ዋዜማ ራዲዮ- በየካ ክፍለ ከተማ ሚስስ ሳንፎርድ ትምህርት ቤት አካባቢ የሚገኙ ሁለት ሺሕ የሚጠጉ ቤቶች በቅርብ ወራት ዉስጥ የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡ ከነዚህ ዉስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ሰፋፊ የግለሰብ ይዞታዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የቀበሌ ቤቶች ናቸው፡፡ እንዲፈርሱ የዉሳኔ ሐሳብ የተሰጠባቸው የአቧሬ ሰፈሮች ሕገወጥ በመሆናቸው ሳይሆን ቦታው ለመልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች በእጅጉ በመፈለጉ ነው፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት ሰራተኞች ባሳለፍነው ሳምንት በጽሑፍ የተላለፈላቸው መመሪያ እንደሚያስረዳው አቧሬና አካባቢውን በአስቸኳይ ለማልማት አቅጣጫ በመያዙ በወረዳ 6 (በቀድሞ አጠራር ቀበሌ 09) ዙርያ የሚገኙ የግል ይዞታዎችና የቀበሌ ቤቶች ቁጥርና ስፋት በዝርዝር አጥንተው በአጭር ጊዜ ዉስጥ እንዲያቀርቡ በማዕከል ኃላፊዎች ታዘዋል፡፡
በአንጻሩ የቤቶቹን መፍረስ ዉሳኔ በጥርጣሬ የሚመለከቱ በክፍለከተማ በተለያየ ኃላፊነት ደረጃ እየሰሩ የሚገኙ የዋዜማ ምንጮች በቅርብ ወራት ዉስጥ ምንም አይነት የቤት ማፍረስ ሥራ እንደማይከናወን ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ ይህም የሚሆነው ቤቶችን ለልማት ሲባል የማፍረስ ተግባር ለተቃውሞ እንቅስቃሴ በር ሊከፍት ይችላል የሚል ስጋት በካቢኔው ዘንድ በመኖሩ ነው፡፡
አገሪቱ ወደለየለት ብጥብጥ እንድታመራ የሚሹ አክራሪ ኃይሎች በዋና ከተማዋ አመጽ ለመቀስቀስ አጀንዳ አጥተዋል፤ እኛ ቤቶችን ለልማት ስናፈርስ እነርሱ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚል ስጋት በከንቲባው ዋና የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ተወልደ ገብረጻዲቅ ሲንጸባረቅ በተደጋጋሚ ሰምቻለሁ ይላል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የይዞታ ጽሕፈት ቤት ዉስጥ በኦፊሰርነት የሚያገለግል ወጣት የድርጅት አባል፡፡
ቤት የማፍረስ ተግባር ዘንድሮ የማይታሰብ ነው የሚሉት ወገኖች እንደ ተጨማሪ ማስረጃ የሚያቀርቡት በ2008 መጨረሻ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቀርሳ፣ ኮንቶማና ማንጎ ሰፈሮች ዉስጥ ሕገወጥ ሰፋሪዎችን ለማንሳት በተደረገው ሙከራ የወረዳ አንድ ሥራ አስፈጻሚን ጨምሮ የነዋሪዎች ሕይወት መጥፋቱን ተከትሎ ዉጥረት መንገሱን በማስታወስ ነው፡፡ በወቅቱ በነዋሪውና በፀጥታ ኃይሎች መሐል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ ከንቲባው አቶ ድሪባ ኩማ ሕገወጦችን የማፍረስ ጉዳይ ለድርድር አይቀርብም የሚል መግለጫ ቢሰጡም በዚያው ሰሞን እንዲፈርሱ ቀነ ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበሩ ሰፈሮች ለጊዜው እንዲታለፉ ለክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ማደስ ኃላፊዎች የቃል ትዕዛዝ ተሰጥቶ ነበር፡፡
እንደ ምሳሌም የቀርሳና ኮንቱማ ሰፈሮችን የሚያዋስነውና በርካታ ሕገወጥ ሰፋሪዎች ይገኙበታል የሚባለውን የአቃቂ ቃሊቲ መንደር ለማፍረስ ግብረኃይል ተደራጅቶ፣ ቀን ተቆርጦ፣ ልዩ የፖሊስ ኃይል ተመድቦ፣ ዶዘሮች ወደ አካባቢው እንዲቀርቡ ከተደረገ በኋላ ባልታወቀ ምክንያት የማፍረስ ሂደቱ ድንገት እንዲታጠፍ ሆኗል ይላሉ የወረዳው ባልደረቦች፡፡
