Singer Abdu Kiar
Singer Abdu Kiar

ዋዜማ ራዲዮ- በአሮጌው ዓመት መጨረሻ በተከሰቱ ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች የተነሳ የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ተከትሎ ለአዲሱ ዓመት መቀበያ የተሰናዱ ሙዚቃዎች እንዲሰረዙ ሆነዋል፡፡ አዲሱን የኢትዮጵያዊያን ዓመት አስመልክቶ የተሰረዙት የሙዚቃ ዝግጅቶች በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በአውስራሊያ በመካከለኛው ምስራቅ እንዲሁም በአገር ቤት እንዲካሄዱ የተሰናዱ ነበሩ፡፡
ይህ በአመዛኙ በማኅበራዊ ሚዲያ ጫና የተከሰተና በውል የሚታወቅ አካል ያልመራው የሙዚቃ እቀባ ዘመቻ በሙዚቀኞች ላይ ብቻም ሳይሆን በባንዶችና በሙዚቃ አሰናጆች ላይ ከፍ ያለ ኪሳራን ማስከተሉ ተሰምቷል፡፡
በአገር ቤት የሚታተመው ሳምንታዊው ፎርቹን ጋዜጣ ሁለት የሙዚቃ አሰናጆችን ጠቅሶ ባስነበበው ዘገባ ኪሳራው ለአሰናጆቹና ለሙዚቀኞቹ በሚሊዮን የሚገመት ነው፡፡
በጊዮን ሆቴል እንደሚካሄድ ሲጠበቅ የነበረውና ከ15 ቀናት ቀደም ብሎ ሰፊ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እንደተነገረለት የተገለጸው የአብዱ ኪያርና የብርኩታዊት ጌታሁን የሙዚቃ ድግስ ዝግጅቱ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት እንዲሰረዝ ሲደረግ ዘፋኞቹ በድምሩ ከግማሽ ሚሊዮን ብር ያላነሰ ገቢን እንዲያጡ ሆነዋል፡፡
በተለይም አብዱ ኪያር ከጊዮን ኮንሰርቱ ባሻገር በእስራኤል ሊያቀርበው የነበረው ዝግጅት ለመሰረዝ በመገደዱ ጫን ያለ ኪሳራን ለማስተናገድ ተገዷል፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎ በመቀሌ የነበረውን ዝግጅቱን መሰረዙ ይታወቃል፡፡ የጊዮኑን የአዲስ ዓመት ኮንሰርት አስመልክቶ ሰፋፊ ቢልቦርዶች በከተማዋ ዋና ዋና አደባባዮች ተሰቅለው ነበር፡፡ አርቲስቱ ከአናጁ ጋር በመመካከር ዝግጅቱን ለመሰረዝ እንደወሰነ ለቪኦኤ የገለጸ ሲሆን እዮሃ ኢንተርቴይነመንት ብዙ ወጪ የወጣበት ዝግጅት በመሰረዙ እስከ ስድስት መቶ ሺ ብር ሳይከስር እንዳልቀረ ተዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል የአውሮራ ፕሮዳክሽን በፋና ፓርክ ያሰናዳው የሙዚቃ ድግስ የከተማው ትልቁ የሙዚቃ ኮንሰርት የነበረ ሲሆን 4 ዓለማቀፍ ዝና ያላቸው ሙዚቀኞችንም አስመጥቶ ነበር፡፡ የዚህ ድግስ ማጣፈጫ እንዲሆን ታስቦ የነበረው ልጅ ሚካኤል በመጨረሻው ሰዓት ራሱን ከድግሱ ለማግለል ቢገደድም ዝግጅቱ እንዲቀጥል መደረጉን ሌላው ሳምንታዊ የቢዝነስ ጋዜጣ ካፒታል ዘግቧል፡፡
የአውሮራ ፕሮዳክሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ሸዊት ቢተው ለሳምንታዊው ፎርቹን በጉዳዩ ዙርያ በሰጡት አስተያየት ብዙዎቹ ዘፋኞቹ ዝግጅታቸውን እየሰረዙ ያሉት ወደፊት የሚደርስባቸውን መገለል በመፍራት ነው፡፡
አቶ ሸዊት የሚመሩት አውሮራ ፕሮዳክሽን ለ6 ወራት የዘለቀ ድርድር ከውጭ ዘፋኞች ጋር ሲያደርግ መቆየቱናና በሚሊዮን የሚቆጠር ወጪ ማውጣቱን በመጥቀስ ዝግጅቱን ሊሰርዘው እንደማይቻለው ለሳምንታዊው ካፒታል ጋዜጣ ተናግሯል፡፡
