- ኮንስትራክሽን ቢሮ ለጊዜው የሁሉንም ፈቃድ ሰርዟል
ዋዜማ ራዲዮ- የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በፌዴራል ደረጃ ሲሰጥ የቆየውን የባለሞያዎችን፣ የሥራ ተቋራጭ ኩባንያዎችን የመሳሪያና የሞያ ምዝገባና ፍቃድ ሙሉ በሙሉ መሰረዙን አስታወቀ፡፡ እስከ መስከረም 30 ድረስም ለሥራ ተቋራጮችና ለአማካሪ መሐንዲሶች ማንኛውንም የሥራ ፈቃድ፣ እድሳትና የምዝገባ አገልግሎት እንደማይሰጥ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በማስታወቂያ ሰሌዳው በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡
ይህ የሆነው በሐሰተኛ ተቋራጮች የሚገነቡት ብዙዎቹ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጉልህ ግድፈቶች እየታዩ በመምጣታቸውና ሕጋዊ የሆኑ ተቋራጮች ቅሬታ እያቀረቡ መሆኑን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የ40/60 እና የ20/80 ጋራ መኖርያ ቤቶች ግንባታ እያካሄዱ ያሉ የሥራ ተቋራጮችና አማካራ መሐንዲሶች የሚፈለገውን ደረጃ የማያሟሉ፣ በቂ የሰው ኃይልና የማሺነሪ አቅርቦት የሌላቸው፣ አንዳንዶቹም ሐሰተኛ ማስረጃ በማቅረብ የግንባታ ዉል የፈጸሙ እንደሆኑ ተደርሶበታል፡፡
መስሪያ ቤቱ የትኞቹ በዚህ ተግባር ላይ እንደተሰማሩ በስም ባይዘረዝርም ጉዳዩን ለሕግ ለማቅረብ ከሚመለከታቸው የፍትህ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡
በ40/60 የቤት ፕሮጀክት ብቻ በአሁኑ ሰዓት የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ከባለ 8 እስከ 18 ወለል የሚደርሱ 371 ሕንጻዎችን በ13 የተለያዩ አካባቢዎች በማስገንባት ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህን ግንባታዎች ከሚያካሄዱት ተቋራጮች ዉስጥ ምን ያህሉ በሐሰተኛ ፍቃድ እየሰሩ እንደሆነ መሥሪያ ቤቱ ከመዘርዘር ቢቆጠብም የዋዜማ ዘጋቢ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ሰራተኞች ባገኘው መረጃ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ምንም አይነት የገንቢነት ፍቃድ የሌላቸው ወይም የሚፈለገውን አነስተኛ ደረጃ እንኳ የማያሟሉ እንደሆኑ ተረድቷል፡፡
ከዚህ ባሻገር መንግሥት የሥራ እድል ለመፍጠር በሚል ከደረጃ በታች የሆኑ ተቋራጮችና ዕቃ አቅራቢዎችን በቤቶች ግንባታ ፕሮጅክቶች ልቅ በሆነ መልኩ ያሳትፋል፡፡ ለ40፣60 ፕሮግራም በብሎኬት፣ በፕሪካስት ምርት፣ በሳኒተሪና በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ብቻ ለ25 ሺህ ዜጎች ሥራ መፍጠሩን ይናገራል፡፡ ኾኖም የሚቀርቡት እቃዎች ጥራት አሳሳቢ ሆኗል፡፡ የግንባታና ቁጥጥር ሥራው ፍጹም በማይመጥኑ ተቋራጮችና ባለሞያ ባልሆኑ ግለሰቦች መሠራቱ ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል ከፍተኛ የአገር ሀብት ብክነትን እያስከተለ ይገኛል ይላሉ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች፡፡ በደረጃ አንድ ገንቢነት በ40/60 ፕሮጀክት የ18 ፎቅ ግንባታ ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ ስማቸውን መግለጽ የማይሹ አንድ አማካሪ መሐንዲስ ችግሩ እንዲሁ በቀላሉ የሚነገር አይደለም ይላሉ፡፡ ወደፊት ነዋሪው ላይ ሊፈርሱ የሚችሉ ቤቶች ቢያጋጥሙ አይገርመኝም ሲሉ የግንባታ ጥራቱን ደረጃ መውረድ ተችተዋል፡፡
