ዋዜማ ራዲዮ- ለዛሬ (ቅዳሜ) የተጠራው የሰማያዊ ፓርቲ ጉባኤ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መታገዱ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፅ/ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ወንድሙ ጎላ ጠቅላላ ጉባኤው እንዳይደረግ መከልከላቸውን ምክንያት እድርገው የገለፁት በፓርቲው የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን የተጠራው ጠቅላላ ጎባኤ የፕሬዝዳንቱን እውቅና ባለማግኘቱ ነው።
ሁለቱ ወገኖች ማለትም ስራ አስፈፃሚው እና ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽኑ ልዩነታቸውን በመፍታት ጠቅላላ ጉባኤውን ማድረግ አለባቸው ሲሉ አቶ ወንድሙ ተናግረዋል። ለዛሬ (ቅዳሜ) በፓርቲው የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን የተጠራውን ጠቅላላ ጉባኤ በተመለከተ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ይልቃል ጌትነት ሆን ተብሎ ፓርቲውን የማፍረስ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በቦርዱ ትእዛዝ የተሰረዘው ጉባኤ መስከረም 21 እንዲደረግ እንጥራለን ሲሉ የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን አንጃው ተጠሪዎች ለዋዜማ ሪፖርተር ተናግረዋል።
የፓርቲው ፕ/ት ይልቃል ጌትነት ፅ/ቤቴ መግባት አልቻልኩም ማህተሙንም ተነጥቄአለሁ ብለዋል።
ለፓርቲው ስራ ውጭ ሀገር ቆይቼ ስመለስ የፅ/ ቤቴ ቁልፍ ተቀይሮና እንዳልገባ ተደርጎአለሁ ያሉት ፕሬዝዳንቱ ነገሩን በዝምታ እየተከታተልኩ ነው ብለዋል ።
በሰማያዊ ፓርቲ ቤት ያለው ሁኔታ ሲታይ እንደቀደሙት አንድነትና ቅንጅት ፓርቲዎች የመከፈል አደጋ እንዳንዥበበት ብዙ ሰዎች ሲናገሩ ይሰማል።
ጠቅላላ ጉባኤውን ከፕሬዝዳንቱ እውቅና ውጭ ለማድረግ የተነሱት ቡድኖች በመንግስት የገንዘብ ድጎማ የሚደረግላቸውና ፓርቲውን ለመከፋፈል ስራ የተሰጣቸው ወገኖች ናቸው ሲሉም የሚናገሩ የፓርቲው አባላት መኖራቸው ይነገራል።