ዋዜማ ራዲዮ- ከቀኑ 9ሰዓትከ30 የደረሰን
ዓለም ገና አመጽ ቀስ በቀስ እየበረደ ነው፡፡ በሳሙና ፋብሪካ ተነስቶ የነበረው እሳትም ጠፍቷል፡፡ ከፖሊስ ኃይል ዉጭ በአካባቢው የሚዘዋወር ሰው እምብዛምም ነው፡፡ የማማ ወተት፣ የስ ዉሃ፣ እና ሌሎች ፋብሪካዎች አካባቢ ተጨማሪ ኃይል ተልኮ ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው፡፡ ፖሊሶች መንገድ የዘጉ ድንጋዮችን ከአስፋልት እያነሱ ነው፡፡
ነዋሪዎች ወጥቶ አስቤዛ ለመግዛት እንኳ የሚችሉበትነ እድል አላገኙም፡፡
08 ቀበሌ በእሳት ከመጋየት ቢተርፍም በዉስጡ ይገኙ የነበሩ ፋይሎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡
ሳይንገን ዲማ የኢንደስትሪ መንደር በርካታ የኬብልና የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የሚገኙበት ሲሆን መንግሥት ጥበቃ እንዲያደርግላቸው በወተወቱት መሠረት በርካታ ፌዴራል ፖሊሶች በክፍት መኪና ተጭነው ወደዚያ ሲጓጓዙ ነበር፡፡
ወለቴ ትናንት ምሽት መጠነሻ ረብሻ ተነስቶ ነበር፡፡ በርከት ያሉ መኖርያ ቤቶች መስታወቶቻቸው ተሰባብሮ ነበር፡፡ ከመሐል ከተማ የመጡ ነዋሪዎችን ይህ የኛ መሬት ነው ልቀቁ የሚል መልዕክት በሚያስተላልፉ የአካባቢው ወጣቶች ታውከው እንደነበር ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ ከማለዳ ጀምሮ ግን አካባቢው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሷል፡፡
ትናንት ማምሻውን ከ18 ልኳንዳ አሸዋ ሜዳ ሳይደረስ ፊሊዶሮ በሚባለው አካባቢ በመሬት ይገባኛል ጥያቄ በኦሮሞና በወላይታ ተወላጆች በተነሳ ጸብ የ2 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተነግሯል፡፡ የጸቡ መነሻ የግለሰቦች ይሁን እንጂ ሁኔታው ወደ መለስተኛ አመጽ አድጎ አካባቢው በጸጥታ ኃይሎች በአይነ ቁራኛ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡ ዛሬ ምንም አይነት አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ወደ ሥራ አልተመለሰም፡፡
ወደ ለቡ የሚወስዱ መንገዶች ዛሬ ከረፋዱ ጀምሮ ከፍተኛ የፌዴራል ፖሊስ ፈሶባቸው ነበር፡፡ ዋንኛው ምክንያት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ 70 ቢሊዮን በር በላይ የፈጀውን የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ጣቢያን ለመመረቅ በዚያ ያልፉ ስለነበር ነው፡፡
ዋዜማ ራዲዮ- ከቀኑ 6 ሰዓትከ15 የደረሰን
- በአለምገና ቀበሌ 08 ተቃጥሏል የተባለው ሐሰት እንደሆነና የተቃጠለው ጊቢው ዉስጥ ቆሞ የነበረ መኪና እንደሆነ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
- አለምገና ኬንቴሪ አካባቢ ወደ ዉስጥ ገባ ብሎ የሚገኝ ሳሙና ፋብሪካም ተቃጥሏል፡፡
- በአሁኑ ሰዓት አካባቢው በድንጋይ በመዘጋቱ መተላለፍ አይቻልም
