውን ደረጃ የያዘችው ኤርትራ ከገንዘብ ድጋፉ የአንበሳውን ድርሻ እንደምትወስድ ይጠበቃል፡፡ በእርግጥም ዜናው በገንዘብ እጥረት ለተቸገረው የኤርትራ መንግስት መልካም ዜና ነው፡፡ ከጥር እስከ መስከረም ባሉት ስምንት ወራት ብቻ ሰላሳ ስድስት ሺህ አራት መቶ በላይ ኤርትራዊያን ስደተኞች በተለያዩ አውሮፓ ሀገራት ጥገኝነት መጠየቃቸውን ከአውሮፓ ህብረት የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ሆኖም ኤርትራ በጨቋኝ አገዛዝ ስር በመሆኗ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ስምምነቱን ክፉኛ ተችተውታል፡፡ የኤርትራ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም በስብሰባው ላይ የገንዘብ ድጋፉ ለኤርትራ እንዳይሰጥ ተማፅነው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም ኤርትራ ከተጠቃሚነቱ እንድትገለል ግፊት ማድረጉ ይሰማል፤ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያምም በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ወደ ፈረንሳይ ያቀኑ ሲሆን የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንትም በኤርትራ ላይ የከረረ አቋም መያዛቸውን ታዛቢዎች ይገልፃሉ፡፡

Migrants Death
ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንደ ግብፅ፣ ሱዳን እና ኤርትራ ላሉ ጨቋኝ መንግስታት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የበለጠ እንዲረጋጉ ስለሚያስችላቸው ወደፊት በርካታ ዜጎች ለስደት እንዲዳረጉ መንገድ ይከፍታል በማለት ይከራከራሉ፡፡ ብዙ አፍሪካዊያን መንግስታትም በገንዘብ ድጋፉ በድንበሮቻቸው ላይ ቁጥጥራቸውን ለማጥበቅና ወደ አውሮፓ የሚደረገውን ስደት ለመቀነስ ይጠቀሙበታል ብሎ መጠበቅ ያስቸግራል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ባለፈው መስከረም የህብረቱ መሪዎች በግሪክ እና ጣሊያን የተጠለሉ አንድ መቶ ስልሳ ሺህ ስደተኞችን በኮታ ድልድል ለመቀበል ቢወስኑም እስካሁን ድረስ ጥገኝነት ያገኙት ግን አንድ መቶ አርባ ሰባት ስደተኞች ብቻ መሆናቸው ቀውሱን የከፋ አድርጎታል፡፡ የህብረቱ አባል ሀገራትም መዋጮ ለማዋጣት ያላቸው ፍላጎት እምብዛም እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በበቅርቡ አውሮፓ ህብረት ካወጣቸው ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ እኤአ እስከ 2017 ድረስ ለአፍሪካዊያን ተማሪዎችና የትምህርት ባለሙያዎች የሚሰጠውን ነፃ ትምህርት ዕድል በእጥፍ እንዲጨምር ማድረግ ነው፡፡ እቅዱ ተማሪዎቹ ሰልጥነው ወደሃገራቸው ሲመለሱ በህገወጥ ስደተኝነት አውሮፓ ውስጥ ያሉ ዘመዷቻቸውን ይዘው እንዲመለሱ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ምንም እንኳ ውጤታማነቱ አጠራጣሪ ቢሆንም፡፡