ዋዜማ ራዲዮ- የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግዳጅ ለአንበሳ አውቶብስ ከሸጣቸው 550 አውቶቡሶች ዉስጥ ግማሽ የሚኾኑት ከጥቅም ዉጭ ኾነው እየተጣሉ ነው፡፡ አንዳንዶቹም “ታርደው” የተወሰነ እቃቸው በሥራ ላይ ላሉ ቀሪ አውቶቡሶች መለዋወጫ እንዲውል እየተደረገ ነው፡፡
ከ20 ዓመታት በላይ በድርጅቱ ዉስጥ በሾፌርነት እንዳገለገሉ የተናገሩ አንጋፋ ሾፌር ለዋዜማ እንደተናገሩት ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ የሚገጣጥማቸው እነዚህ ከባድ አውቶብሶች ለ20 ዓመታት ያለምንም የጎላ ችግር አገልግሎት ይሰጣሉ ተብለው እንደተገዙ ይናገራሉ፡፡ ኾኖም ስድስት ወራት እንኳ አገልግሎት ሳይሰጡ ሞተራቸው እንዲወርድ የተደረጉ እንዳሉ እንደሚያውቁ ይናገራሉ፡፡
ባለፈው ዓመት መጨረሻ ብቻ 143 አውቶብሶች ከጥቅም ዉጭ ኾነው ቆመዋል፡፡ አንዳንዶቹ በመለዋወጫ እጦት ነው የቆሙት ቢባልም ይህ እውነት እንዳልሆነ እኚሁ ሾፌር ይከራከራሉ፡፡ በርካታ ጊዜያት መለዋወጫ ነው እየተባለ ሪፖርት ይደረጋል፡፡ ብዙ ሚሊዮን ብር እየወጣ መለዋወጫ ከቻይናም ከቢሾፍቱም ተገዝቶ ያውቃል፡፡ የመለዋወጫ ጨረታ የማይወጣበት ወር አላስታውስም፤ ነገር ግን አውቶቡሶቹ ከእድሳት በኋላ ለጥቂት ወራት ብቻ አገልግሎት ሰጥተው በድጋሚ ይበላሻሉ፡፡ አንድ አውቶብስ ከተገዛበት ዋጋ በላይ ለመለዋወጫ እንደሚወጣለት ሁላችንም የድርጅቱ ሠራተኞች እናውቃለን ብለዋል፡፡ “በአገር ሀብት ለምን ይቀለዳል ብለን በድርጅቱ ለረዥም ዘመን ያገለገልን ሠራተኞች ተፈራርመን የቅሬታ ደብዳቤ ብናስገባም ምላሽ አላገኘንም” ይላሉ እኚህ ሾፌር ከፍ ባለ ሐዘኔታ፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት ከመከላከያ ኢንጂነሪንግ 550 አውቶቡሶች በግዳጅ ግዢ ሲፈፀም መስተዳደሩ 900 ሚሊዮን ብር ወጪ እንዲያደርግ ተገዶ ነበር፡፡ ከ550ዎቹ የመከላከያ አውቶቡሶች ዉስጥ 100 የሚኾኑት ተጣጣፊ (አርቲኪዩሌትድ ባስ) እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
እነዚህ ባለ ሁለት ተሳቢ አውቶብሶች በዚህ ከተማ መንገድ ለመንዳት አስቸጋሪ እንደሆኑ የተነገረ ሲሆን ሻተራቸው ወዲያዉኑ ስለሚተረተር፣ ወለላቸውም በቀላሉ ስለሚቀዳደድ ከ6 ወር በላይ አገልግሎት አይሰጡም፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳደር የትራንስፖርት ችግርን በአጭር ጊዜ ለመቅረፍ ይረዳሉ ያላቸውን አውቶብሶች በ900 ሚሊየን ብር ወጪ ግዢ የፈጸመው ከአምስት ዓመት በፊት ነበር፡፡ በግዢው ሰነድ ላይ አውቶብሶቹ ከ15 እስከ 20 ዓመታት ምንም አይነት የጎላ ችግር ሳያጋጥማቸው በአስተማማኝነት አገልግሎት እንደሚሰጡ ሰፍሯል፡፡ ኾኖም ብዙዎቹ አሁን ላይ ከጥቅም ዉጭ ኾነው በአምቼ ጋራዥ ቆመዋል፡፡ አንዳንዶቹም አገልግሎት ለሚሰጡ ባሶች እቃቸውን “እየታረደ” እየተሰጠ ነው፡፡ ይህም ድርጅቱንም ለከፍተኛ ወጪ ዳርጎታል፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በቅርቡ የከተማ አውቶቡስ ሥራ አስኪያጅንና የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የግዥና ሽያጭ ኃላፊን ጠቅሶ በሰራው ዘገባ ተበላሽተው ከጥቅም ዉጭ የኾኑ አውቶብሶች ቁጥር 195 ብቻ እንደሆነ ጠቅሷል፡፡ የመከላከያ ኢንጂነሪንግ የግዥና ሽያጭ ኃላፊው ችግሩ ከአንበሳ አውቶቡስ ድርጅት አጠቃቀም የመነጨ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ የአንበሳ አውቶቡስ ሥራ አስኪያጅ አቶ አለምነው ጌትነት በበኩላቸው በኃላፊው ምላሽ የተበሳጩ ይመስላሉ፡፡ “ከአጠቃቀም አንጻር አገልግሎት ፈላጊው ብዙ ነው፤ ነገር ግን አውቶብሶቹ የጥራት ችግር እንዳለባቸው መካድ አይገባም፤ የጥራት ችግር ባይርባቸው ኖሮማ እንዴት ከ15 እስከ 20 ዓመት ሊያገለግሉ የተሠሩ አውቶቡሶች በአራት ዓመት ዉስጥ ይህን ያህል ይበላሻል?” ሲሉ በድፍረት ጠይቀዋል፡፡