- የአምቡላንስ ድምጽ አልፎ አልፎ ይሰማል፡፡
- ምንም አይነት አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት የለም፡፡
ዋዜማ ራዲዮ- ከቀኑ 5 ሰዓት የደረሰን
- ዓለምገና በተለምዶ ዋጦ የሚባለው ሰፈር የሚገኘው ሀይፐር ግላስ ሮቶ ፋብሪካ እየነደደ ነው፡፡
- አዲስ አበባ በከፊል ስጋት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሳለች፡፡
- በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለመላክ አልፈቀዱም፡፡
- ተማሪዎች ትምህርት ቤት የደረሱት ከተለመደው ሰዓት አረፋፍደው ነው፡፡
- በሁሉም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በር ላይ በርከት ያለ የጸጥታ ኃይል ተመድቧል፡፡
- ብዙ ሺ ደንበኞች ተቀማጭ ገንዘባቸውን ከባንክ እያወጡ ነው፡፡
- በአራት ኪሎ፣ በፊት በር፣ በሸራተን ዙርያ፣ በዉጭ ጉዳይና ደኅንነት መሥሪያ ቤት ከፍተኛ የፀጥታ ኃይል ይታያል፡፡
- በስልክ የኢንተርኔት አገልግሎት ከሌሊት ጀምሮ በከፊል ተቋርጧል፡፡ የብሮድባንድ መስመርም ቢሆን በአብዛኛው ቀርፋፋ የሚባል ነው፡፡
- ከ30 ደቂቃ በፊት ጀምሮ በአለምገና ሮቶ ፋብሪካ በእሳት እየጋየ ነው፡፡
ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ ዘጋቢዎቻችን በተዘዋወሩባቸው የባንክ ቅርንጫፎች ደንበኞች ባልተለመደ ሁኔታ ገንዘብ ለማውጣት ተሰልፈው ዉለዋል፡፡
የፒያሳ ባንኮዲሮማ አካባቢ ቅርንጫፍ ባልደረባ ለዘጋቢያችን በስልክ እንደነገረው አራት ተኩል ላይ የለመድናትን ሻይ ለመጠጣት እንኳ ፋታ አላገኘንም ሲል ቅርንጫፉ በሰዎች መጨናነቁን ገልጾለታል፡፡ ተመሳሳይ የደንበኞች መጨናነቅ የሚከሰተው በገናና አዲስ አመት ዋዜማ ብቻ ነበር፡፡
ብዙዎቹ ነዋሪዎች ስለምን ተቀማጭ ገንዘብ እያወጡ እንደሆነ ባይናገሩም ምናልባት ቀጣይ ቀናት ከተማው ሰላም ሊርቃት ይችላል ከሚል ስጋት የመነጨ እንደሆነ ተገምቷል፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ የሚሄዱ በራሪ ዶልፊኖችና አባዱላዎች ተሳፋሪዎችን ለመጫን ፍቃደኛ ባለመሆናቸው በዋናው አውቶቡስ ተራ መጠነኛ የተሳፋሪ እንግልት ይታያል፡፡ ሰላማዊ ወደሆኑት እንደ ወሊሶ መስመሮች ፍቃደኛ በሆኑ ሚኒባሶች አገልግሎት እየሰጠን ነው፣ ባሉካዎች አንሄድም ካሉ ማስገደድ አንችልም ይላል በዋናው በአውቶቡስ ተራ የሚገኝ የስምሪት አስተናባሪ፡፡
ትናንት ከቀትር ሰዓት ጀምሮ የአመጽ እንቅስቃሴ ታይቶባቸው ከነበሩ ሰፈሮች መሐል ፉሪ አካባቢ ወጣቶች ምሽቱን እየታደኑ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ መንገዶች ክፍት የሆኑ ሲሆን ከቤት መኪናዎች ዉጭ ታክሲዎች በአካባቢው የትራንሰፖርት አገልግሎት ለመስጠት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡
