ዋዜማ ራዲዮ-በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተነሳውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የግጭት ስጋት የጫረባቸው ወላጆችና ተማሪዎች የዝውውር ጥያቄን ለየዩኒቨርስቲዎቻቸው እያቀረቡ ነው፡፡
የዋዜማ የየዩኒቨርስቲው ምንጮች እንደሚገልጹት ከሆነ የዝውውር ጥያቄው እስካሁን መደበኛ ባልሆነ መንገድ እየተስተናገደ ቢሆንም የጠያቂዎቹ ቁጥር ከዕለት ዕለት እያየለ በመምጣቱ አንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች አቅጣጫ እንዲሰጣቸው ትምህርት ሚኒስቴርን ለመጠየቅ ተገደዋል፡፡
ለወትሮ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ብቻ በስፋት ያነሱት የነበረው የዩኒቨርስቲ የቅያሪ ጥያቄ አሁን በነባር ተማሪዎች በዚህ መጠንና ደረጃ መጠየቅ መጀመሩ አገሪቱ ያለችበትን የስጋት ደረጃ የሚያሳይ ሆኗል፡፡
በሌላ በኩል አዲስ አበባ የሚገኙ በርከት ያሉ ወላጆች ለከፍተኛ ትምህርት የሚያበቃ ዉጤት ያመጡ ልጆቻቸውን ክልልወደሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ለመላክ ማንገራገር መጀመራቸውን በዋዜማ ዘጋቢዎች የተሰራ ኢመደበኛ ዳሰሳ ይጠቁማል፡፡ በያዝነው ዓመት በተለያየ መርሀ ግብር 185ሺህ 772 ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምሀርት ተቋማት እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡ ኾኖም ሻል ያለ ገቢ ያላቸው አንዳንድ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ክፍለ ሀገር ወደሚገኝ ዩኒቨርስቲ ለመላክ ድፍረት ማጣታቸው እየተሰማ ነው፡፡
ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ክልልዩኒቨርስቲዎች ለመላክ ፍርሃት እንዳደረባቸውና መንግሥት እንዴት ሊያሳምናቸው እንደሚችል አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ለልጆቹ ደኅንነት ኀላፊነት እንደሚወስድ በድፍኑ በመጥቀስ መንግሥትም ስርዓት ያስከብራል፣ ይህን ወላጆች ማመን ይኖርባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አገሪቱ ላይ እያንዣበበ ያለው የሰላም እጦት ያሳሰባቸው አንዳንድ ወላጆች የነባሪ ተማሪ ልጆቻቸውን ያልተሟላ ትራንስክሪፕት ከሬጅስትራር በማስላክ በምትኩ አዲስ አበባ በሚገኙ የግል ኮሌጆች ለማስመዝገብ እየተሯሯጡ እንደሆነም ታውቋል፡፡
ከዚሁ የግጭት ስጋት ጋር ተያይዞ ባሳለፍነው ሳምንታት ዉስጥ በርከት ያሉ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች በቤተሰብ ድጋፍና የጤና ማስረጃ ጭምር በማቅረብ ይማሩባቸው ከነበሩ ዩኒቨርስቲዎች እየለቀቁ ወደ ትውልድ አገራቸው ዩኒቨርስቲዎች እየተመለሱ እንደሆነ ለዋዜማ ሬዲዮ የደረሱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ክስተት በተማሪዎች ብቻ ሳይወሰን መምህራንም በተመሳሳይ ሁኔታ ዝውውር ለማስጨረስ እየሞከሩ እንደሆነ ተረድተናል፡፡ ተጨማሪ ስታፍ ለመቅጠር ፍላጎት ባይኖረንም፣ ከፕሬዝዳንቱ በመጣ ደብዳቤ ቦታ ፈልገን እንድንቀጥራቸው ታዘናል ይላሉ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑ ግለሰብ፡፡ መምህራኑ በዝውውር የመጡት ከጅማና ከአምቦ ዩኒቨርስቲዎች እንደሆነም ረዳት ፕሮፌሰሩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የትግራይ ተወላጆች እየተቀየሩ ለምን እኛ እምቢ እንባላለን ያሉና በአዲግራትና በአክሱም ዩኒቨርስቲዎች የአንድ ባች ተማሪዎች የነበሩ በቁጥር 16 የሚሆኑ ወጣቶች ለትምህርት ሚኒስትር የቅያሪ ጥያቄና የአቤቱታ ደብዳቤ ያስገቡ ሲሆን ምላሻቸውንም በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ለዋዜማ ሪፖርተር ገልጸውለታል፡፡ ተማሪዎቹ በብዛት አማራ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የመዛወር ፍላጎት ያላቸው ናቸው፡፡
