ዋዜማ ራዲዮ- የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃይል አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ እሸቱ ደሴ በቅርቡ ወደ ካናዳ ለመጓዝ የቪዛ ጥያቄ አቅርበው ክልከላ ተደርጎባቸዋል፡፡ ጉዟቸው ታልሞ የነበረው ለመንግሥታዊ ጉዳይ ይሁን ለግል ማወቅ አልተቻለም፡፡ ኾኖም የቪዛ ክልከላው ባለፉት 9 ወራት ከቆየው የኦሮሚያ አመጽ ጋር ተያይዞ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመው ሊሆን ይችላል በሚል ጥርጣሬ መነሻነት እንደሆነ ተገምቷል፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ወታደሩን የማዘዝ ስልጣን ከነበራቸው አልያም አብይ የሰብአዊ መብት ጥሰትና የሰዎች ግድያን ባስፈጸመ መዋቅር ዉስጥ መሆናቸው ከተረጋገጠ የቪዛ ጥያቄያቸው ክልከላ ሊገጥመው እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ያስረዳሉ፡፡ ያም ሆኖ አቶ እሸቱ ደሴ የቪዛ ጥያቄያቸው ላይ ይግባኝ የማለት መብታቸው የተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡
አቶ እሸቱ ደሴ በመስከረም 20፣ 2008 በአዳማ ከተማ ተደርጎ በነበረው የጨፌ አምስተኛ የሥራ ዘመን፣ አንደኛ ዓመት፣ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የአቶ ሙክታር ከድር ምክትል ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስቴር ሆነው አገልግለዋል፡፡
በቅርቡ በኢሬቻ የተፈጠረውን አደጋ ተከትሎ የክልሉ መንግሥት ሁኔታውን ለማረጋጋት እየሞከረ ያለው የጸጥታ ኮሚቴ ከሚመሩት የኦህዴድ አመራሮች አንዱ አቶ እሸቱ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ክልሉን ወክለው ወደ ሚዲያ እየወጡ ያሉት እርሳቸው ናቸው፡፡ ይህም የሆነው ኦህዴድን እንዲመሩ የተመረጡት አቶ ለማ መገርሳ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ለመመረጥ ጥቂት ጊዜያት ስለሚቀራቸው ነው፡፡ ይኸ ሁኔታ የፈጠረው ክፍተት አቶ እሸቱ በአስቸጋሪ ወቅት ወደፊት እንዲመጡ ሳያስገድዳቸው አልቀረም፡፡
ካናዳ በቪዛ ጥያቄ ጥብቅ የሰብአዊ መብት ፍተሻ ከሚያደርጉ አገራት የምትመደብ ናት፡፡