ከአመት በፊት በተጠናቀቀው የአራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት አካባቢ ኮንዶሚንየም ከፍተኛ የጥራት መጓደል በመስተዋሉ አጣሪ ቡድን ተቋቁሞ በሕንጻዎቹ ላይ ጥናት እያደረገ እንደሚገኝ ሸገር ሬዲዮ በቅርቡ ዘግቧል፡፡
ኮንስትራክሽን ቢሮ ለጊዜው አዲስ ፍቃድም ሆነ እድሳት እንደማይቀበል በማስታወቂያ ሰሌዳው ቢገልጽም ከመጪው ጥቅምት 1፣ 2009 ጀምሮ አዲስ አሰራር በመዘርጋት በአዲስ መልክ ተቋራጮችን መመዝገብ የሚጀምር መሆኑንም አገልግሎቱን ለሚፈልጉ ደንበኞቹ ባስተላለፈው መልእክት አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት በአገሪቱ በፌዴራል ደረጃ ለተቋራጮችና አማካሪ መሐንዲሶች የተሰጡ የብቃት ማረጋገጫዎች ለጊዜው ሙሉ በሙሉ ዉድቅ በመሆናቸው ሁሉም በዘርፉ የተሰማራ ነባር ተቋራጭም ሆነ አማካሪ መሐንዲሶች ለአዲስ ምዝገባ እንዲሰናዱ መመሪያ ተላልፏል፡፡
ኮንስትራክሽን ቢሮ የሥራ ተቋራጭነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት፣ ለማደስ ወይም ለማሻሻል ለሚኒስቴሩ የሚቀርቡ ማመልከቻዎችን ተቀብሎ የቀረቡ ማመልከቻዎች አዋጁ፣ ደንቡና መመሪያው በሚያዘው መሠረት በመረጃ ተሟልተው መቅረባቸውንና ትክክለኛ መሆናቸውን በማረጋገጥ እንዲመዘገብ፣ የሞያ ፈቃዱ ወይም የምዝገባ የምስክር ወረቀቱ እንዲታደስ፣ እንዲሻሻል ወይም ማመልከቻው ውድቅ እንዲሆን የመወሰን ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ማመልከቻዎች ውድቅ እንዲሆን ከወሰነ ደግሞ የወሰነበትን ምክንያት ለአመልካቹ በጽሑፍ ያሳውቃል። የሞያ ፈቃድ ወይም የምሥክር ወረቀት እንዲሰረዝ ወይም እንደገና እንዲተካ የቀረበ ማመልከቻን በመመርመር እንዲሰረዝ ወይም እንዲተካ የመወሰን ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ያም ኾኖ በቢሮው ሰፊ የአሰራር ክፍተት ሊፈጠር የቻለው አመልካቾች የሌሏቸውን ግዙፍ የግንባታ ማሽነሪዎች አሉን በማለት ሐሰተኛ ማስረጃ ሲያቀርቡ ያንን በአካል ሄዶ የማጣራት አቅሙ ዉስን በመሆኑ ጭምር ነው፡፡
የታረደ መኪና ሊብሬ በማሳየት ብቻ ፍቃድ ይሰጡሀል፣ በአንድ ገልባጭ መኪና 20 ተቋራጮች ፍቃድ ሲያወጡበት ታያለህ፣ ሁሉም ነገር ተጨመላልቆ ነው ያለው ይላል ዘጋቢያችን ያነናገረው ወጣት ተቆጣጣሪ መሐንዲስ፡፡
ኮንስትራክሽን ቢሮ የሞያ ፈቃድ ወይም የምዝገባ የምሥክር ወረቀት የተሰጠው ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ወይም ተቋራጭ በሥራ አፈጻጸሙ ሞያው የሚጠይቀው ብቃት የሌለው ስለመሆኑ በማስረጃ ሲያረጋግጥ የሞያ ፈቃዱን የማገድና የመሰረዝ ስልጣን ቢኖረውም እስከዛሬ ይህን ለማከናወን ተስኖት ቆይቷል።
በመሆኑም ሥራ ተቋራጮች የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሳያገኙ በኮንስትራክሽን ሥራዎች ላይ መሰማራት ባይችሉም በቀላል እጅ መንሻ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ለደረጃቸው የሚያስፈልጓቸውን የሰውና የማሽነሪ ብዛት ሳያሟሉ በሐሰተኛ መረጃ ብቻ የሚሹትን ፍቃድ በቀላሉ በመያዝ ግንባታ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በአሰራር ክፍተት የተነሳ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በቀላሉ ስለሚያገኙም የንግድ ፍቃድ ለመውሰድ እምብዛምም አይቸገሩም፡፡ ይህም ከአስገንቢዎች ጋር በቀላሉ የሥራ ዉል ለመፈጸም ያስችላቸዋል፡፡ የኮንስትራክሽን ቢሮ ደንብ እንደሚያስረዳው አስገንቢዎች የጸና የብቃት የምስክር ወረቀትና የንግድ ፍቃድ የሌላቸው ተቋራጮችን ማሰራት በሕግ ያስጠይቃቸዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ቢሮ ከዚህ ቀደም በየካቲት ወር 2008 ዓ. ም አምስት መቶ የሚሆኑ የሥራ ተቋራጮች ፈቃድ ሰርዞ የእግድ ዉሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሌላቸውን የኮንስትራክሽን መሳሪያ እንዳላቸው አድርጎ በማቅረብና ለደረጃ መሟያ ሐሰተኛ ሰነዶችን እንደ አስረጅ አቅርበው በዘርፉ በመሰማራታቸው ነው፡፡ በፌዴራል ደረጃ የተሰማሩ ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አራት ብቻ አንድ ሺ ሰባት መቶ የሚጠጉ የሥራ ተቋራጮች በአገሪቱ ፍቃድ ወስደው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ኾኖም ከነዚህ ዉስጥ የሚበዙቱ መመሪያው የሚጠይቀውን ዝቅተኛ የባለሞያና የማሽነሪ ግብአት የሚያሟሉ አይደሉም፡፡ ባለፈው ዓመት አጋማሽ በተደረገ አሰሳ 52 የሚሆኑት ተቋራጮች ፈጽሞ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የማያውቃቸው፣ ምዝገባም አካሄደው የማያውቁ ሆኖም ራሳቸው ባዘጋጁት ሐሰተኛ ሰነድ ኮንዶሚንየሞችንና ሌሎች ግንባታዎችን ሲያካሄዱ የቆዩ መሆናቸው ተደርሶበታል፡፡ የ40/60 ፕሮጀክቶችን ከሚገነቡ 103 ተቋራጮች 52 የሚሆኑት ለዚህ ፕሮጀክት የሚመጥን የሥራ ደረጃና ፍቃድ ሳይኖራቸው የተሰማሩ ናቸው፡፡
ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ገንቢዎች በፕሮጀክቶቹ የሚታዩ ችግሮች ዘርፈ ብዙ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ብሎኬቶቹ ገና ስትነካቸው ፍርክስክስ የሚሉ ናቸው፡፡ የሁሉም ግንባታ ጥሬ እቃ አቅራቢ መንግሥት ነው፡፡ የመጨረሻው ዝቅተኛ የጥራት ደረጃን እንኳን የማያሟሉ እቃዎች ነው የሚቀርቡት፣ ክፍያ ይጓተታል፣ ለሰራተኛ ደመወዝ መክፈል የማይችል ተቋራጭ ብዙ ነው፡፡ ይህም የሚሆው በዋናነት ክፍያ ቶሎ ስለማይለቀቅልን ነው ይላል በሲኤምሲ ሳይት ሁለት ብሎኮችን በመገንባት ላይ ያለ አማካሪ መሐንዲስ፡፡ ለግንባታ የሚዉለው አሸዋ፣ ሲሚንቶና ጠጠር ዉህደት መጠንና ጥራት በዘፈቀደ የሚካሄድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሮች ይነሳሉ፡፡ እኛ ጋ ደህና ነው፡፡ ዉሀ እንደልብ ማግኘት ይቻላል፡፡ የዉሀ አቅርቦት ዉስን በሆነባቸው ሳይቶች የተለሰነ ግድግዳ በጆክ ነው ዉሀ የሚጠጣው፡፡ ሲል የጥራቱን አሳሳቢነት ይገለጻል፡፡
የአንድ ኮንዶሚንየም ሕንጻ የግንባታ ሂደት ዉስጥ 40 ከመቶ ሥራው የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ድርሻ ሲሆን በርና መስኮትን ጨምሮ የጣሪያ ሥራ፣ የብሎኬት ምርቶች በነዚህ ማኅበራት እንዲቀርቡ መንግሥት ያስገድዳል፡፡
ተቋራጮች በጥቅሉ በአራት የሚከፈሉ ሲሆን ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ (GC)፣ የሕንጻ ሥራ ተቋራጭ (BC)፣ የመንገድ ሥራ ተቋራጭ (RC)እና ልዩ ሥራ ተቋራጭ (SC) በሚል ይከፈላሉ፡፡ አንድ በደረጃ 1 ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ በትንሹ አራት ዶዘሮች፣ 30 ሜትር እስከ አንድ ቶን ማንሳት የሚችል አንድ ክሬን ፣ 2 ሎደሮች፣ 2 ክረሸሮች፣ 2 ግሬደሮች፣ 2 ኤስካቬተሮች፣ 3 ሮለር ሚክሰሮች፣ 2 ፎርዊል ድራይቨ እና አምስት ኩንታል በላይ መጫን የሚችሉ አራት ፒክአፖች ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት 130 የሚሆኑ ደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጮች ይገኛሉ፡፡