ዋዜማ ራዲዮ- የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በድጋሚ በጋምቤላ ክልል ባደረሱት ጥቃት 18 ሰዎች መግደላቸውን የአካባቢው ተወላጆች ገለጹ፡፡ በርካታ ህጻናትም ታፍነው ተወስደዋል፡፡
ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የፈጸሙት ባለፈው አርብ እና ቅዳሜ የአኙዋ ተወላጆች በሚኖሩባቸው መንደሮች ነው፡፡ አርብ መጋቢት 1 ከቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ ጂሎ ወንዝ አቅራቢያ በምትገኘው አንጄላ መንደር በተከፈተ ጥቃት ስድስት ሰዎች ሲገደሉ ሁለት መቁሰላቸውን የአኙዋ ተሟጋች ድርጅት “አኙዋ ሰርቫይቫል” ገልጿል፡፡ አራት ህጻናትንም አፍነው መውሰዳቸውን አስታውቋል፡፡
ከትናንት በስቲያ መጋቢት 2 እኩለ ቀን ኦባዋ የተሰኘችውን መንደር በተመሳሳይ የወረሩት የሙርሌ ታጣቂዎች 12 ሰዎች ገድለው ሁለት ማቁሰላቸውን ድርጅቱ ይፋ አድርጓል፡፡ የአካባቢው ተወላጆች ግን የሟቾቹንም ሆነ የቁስለኞቹን ቁጥር በአንድ ከፍ ያደርጉታል፡፡ ደርጅቱ ከመንደሯ ታፍነው የተወሰዱ ህጻናት ቁጥር 21 ሰው ሲል የአካባቢው ተወላጆች ደግሞ 22 ነው ባይ ናቸው፡፡ የአካባቢው ተወላጆች በፎቶግራፍ አስደግፈው በማህበራዊ ድረ ገጽ ባወጡት መረጃ ታጣቂዎቹ መኖሪያ ቤቶችንም አቃጥለዋል፡፡
የሙርሌ ታጣቂዎች ቅዳሜ ዕለት ኦትዮዎ ወደተሰኘች ሌላ መንደር በመሄድ ተጨማሪ ህጻናትን አግተው መውሰዳቸውን “አኙዋ ሰርቫይቫል” ገልጿል፡፡ ከደቡብ ሱዳን የሚነሱት ታጣቂዎች በጥር ወር መጨረሻ ተመሳሳይ ጥቃት ፈጽመው 13 መግደላቸውን 20 ህጻናትን አፍነው መውሰዳቸውንም አስታውሷል፡፡ ይህ ጥቃት መፈጸሙን የጋምቤላ ክልል መንግስት አረጋግጧል፡፡
የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ባደረሱት ጥቃት ወደ 200 የጋምቤላ ተወላጆችን ህይወት መቅጠፋቸውን ተከትሎ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ ታፍነው የተወሰዱ ህጻናትን ከማስመለስ ጎን ለጎን የድንበር ቁጥጥሩን ለማጥበቅ ቃል ተገብቶ ነበር፡፡ ሆኖም የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ድንበር እያቋረጡ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ጥቃት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል፡፡ ታጣቂዎቹ “ሰሞኑን በጋምቤላ ድንበር አካባቢ ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ” የሚሉ ጭምጭምታዎች ከቀናት በፊት ተሰምተው ነበር፡፡