ለምን አሁን የዝውውር ጥያቄ እንዳቀረቡ ተጠይቀው ሲመልሱም ረብሻ ቢነሳ ኢላማ እንዳንሆን በመስጋት ነው ሲሉ ከፊሎቹ በወላጆቻቸው ግፊት፣ አንዳንዶቹም ብዙ ጓደኞቻቸው የዝውውር ሂደትን እንደጀመሩ በመስማታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ትግራይ በነበረ ጊዜ አንድም ቀን “ዘረኝነት ያለበት መገለል” ከሕዝቡም ሆነ ከዩኒቨርስቲ ማኅበረሰብ ደርሶበት እንደማያውቅ የገለጸ ሌላ ወጣት “ለመቀየር እየሞከርኩ ያለሁት ፌስቡክ ላይ የማያቸው ነገሮች ስላስፈሩኝ ነው” ይላል፡፡ ይኸው ወጣት ትግርኛ ተናጋሪ የሆኑ ተማሪዎች ከወለጋና ከሐረማያ ወደ መቀሌ መቀየራቸውን መስማቱን ተናግሯል፡፡ “የሚሳካልኝ አይመስለኝም፣ እኔም እድሌን ልሞክር ብዬ ነው ፕሮሰሱን የጀመርኩት” ሲል ያክላል፡፡
ዩኒቨርስቲ ዝውውር ለማካሄድ አንዳንድ ጊዜ የትምህርት ሚኒስቴር ይሁንታ ሳያስፈልግ ሁለቱ ዩኒቨርስቲዎች ደብዳቤ በመጻጻፍ ብቻ ሊፈጽሙት የሚችልበት ጊዜ ያለ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የተማሪ በጀት መዛወር ያስፈልጋል ስለሚባል የትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ ግድ የሚልበት ሁኔታ አለ፡፡ ኾኖም በተማሪ ዝውውርና ቅያሪ ጋር ተያይዞ ይህ ነው የሚባል ወጥ አሰራር የለም፡፡
በተለምዶ የዩኒቨርስቲ መምህራን ቤተሰቦቻቸውን ከአንድ ዩኒቨርስቲ ወደ ሌላ ዩኒቨርስቲ የማስቀየር ልዩ መብት እንዳላቸው የሚነገር ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይመስላል የዩኒቨርስቲ መምህራን በዝውውር ጥያቄ መቸገራቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ መምህር የሆነ ግራጅዌት አሲስታንት ባለፉት ሳምንታት ከወዳጅ ዘመዶቹ ልጄን ከክፍለ አገር ዩኒቨርስቲ ወደ ከተማ አስቀይርልኝ የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ እንደቀረበለትና ነገሩ ግራ እንደገባው ለዋዜማ ሪፖርተር ተናግሯል፡፡ ጥያቄው ሲደጋገምብኝ ነው ሲሪየስ ችግር እንዳለ ያወቅኩት ይላል በመገረም፡፡
ባለፉት ሳምንታት በመተማ በጎንደርና፣ በባህርዳር በትግራይ ተወላጆች ላይ ደረሰ የተባለው ዘርን ያማከለ ጥቃት ተከትሎ ልጆቻቸውን በወለጋ፣ በሐረማያ፣ በጎንደርና ባህርዳር ዩኒቨርስቲዎች ያስተምሩ የነበሩ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ስጋት ገብቷቸዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ልጆቻቸውን ወደ አዲስ አበባና ትግራይ ዉስጥ ወደሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ለመቀየር የሞከሩ ብዙ ናቸው፡፡ ከፊሎቹም አሳክተውታል፡፡ከፊሎቹ ተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ ባለመኖሩ ምርጫ አጥተዋል፡፡ ባሳለፍናቸው ሁለት ሳምንታት ብቻ በርከት ያሉ መምህራን ከአምቦ፣ ከሐረማያ፣ ከጎንደርና ከወለጋ ዩኒቨርስቲዎች በመልቀቅ ትግራይ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች እንዲቀጠሩ ከፕሬዝዳንቶቹ የትብብር ደብዳቤ ማግኘታቸውን የዋዜማ ምንጮች ገለጸዋል፡፡
የመምህራን ዝውውር የብሔር ግጭቶች ከመነሳታቸው ቀደም ብሎም ሌሎች የጤናና የቤተሰብ ምክንያቶች እየተሰጡት ዉስጥ ለዉስጥ ይካሄድ እንደነበር የገለጹ መምህራን በበኩላቸው አሁን ጥያቄው እየበረታ መሄዱ ከግጭቶች መበራከትና አገሪቱ ካለችበት ፖለቲካዊ አጣብቂኝ ጋር የሚያያዝ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ፡፡ኾኖም ከዘር ጉዳይ ጋር በተያያዘ የቅያሪና የዝውውር ወትሮም የነበረና የጤና ሽፋን እየተሰጠው በድብቅ ይካሄድ እንደነበር አልሸሸጉም፡፡
የአዲስ አበባ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ከሳምንታት በፊት ባወጣው የሥራ ማስታወቂያ ወደ ዩኒቨርስቲው ተወዳድረው የሚያልፉ መምህራን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይሰሩበት ከነበረ ዩኒቨርስቲ መልቀቂያ እንዲያገኙ እንደሚመቻች ገልጾ ነበር፡፡