ለዋዜማ አስተያየታቸውን የሰጡ አንጋፋ ሾፌር እንደሚናገሩት በሩብ አመት ብቻ 72 ሚሊዮን ብር ወጥቶ መለዋወጫ ግዢ እንደተፈጸመ እንደሚያውቁ ገልጠው ኾኖም በዚህ ሁኔታ ወደ ሥራ የተመለሱ አውቶብሶች ከ5 አይበልጡም ይላሉ፡፡ እነሱም ቢኾን በወራት ዉስጠ ተመልሰው እንደሚቆሙ ምንም ጥርጥር የለኝም ይላሉ፡፡ ” እንደኢህአዴግ መንግሥት ለአገር ሐብት ደንታ የሌለው አላየሁም” ሲሉም ቁጭት ያክሉበታል፡፡
ባለፉት ዓመታት በአንበሳ አውቶቡስ ሠራተኞች መካከል በተደረገ የመልካም አስተዳደር ጉባኤ ስለነዚህ አውቶቡሶች የጥራት መጓደል ከፍተኛ ትችት ከተራ ሠራተኞች ጭምር የቀረበ ሲኾን ኃላፊዎች በበኩላቸው ይሄ የምታነሱት ጉዳይ ከኛ አቅም በላይ ነው የሚል መልስ በደፈናው ሰጥተው አልፈዋል፡፡
እኔ እድሜ ዘመኔን ሙሉ የነደኋቸው የዳፍ አውቶብሶች የጎላ ችግር ሳይገጥማቸው ከ10 ዓመት በላይ አገልግለዋል፡፡ እንዴት ጥራቱ ያልተፈተሸ አውቶቡስ ሲገዛ መንግሥት ዝም ብሎ ያያል የሚሉት እኚህ ሾፌር በጓደኞቻቸው የሚነዱ አዳዲስ የተባሉ ቢሾፍቱዎች ብዙዎቹ የፍሬን ችግር ስላለባቸው ተደጋጋሚ በሰውና በንብረት ላይ አደጋ ማድረሳቸውን እንደሚያውቁ አስረድተዋል፡፡ ብዙ ሾፌር ቢሾፍቱ ሲሰጠው አልነዳም እንደሚልና የደመወዝ ቅጣት ስለሚጣልበት ብቻ ለመንዳት እንደሚገደድ እኚህ ሾፌር ያብራራሉ፡፡
በከተማዋ 1000 የሚጠጉ ቢጫ ታክሲዎች፣ አንድ መቶ አሊያንስ አውቶብሶች በቅርብ ወራት ዉስጥ ከቀረጥ ነጻ የገቡ ሲኾን በቀጣዮቹ አመታት አራት መቶ የአሊያንስ አውቶብሶች ወደ አገሪቱ ለማስገባት እየተሞከረ እንደሆነ በመገናኛ ብዙኃን ተነግሯል፡፡ ከዚህ ባሻገር ቁጥራቸው ከ10ሺ በላይ የሚኾኑ ሰማያዊ ሚኒባሶችን በማኅበራት በማደራጀት አዳዲስ አውቶቡሶችን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡና የሚኒባስ አገልግሎት በሂደት ሙሉ በሙሉ እንዲቀር ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል፡፡
አንበሳ አውቶቡስ ከ73 ዓመታት በፊት የንጉሣዊ ቤተሰብ ንብረት ኾኖ የተቋቋመ ሲኾን በወቅቱ በ5 የወታደር አውቶብሶች በአምስት መስመሮች ሥራ እንደጀመረ ይነገራል፡፡ ከተቋቋመ ከ10 ዓመት በኋላም ድርጅቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ በንጉሣዊ ቤተሰብ፣ በመንግሥትና በታዋቂ ነጋዴዎች ሽርክና ተፈጥሮ በአክሲዮን ባለቤትነት ጅማ ከተማን ጨምሮ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የአንበሳ አውቶቡስ በግዳጅ ከመከላከያ የተገዙ በጥራታቸው ደካማ የኾኑ 550 አውቶብሶችን ጨምሮ 880 የሚኾኑ አውቶብሶች አሉት፡፡ ድርጅቱ በወር አንድ ሚሊዮን ብር ድጎማ እየተደረገለት እስከዛሬም ወደ ትርፍ አልተሸጋገረም፡፡ በዓመት በትንሹ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራን ያስመዘግባል፡፡ ዋንኛው የኪሳራ ምንጭ ኾኖ የቆየውም የአውቶቡሶች ተደጋጋሚ ብልሽት እንደሆነ ይነገራል፡፡