ከኢትዮጵያ ዉጭ የተሰናዱ ዝግጅቶችም ተመሳሳይ እጣ ገጥሟቸዋል፡፡ ድምጻዊት ቤተልሄም በቀለ ለንደን ዉስጥ የዋዜማ ዝግጅቷን ለምን እንደሰረዘች ለቪኦኤ ስትናገር የኢትዮጵያዊያን ለቅሶ እኔንም ይመለከተኛል፣ ወጣቱ እየረገፈ እኔ እዚህ የምጨፍርበት አቅም የለኝም ብላ ነበር፡፡ ቪኦኤ ያነጋገራቸው 8 የሚሆኑ ድምጻዊያን በተመሳሳይ መልኩ ዝግጅታቸውን መሰረዛቸውን ገልጸው ነበር፡፡ አርቲስት ሚካኤል ለማ፣ ሄለን በርሄ፣ ደረጀ ደገፋ ዝግጅታቸውን ከሰረዙት መሐል ይገኙበታል፡፡ የዕቀባ ዘመቻው ከመጀመሩ ቀደም ብለው ዝግጅታቸውን መሰረዛቸውን ከገለጹት መሐል አርቲስት አብይ ላቀው ትገኝበታለች፡፡ ሰው እየሞተ የምዘፍንበት አንጀት የለኝም ያለችው አብይ፣ በቺካጎ፣ አትላንታ ዳላስ እና ላስቬጋስ የነበራትን ዝግጅት መሰረዟን የገለጸችው በፌስቡክ ነበር፡፡
ብርሃኑ ተዘራ በበኩሉ ወገኔ እየሞተ ዘፈን የለም ሲል ለቪኦኤ የአማርኛው ክፍል የገለጸ ሲሆን አስቴር አወቀና መሐሪ ደገፋው የዋሽንግተን ሲያትል ዝግጅታቸውን በተመሳሳይ መልኩ መሰረዛቸውን አስታውቀው ነበር፡፡ ኤፍሬም ታምሩና ማዲንጎ አፈወርቅ ያሉበት ሌላ የሲያትል ዝግጅትም በተመሳሳይ ሁኔታ መሰረዙ ይታወሳል፡፡
የዋዜማ ሪፖርተር ያነጋገረው የሙዚቃ ፕሮሞተር ለአዲስ ዓመት በሚዘጋጁ ተመሳሳይ የሙዚቃ ድግሶች መሪ ዘፋኞች ከመቶ ሀምሳ እስከ ሦስት መቶ ሺ ብር ክፍያን እንደሚያገኙ ይገልጻል፡፡ በድምሩ 26 የሚሆኑ ሙዚቀኞች ዝግጅታቸውን መሰረዛቸው ታሳቢ ቢደረግ ሙዚቀኞቹ በድምሩ ወደ አምስት ሚሊዮን ብር ማጣታቸውን መገመት ይቻላል ይላል ፕሮሞተሩ፡፡ አንድ መለስተኛ የሙዚቃ ድግስን ለማሰናዳት የቦታ ኪራይና የማስታወቂያ ወጪን ጨምሮ በትንሹ ስምንቶ መቶ ሺህ ብር ያላነሰ ወጪን የሚጠይቅ እንደሆነ የገለፀው ይኸው ፕሮሞተር አገር ቤት በተለያዩ ፓርኮችን ሆቴሎች የተሰረዙ ከ12 ያላነሱ ድግሶችን በግሉ እንደሚያውቅ ጠቅሶ በድምሩ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አስወጥቷቸው ሊሆን እንደሚችል ይገምታል፡፡ ብዙዎቹ ቀብድ የተቀበሉ ሙዚቀኞች ከአሰሪዎቻቸው ጋር ለመግባባት የሞከሩት ወደፊት ያለክፍያ ኮንሰርት ለማቅረብ ፈርመው ነው ሲል ከገለጸ በኋላ የሙዚቀኞችን ስም ዝርዝር ከመግለጽ ግን ተቆጥቧል፡፡
በተያያዘ ዜና የሙዚቃ እቀባውን ዘመቻ ቸል ብለው ሥራዎቻቸውን ካቀረቡት ሙዚቀኞች መካከል ሰሜ ባላገሩና አብነት አጎናፍር ይገኙበታል፡፡ በናሁ ቲቪ የበዓል ዝግጅት 4 ያህል ሙዚቃዎችን ያቀነቀነው አብነት አጎናፍር ሲሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከሀርመኒ ሆቴል በቀጥታ ይተላለፍ በነበረው ዝግጅት ሥራዎቹን ያቀረበው ሰማኸኝ በለው ገና ከማግስቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ዛቻዎች እየተሰነዘሩበት ይገኛሉ፡፡ ቦሌ ቡልቡላ የሚገኘውን የቤቱን አድራሻ ጭምር በፎቶ በማስደገፍ ሕዝብ እንዲያወግዘው የጠየቁ የማኅበራዊ ሚዲያ አዝማቾች አልታጡም፡፡
ሰማኸኝ በለው ሥራዎቹን ባቀረበበት መድረክ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ የመግቢያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ጉዳዩን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር በየቦታው ይሄን አመት የሐዘን ዓመት እንዲሆን የሚፈልጉአንዳንድ ወንድሞቻችን ፈልገውም ተገደውም ኮንሰርት እንሰርዛለን ወደሚል ወዳልሆነ አቅጣጫ እንዲሄዱ የተደረጉ ወንድሞች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ሲሉ በሙዚቀኞች ላይ የነበረውን ጫና ለማንጸባረቅ ሞክረዋል፡፡
አስተያየቱን ለዋዜማ ሪፖርተር የገለጸው የሙዚቃ ፕሮሞተር ዘመቻው አግባብነት የሌለውና የግለሰቦቹን ሰርቶ የመኖር ነጻነትም መጋፋት ነው ካለ በኋላ ለመስቀል ደፍሮ ሙዚቃን የሚያዘጋጅ ይኖራል ብዬ አልገምትም ሲል ዘመቻው በመስቀል በዓል ላይም ጥላውን እንዳጠላ ይናገራል፡፡