የዋዜማ ዘጋቢ ያናገራቸውና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ የአራዳ ክፍለ ከተማ ሰራተኛ ዉሳኔው የታጠፈው ዜጎችን በክረምት ማፈናቀል አግባብ እንዳልሆነ በካቢኔው አቅጣጫ በመያዙ ነው ሲሉ ሌሎች በመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት የሚሰሩ ኦፊሰሮች ደግሞ በተቃራኒው እንዲያውም ሕገወጥ ቤቶች እንዲፈርሱ የሚመረጠው በክረምት ወቅት ነው፡፡ ይህም በበጋ ቤቶችን ማፍረስ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ሊያርቃቸው ስለሚችል ነው ሲሉ ተጻራሪ ሐሳቦችን ያቀርባሉ፡፡
በኦሮሚያ መንግሥትን ለሰፊ ሕዝባዊ ተቃውሞ የዳረገው የተቀናጀ ማስተር ፕላን ለጊዜው እንዲታጠፈ ከተደረገ በኋላ አዲስ አበባ የተናጥል የከተማ መሪ ፕላን ለማዘጋጀት ተገዳለች፡፡ ኾኖም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ እስከዛሬም በይፋ አላጸደቀችውም፡፡ የሕዝብ ዉይይት ተደርጎ በአስቸኳይ ይፀድቃል የተባለው መሪ ፕላን ከዛሬ ነገ እየተባለ ለወራት ሲንከባለል ቆይቷል፡፡ ያም ኾኖም አስሩም ክፍለ ከተሞች በአሁኑ ሰዓት የመሬት ጉዳዮችን እየፈጸሙ ያሉት ያልጸደቀውን የከተማዋን መሪ ፕላን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ባይፀድቅም እየሰራንበት ነው፤ በሱ መስራት ከጀመርን ዓመት አልፎናል ይላል ለዋዜማ ሐሳቡን የገለጸ አንድ የአራዳ ክፍለ ከተማ የመሬት ባለሞያ፡፡
በአዲሱ መሪ ፕላን የከተማዋ 30 በመቶ ለአረንጓዴ ልማት የሚፈለግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለአረንጓዴ ቦታ የተከለሉ ሥፋራዎች ዉስጥ እየኖሩ ያሉ ዜጎች በሂደት እንዲነሱ እንደሚደረግ የከተማዋ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡ ኾኖም ቁጥራቸው በርካታ ከመሆኑ ጋር ምትክ ቦታ ለመስጠት አስተዳደሩ ፈተና እንደሚገጥመው ከወዲሁ ተሰግቷል፡፡
ባለፉት ዓመታት የከተማዋን አብዛኛዎቹን የቆረቆዙ መንደሮች በመልሶ ማልማት ለማልማት በተደረጉ እንቅስቃሴዎች በሰንጋ ተራና አካባቢው 14 ሄክታር መሬት ለፋይናንስ ተቋማትና ለ40/60 የቤት ልማት ፕሮጀክት የተላለፈ ሲሆን በልደታ ቤተክርስቲያን አካባቢ 16 ሄክታር መሬት ደግሞ ለ20/80 ቤቶች ልማት ማከናወኛ የተሰጠ ነው፡፡ በተለይ በልደታ ክፍለ ከተማ የልደታና አካባቢው መልሶ ማልማት ፕሮጀክት በመስተዳደሩም ሆነ በፌዴራል ደረጃ በስኬታማነቱ በተደጋጋሚ የሚወደስ ፕሮጀክት ነው፡፡ የግልና የመንግሥት ባንኮች ሕንጻዎችን፣ ፀሜክስ ኢንተርናሽናል እያስገነባው እንዳለው አይነት ባለ ኮከብ ሆቴል ፕሮጀክቶችን፣ ፍሊንስቶን ያስገነባውን ዘመናዊ የገበያ ማዕከል (ሞል) ተግባራዊ ማድረግ የተቻለው በዚህ እንደ ሞዴል በሚወሰድ የመልሶ ማልመት ሥራ እንደሆነ በኃላፊዎች በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡
ይህ የልደታ መልሶ ማልማት ፕሮጀክት የኮንዶሚንየም ነዋሪዎች ከመሀል ከተማ ርቀው እንዳይሰፍሩ፣ በመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች መሐል መራራቅ እንዳይኖር ያደረገ ልማት እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ አማካሪ አቶ አባይ ፀሐዬ በተደጋጋሚ ሲያሞካሹት ይሰማል፡፡ ኾኖም ተመሳሳይ የመልሶ ማልማት ስኬት ሊደገም አልቻለም፡፡ ብዙዎቹ በመልሶ ማልማት ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ዜጎች ከነባር ይዞታቸው ተፈናቅለው በከተማዋ ጫፍ በሚገኙና መሠረተ ልማት ባልዳሰሳቸው ሥፍራዎች እንዲሰፍሩ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በቅርቡ የመፍረስ አደጋ የተጋረጠበት አቧሬ ሰፈር ከአንድ ሺ ካሬም የሚልቁ ሰፋፊ ይዞታዎች የሚገኙበት ሲሆን የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ዋና መቀመጫም የሚገኘው በዚህ ወረዳ ነው፡፡ በመልሶ ማልማት ምክንያት የሚነሱ ዜጎች ይዞታቸው ምንም ያህል ሰፋፊ ቢሆን እንኳ በመኖርያ ቤት እስከተመዘገበ ድረስ በምትክነት የሚሰጣቸው የካሬ ስፋት ከ500 ሜትር ስኩዌር ካሬ በላይ እንዳይሆን መመሪያው ያዛል፡፡ ኾኖም ተነሺዎቹ ይዞታቸውን በግላቸው የማልማት ፍላጎት ካላቸውና የፋይናንስ አቅም በራሳቸው መፍጠር ከቻሉ መሪ ፕላኑ በሚያዘው መሠረት በአካባቢው ዘጠኝ ፎቅና ከዚያ በላይ የመገንባት መብት ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ ግን ለብዙ የከተማዋ ጎስቋላ ነዋሪዎች የሚታሰብ ጉዳይ አይሆንም፡፡
ባለፉት ጥቂት አመታት ዉስጥ በልማት ስም ከፈረሱ የአዲስ አበባ ከተሞች መሐል አሜሪካን ግቢ ተጠቃሽ ነው፡፡ በአካባቢው ለ30 አመታት ነዋሪ የነበሩ ዜጎች የይዞታ ባለቤትነትን ከማረጋገጥና ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ዉዝግብ ዛሬም ሙሉ በሙሉ ምላሽ አላገኘም፡፡ ኾኖም ከአካባቢው የተነሱ ሱቆች ራሳቸውን በቡድን እያደራጁ ቁራሽ መሬቶች እየተሰጣቸው ቆይቷል፡፡
ከነዚህ አካባቢዎች በተጨማሪ አዲስ ከተማ፣ ጎጃም በረንዳ፣ ቁጭራ ሰፈር፣ ጣሊያን ሰፈርና ገዳም ሰፈር በመልሶ ማልማት የሚፈርሱና እየፈረሱ ያሉ አካባቢዎች ናቸው፡፡
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዉስጥ የሚካተተው የመስቀል አደባባይ ኢሲኤ ጀርባ 4 ሄክታር መሬት፣ አራዳ ክፍለ ከተማ ዉስጥ የሚካተተው የ አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት አካባቢ 24 ሄክታር መሬት በመልሶ ማልማት ተነስቷል፡፡ የባሻ ወልዴ ችሎት አካባቢ በሊዝና በምሪት ለባለሀብቶችና ለድርጅቶች የተላለፈ ሲሆን ቦታ ከወሰዱ ድርጅቶች መሐል የብአዴን ጽሕፈት ቤት ግንባታ፣ ሁለት የግል ሆስፒታሎች ግንባታ፣ የዳሽን ባንክ ቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ፣ የሂልኮ ኮምፒውተር ኮሌጅ ግንባታ በአመዛኙ ተጠናቋል፡፡
የባሻ ወልዴ ችሎት አካባቢ እየተከናወኑ ካሉ ፕሮጀክቶች ትልቁ በአምባሳደር ልብስ ስፌት ባለቤት በአቶ ሰኢድ መሐመድ ብርሃን እየለማ ያለው ቦታ ሲሆን ከአርበኞች ግንብ ሕንጻ ጎን ከፓርላመው ባሻገር የሚገኝ 3ሺ ካሬ ቦታ ነው፡፡ አገልግሎቱም ባለ 4 ፎቅ ሰፊ የገበያ ማዕከል ግንባታ ነው፡፡ ይህ ግንባታ ረዥም ዓመታትን የወሰደ ቢሆንም እስካሁንም አልተገባደደም፡፡ የባሻ ወልዴ ችሎት መልሶ ማልማት ቦታዎች በተፈለገው ፍጥነት አለመሄዳቸው ብቻም ሳይሆን ብዙዎቹ ቦታዎች ከፈረሱ አመታት ቢያስቆጥሩም አሁንም አለመልማታቸው የነዋሪዎች መነጋገሪያ ሆነዋል፡፡ በመሪ ፕላኑ መሰረት አካባቢው ለቤተመንግሥትና ፓርላማ ቅርብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከ4 ፎቅ በላይ መገንባትን አይፈቅድም፡፡