ትናንት የአብዛኛው የከተማዋ ክፍል ማምሻውን በሚያስፈራ ጭርታ ተውጦ ነበር፡፡ ከሰዓት ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ የአዲስ አበባ በሮች ሁከት መቀስቀሱን መዘገብ መጀመራቸውን ተከትሎ በነዋሪው ዘንድ ከፍተኛ ፍርሃት ነግሶ ነበር፡፡ በተለይም በክፍለ ከተሞች አካባቢ የነበሩ ባለጉዳዮች ከሰዓት በኋላ አንዳንድ ሴት ሠራተኞች አገልግሎት ለመስጠት ባለመፍቀዳቸውና ከቢሮ በጊዜ ካልወጣን ብለው አለቆቻቸውን በመሞገታቸው ብዙዎቹ የመሬት አስተዳደር ቢሮዎች አገልግሎት መስጠት አቁመው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የተወሰኑ ሴት ሰራተኞች ከትምህርት ቤት ልጆቻችሁን ዉሰዱ የሚል የስልክ ጥሪ ሲደርሳቸው ድምጽ አውጥተው ማልቀስ መጀመራቸው በተለይ የአቃቂ ቃሊትና የንፋስ ስልክ ከፍለከተማዎች ዉስጥ መጠነኛ መረባበሽ ፈጥሮ እንደነበር ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡
በምሽቱ የኢቢሲ የዜና ዘገባ የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን የከተማዋን ከንቲባ መግለጫ ከዜና በኋላ ያቀረበ ሲሆን በከተማዋ ፍጹም የሆነ ሰላምና ጸጥታ መስፈኑን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ነበር፡፡ ለመንግሥት ቅርብ እንደሆነ የሚነገርለት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዛሬ ማለዳ በድረገጹ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነሩን ጠቅሶ እንደዘገበው በከተማዋ ፀረ ሰላም ኃይሎች ከሚያናፍሱት የፈጠራ ወሬ በስተቀር የተፈጠረ አንዳችም ኮሽታ የለም ብሏል፡፡
አሁን ዘግይቶ በደረሰን መረጃ አለምገና አካባቢ አንድ ቀበሌ 08 በአማጺዎች የተቃጠለ ሲሆን ከምሽት ጀምሮ ፖሊሶችና ሲቪል የለበሱ የደኅንነት ሰዎች በየቤቱ እያንኳኩ ወጣቶችን ለውይይት እንፈልጋችኋለን በማለት ወዳልታወቀ ስፍራ እየወሰዷቸው ይገኛሉ፡፡
አለምገና አዲስ ሰፈር ሱቆች ሙሉ በሙሉ የተዘገቡ ሲሆን ምንም አይነት የተሸከርካሪ እንቅስቃሴ ተገድቧል፡፡ አካባቢውም በፖሊስ ኃይል ተወሯል፡፡ ትምህርት ቤቶች ዝግ ናቸው፡፡ ዛሬ ማለዳ ሶስና ትምህርት ቤትን ለማቃጠል ሞክረዋል የተባሉ ወጣቶች በፖሊስ ኃይል እየተጫኑ ነበር፡፡
ዛሬ ጠዋት አለምገና አዲስ ሰፈር ከየስ ዉኃ አለፍ ብሎ የሚገኝ ሀይፐርግላስ ሮቶ ፋብሪካ በእሳት እየጋየ እንደሆነ ከአካባቢው የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ጭሱ ከርቀት ይታያል ብለዋል፡፡ ይህ ፋብሪካ እንዲቃጠል የሆነው ባለቤቱ ከአመጹ ቀደም ብሎ ብዙ ሰራተኞችን የመንግሥት ተቃዋሚ ናቸው ብሎ ሲያሳስር ስለነበር ነው የሚሉ ያልተጣሩ መረጃዎች ደርሰውናል፡፡
እዚያው ሰፈር ሚካኤል አካባቢ የሚገኝ ፌሮ ማምረቻ አዲስ እየተሰራ የነበረ ትናንትና ማምሻውን በእሳት ጋይቷል ተብሏል፡፡ ሌሎች 2 የመንግስት ታርጋ የለጠፉ መኪኖችም ተቃጥለዋል፡፡ የፌሮ ማምረቻ ፋብሪካው ጥበቃ ሰው ላይ መተኮስ በመጀመሩ በሰልፈኞች ጉዳይ ደርሶበታል ተብሏል፡፡