ተመሳሳይ ሰፊ የመልሶ ማልማት ሥራ ካከናወኑ ክፍለ ከተሞች መሐል የቂርቂስ ክፍለ ከተማ ተጠቃሽ ሲሆን ለአፍሪካ ሕብረት አዲሱ ሕንጻ ግንባታና ለኢሲኤ (የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት የመጀመርያ መሰብሰቢያ አዳራሽ) ማስፋፊያና ፓርክ ሲባል ኢስጢፋኖስ ጀርባ የነበሩ በርካታ ነዋሪዎችን ከቀያቸው ለማፈናቀል ተገዷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ካዛንቺስና አካባቢዋ በርካታ ባለ ኮከብ ሆቴሎች ግንባታ መከናወን የቻለውም ቦታው ለመልሶ ማልማት በመዋሉ ነው፡፡
አሁን ተመሳሳይ ሰፋፊ የሆቴል ፕሮጀክቶች ይካሄዱበታል ተብሎ የሚገመተውና የካዛንቺስ 2 መልሶ ማልማት ዘመቻ በሚል የሚታወቀውን የልማት ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ራዲሰን ብሎ ማዶ፣ ኢንተርኮንቲነንሰታል ሆቴል ፊትለፊት፣ ኦራኤል ቤተክርስቲያን ተሻግሮ የሚገኙ ሰፈሮች ሙሉ በሙሉ እንዲነሱ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ቦታዎቹ ከጸዱ ዘለግ ያለ ጊዜ ቢያስቆጥሩም የፈረሱት ቦታዎች እስከአሁንም ለአልሚዎች አልተላለፉም፡፡
በከተማዋ ነዋሪዎች እንደ ተደጋጋሚ ቅሬታ የሚነሳውም ይኸው ጉዳይ ነው፡፡ ድሀን በልማት ስም አፈናቅሎ መተው፣ ወቅቱን ያገናዘበ ተገቢ ካሳን አለመስጠት፣ የማኅበራዊ ምስቅልቅል የሚፈጥሩ አሰፋፈሮችን መከተል የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ለረዥም አመታት ያማረረ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የፈረሱ ቦታዎች ለአመታት ያለምንም አገልግሎት ተጥረው እንዲቀመጡ መሆናቸው ግርትን የሚፈጥር ጉዳይ ነው፡፡ ይህም አንድም በመስተዳደሩ ድክመት ቦታዎቹን ለአልሚዎች በጊዜ ያለማስተላለፍ ችግር ጋር የሚያያዝ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አልሚዎች ቦታዎቹን አጥረው ይዞታቸውን ካስከበሩ በኋላ ለዓመታት ግንባታ ለማከናወን ሳይፈቅዱ መቆየታቸው ነው፡፡
ይዞታዎች ለአልሚዎች ሲተላለፉ የግንባታ መጀመርያ ጊዜና ማጠናቀቂያ ጊዜ በዉል ተለይተው፣ የሊዝ ዉል ፈርመው የሚገቡበት አሰራር ቢኖርም ይህ ሁኔታ ለሁሉም ዜጎች በእኩል የሚሰራ አልሆነም፡፡
በዚህ ረገድ በከተማዋ የአስተዳደር እርከን በሁሉም ደረጃ ከኤህአዴግ አባላት ሳይቀር ሰፊ ትችትና ትዝብትን የሚያስተናግዱት በሳኡዲያዊው ባለሀብት ሼክ መሀመድ አላሙዲ የተያዙ ሰፋፊ የከተማዋ ይዞታዎች ናቸው፡፡ በተለይም ከካዛንቺስ ኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ጎን ተቆፍሮ የሚገኘው ቦታ መለስተኛ ኩሬ ፈጥሮ ለአካባቢው የጤና ጠንቅ እስከመሆን የደረሰ ሲሆን በኢንተርኮንቴኔንታል ሆቴል የሚያርፉ እንግዶች መስኮቶቻቸውን ለመክፈት እስከመቸገር መድረሳቸው ይነገራል፡፡ የሸራተን ማስፋፊያ በሚል ለጎልፍ ክለብና ልዩ ልዩ መዝናኛዎች የታጠረውና በተለምዶ ፖሊስ ጋራዥ የሚባለው ሰፊ ቦታ ማጅራት መቺዎችና ኪስ አውላቂቆች መሸሸጊያ እየሆነ እንደመጣ ነዋሪዎች ብቻም ሳይሆን የከተማዋ ፖሊስ ጽሕፈት ቤትም የሚያነሳው ጉዳይ ሆኗል፡፡ የፒያሳው ግዙፍ የመንታ ሕንጻዎች ፕሮጀክት በዲዛይን ለውጥና በሌሎች ጥቃቅን ሰበቦች የተነሳ ይህ ነው የሚባል ግንባታ ሳይካሄድበት ለ18 ዓመታት ታጥሮ መቀመጡም የከተማዋ ነዋሪ በአስተዳደሩ ላይ እምነት እንዲያጣ ካደረጉት አበይት ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